በሜቴክ ስር ይተዳደር የነበረው የሞጆ ዋየርና ኬብል ፋብሪካ በዘረፋ ምክንያት መስራት ባለመቻሉ ሊዘጋ ነው ሲሉ ሰራተኞች ስጋታቸውን ለኢሳት ተናገሩ ።
ፋብሪካው ከውጭ የሚገባለት ጥሬ እቃ ባለመኖሩም ከእንቅስቃሴ ውጪ እንዲሆን መደረጉንም ጠቁመዋል።
በፋብሪካው ውስጥ ያሉት በርካታ ምርቶችና ጥሬ እቃዎችም እየተባላሹ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን ችግር የተናገሩ ሰራተኞችም ከደሞዝ ቅጣት ጀምሮ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ ባለ ኮንቴነር ለቀናት እንደሚታሰሩም አጋልጠዋል።
ከተቋቋመ ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል። አሉሚኒየም፣ኩፐርና የኤሌክተሪክ ገመዶችን ያመርታል።
በእነዚህ ዓመታት የተመረቱ ምርቶች በአብዛኛው የሚቀርቡት ለከፍተኛ የመንግስት ተቋማት ቢሆንም በዋናነት ግን ምርቱ የሚላከው ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ መሆኑን ይናገራሉ።
ነገር ግን ምርቱ ደረጃውን ያልጠበቀ በመሆኑ በተቋማቱ ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩንና ወደፊትም ችግሩ የሚከሰት መሆኑን ሰራተኞቹ ስጋታቸውን በግልጽ አስቀምጠዋል።
እንደምሳሌም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ግንባታን ያነሳሉ።
በዚህ የባቡር ግንባታ ላይ የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ገመድ በተደጋጋሚ መፈንዳቱና ባቡሮችም በየቦታው ቆመው እንደነበር አስታወሰዋል።
ፋብሪካው ከሚያመርታቸ ምርቶች ውስጥ ጥራት አለው ተብሎ የሚነሳው በቤት ውስጥ ለሚዘረጉ የኤሌክትሪክ መስመሮች የሚውለው ገመድ ሲሆን ይህ ምርት የህወሃት አባል ለነበሩትና ጉዳት ደርሶባቸው ከአባልነት ተቀንሰው በማህበር እንዲደራጁ የተደረጉት እነሱ ብቻ እንዲወስዱት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
ፋብሪካው የጥሬ እቃ የሚቀርብለት ከኳታር ቢሆንም አቅርቦቱ ግን ደረጃውን ያለጠበቀና መወገድ የሚገባው ምረት እንደሆነም ይናገራሉ ።
የሚቀርበው ጥሬ እቃ የተበላሸ በመሆኑም በርካታ ሰራተኞች ለከፍተኛ ህመም መዳረጋቸውን ይናገራሉ።
በተለይም የምርት ማጠናቀቂያ ክፍል የሚሰሩ ሰራተኞች ለዓይን ህመም ተዳርገዋል፣ በዚህም ምክንያት ስራ የለቀቁ መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ምርቱ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም ብለው የሚከራከሩ የጥራት ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች በግዴታ ጥራቱን የጠበቀ ነው እንዲሉ እንደሚገደዱና ማስፈራሪያም እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም ሰራተኞቹ ያሉ ችግሮችን ሲናገሩም ከፍተኛ የአስተዳደር በደል እንደሚደርስባቸው ፣ የአንድ ዓመት ደሞዛቸውን እንደሚቀጡ፣ ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው፣ በተጨማሪም በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ባለ ኮንቴነር ውስጥ ከሁለት እስከ ሶስት ቀናት እንደሚታሰሩ ተናግራዋል።
ሰራተኞቹ እንደሚሉትንም ለሰባት ዓመታት ያህል በስማቸው ሁለት ፔሮል እየተዘጋጀ በሰራተኛው ስም በርካታ ገንዘብ ሲበዘበዝ ቆይቷል።
ዝቀተኛው ደሞዝ ሰባት ሺ ተብሎ በአንደኛው ፔሮል ላይ የሚሰፍር ሲሆን ለሰራተኛው የሚከፈለው ግን አንድ ሺ አምስት መቶ ብቻ መሆኑን አጋለጠዋል።
በከፍተኛ ተከፋዮችም ላይ ተመሳሳይ እንደሆነ በቅርቡ በተደረገ ስበሰባ ላይ በግልጽ ለሰራተኛው ተገልጿል ይላሉ ።
በሰረተኛው ላይ እንደዚህ ዓይነት በደል እየደረሰ ለተሃድሶ፣ ለበዓል በሚል ሰበብ ለሰዓታት ዝግጅት እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደሚባክንም ሰራተኞቹ አልሸሸጉም ።
ለዚህ ግን የተወሰደ ርምጃ የለም በማለት አሁን ጥቂቶች በፈጸሙት ዝርፊያ በርካታ ሰራተኞችን የሚያስተዳደረው ፋብሪካ በምርት አቅርቦት ችግር የተነሳ ሊዘጋ መሆኑን በምሬት ይናገራሉ።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፋብሪካው ሰራተኛ እንደሚሉት ሰራተኛው ይህንን አይነት ችግር ሲደርስ እየተመለከተ ከሚደረስበት በደልና ግፍ ለመሸሽ ሲል እስከዛሬ ዝምታን መርጦ ቆይቷል።
No comments:
Post a Comment