Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, August 6, 2018

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ባለስልጣን ፍርድ ቤት ቀረቡ


 በአዲስ አበባ ከተማ ሰኔ 16 ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ ሒደቱን በማቀነባበር የተጠረጠሩት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ባለስልጣን ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ባለስልጣኑ ፍንዳታውን በውጭና በሃገር ውስጥ ካሉ ሃይሎች ጋር በማቀነባበርና የጥቃቱን አድራሾች በማስተባበርም ተጠያቂ መሆናቸው ተመልክቷል።
ቅዳሜ ሰኔ 16/2010 በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ለመደገፍ በተጠራው ትዕይንተ ሕዝብ ላይ በተሰነዘረው የቦምብ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ 150 ያህል ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል።
ቦንቡን በቀጥታ በመወርወርና ሒደቱን በቅርብ በማስተባበር የተጠረጠሩ እንዲሁም በዕለቱ በቂ ጥበቃ ባለማድረግ ክፍተት የተው የፖሊስ ባለስልጣናት መታሰራቸው ይታወቃል።
ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መምሪያ ሃላፊ የነበሩ ሲሆን የሰኔ 16ቱን ጥቃት በዋናነት በማቀነባበር ተጠርጣሪ መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ባለስልጣኑ ከሐገር ውስጥና በውጭ ካሉ ሃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ቦምቡን የሚያፈነዱ ሰዎችን በመመልመልና በማሰማራት ጥቃቱ እንዲፈጸም ማድረጋቸው ተመልክቷል።
ፖሊስ በባለስልጣኑ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የገንዘብ ምንጫቸውንና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ከባንኮችና ከኢትዮ-ቴሌኮም መረጃ ለመሰብሰብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍርድቤቱን ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱም የ7 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደፈቀደም ተመልክቷል።
የቀድሞው ባለስልጣን በዋስትና ለመውጣት ያቀረቡትንም ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።
ሰኔ 16/2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ከተሰነዘረው የቦምብ ጥቃት ባሻገር ከመወርወሩ በፊት በቁጥጥር ስር የዋለውን ቦምብ በተመለከተም ምርመራ መቀጠሉም ተመልክቷል።
በዕለቱ በቂ ጥበቃ ባለማድረግ አደጋው እንዲከሰት ምክንያት ሆነዋል የተባሉ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነርን ጨምሮ 10 ያህል ከፍተኛ የፖሊስ ሃላፊዎች መታሰራቸውም ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials