Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, August 15, 2018

"ሄጎ በየኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ባንዲራ ተመልሶ ሁከት እየፈጠረ ነው" (የጅግጅጋ ወቅታዊ ሁኔታ)

"ሄጎ በኦብነግ ባንዲራ ተመልሶ ሁከት እየፈጠረ ነው"
(የጅግጅጋ ወቅታዊ ሁኔታ)
በትናንትናው እለት በጅግጅጋ ከተማ የመንግስት መኪኖችን ጭምር በመጠቀም አብዲ ኢሌ ያደራጃቸው ሄጎ የተባሉ ቡድኖች የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባርን (ኦብነግ/ONLF) ባንዲራ በመያዝ ብጥብጥ ለመፍጠር ሞክረዋል። ሰሞኑን ክልሉን በማረጋጋት ላይ ከነበረው የመከላከያ ሰራዊት ጋር በፈጠሩት ግጭት ምክንያት መከላከያ ሰራዊት በመሳሪያ ሀይል ለመበተን የተገደደ ሲሆን በተከፈተው ተኩስም የፖሊስ መኪና ላይ የኦብነግ ባንዲራ ሰቅሎ ሲያሽከረክር የነበረ የሂጎ አባል ቆስሏል።
በሌላ በኩል ህዝቡ ከነዚሁ ሂጎ ከተባሉ ቡድኖች ጋር በድንጋይ እየተወራወረ የነበረ ሲሆን መከላከያ ሰራዊት ወደቦታው ደርሶ ግጭቱን ቢያበርድም ሂጎዎቹ ግን በመኪና እየተጫኑ መከላከያ ወደማይቆጣጠረቻው አካባቢዎች አምልጠዋል።
በክልሉ በተቋቋመው የኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ጄነራል ሀሰን እንደገለፁት ከሆነ ኦብነግ ራሱን ሂጎ ከሚባሉት በመነጠል እና ስርዓት አልበኝነታቸውን በማውገዝ የለውጡን ሂደት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ አምስት የሚደርሱ የአብዲ ኢሌ ደጋፊዎች የሚመሩ (Somali Printing, Delta Printing, Jigjiga Jet, Fiqi Printing, Nation Voice, Gadhle Printing) ማተሚያ ቤቶች በሂጎ መሪ በሆነው በልዩ ፖሊስ አዛዥ አብዱራህማን ወንድም አብዱላሂ ትዕዛዝ የሶማሌ ሪፐብሊክ ባንዲራ በብዛት እየታተመ ሲሆን ኦብነግን ለመቀበል ነው በሚል እየተዘጋጀ ባለ ሰልፍ ላይ የሚያዙ ባነሮችም እየተዘጋጁ ነው። ባነሮቹ የሶማሌን መገንጠል የሚያወሱ፣ ነዳጁ የሶማሌ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ ወራናለች እና የመሳሰሉትን መፈክሮች ታትመውባቸዋል።
በተለይም የአብዲ ኢሌ ዘመድ እና የጎሳው አባል የሆነው የኦብነጉ ቃል አቀባይ አዳኒ ሂርሙግ ከትናንት በስተያ ወደ ሀገር ቤት ከመግባቱ በፊት ለቢቢሲ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ "የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሶማሌን ህዝብ ወሮታል ህዝቡ ወጥቶ ይቃወማቸው" ማለቱን ተከትሎ የአብዲ ኢሌ ደጋፊዎች ኦብነግን ከአብዲ ኢሌ ቅፅል ስም (CMC) ጋር በየባነሮቹ እና መኪናዎች ላይ በመፃፍ ቅስቀሳ እያደረጉ እና ባቃጠሏቸው ቤተ ክርስቲያኖች ሱቆች እና በዘረፏቸው መኪኖች ላይ ONLF እና CMC እያሉ ሲፅፉ እንደነበር ይታወሳል - ይሄው ቅስቀሳ አሁንም ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኮማንድ ፖስቱ ሀላፊዎች ኦብነግ ይህን ስርዓት አልበኝነት ያውግዝ ከማለት ባለፈም - "እንዲህ ያለውን ሁኔታ አንታገሰውም" በማለት አስጠንቅቀዋል። ከህዝቡ ጋር በነበረው ውይይትም በዚሁ የአብዲ ኢሌ ደጋፊዎች እየተሰራጨ ያለውን ፕሮፖጋንዳ በጋራ አውግዘው - ሰላማችን እና የለውጥ ተስፋችን እንዳይቀለበስ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ቆመው እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የክልሉ ምሁራንም በግጭቱ የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም እየሰሩ ሲሆን - የተቃጠሉ ቤተ ክርስቲያኖችም ተመልሰው እንዲሰሩ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን የክልሉ ምሁራን አስተባባሪዎች ገልፀውልኛል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials