በአዲስ አበባ መካኒሳ የሚገኘው የአንበሳ ከተማ አውቶብስ ጋራዥ በእሳት እንደጋየ ተጠቀሰ።
በቃጠሎው ግምቱ ወደ 45 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚደርስ ንብረት ሙሉ በሙሉ መውደሙንም ሪፓርቶች ገልጸዋል።
በዚህ የእሳት አደጋ በጋራዡ ለጥገና የቆሙ 11 አውቶብሶች ነደው ከጥቅም ውጭ መሆናቸውም ተገልጻል።
የእነዚህ 11 ሙሉ በሙሉ በእሳቱ የወደሙት አውቶብሶች ግምታቸው ወደ 18 ሚሊዮን ብር እንደሚጠጋ ለማወቅ ተችሏል።
በመካኒሳ በተለምዶ ጀሞ በሚባለው ቦታ በሚገኘው የአንበሳ የከተማ አውቶብስ ጋራዥ የተከሰተው ይህ የእሳት አደጋ የድርጅቱን የእቃ መለዋወጫና ማከማቻው ሌሊቱን ሙሉ በሙሉ አውድሞት አድሯል።
የአንበሳ የከተማ አውቶብስ የመካኒሳ ዲፓ ቅርጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ገብር ኪዳን ድርጅቱ ሌሊቱን ሲነድ በማደሩ እጅግ ከፍተኛ የገንዘብና የንብረት ውድመት መከሰቱን ለመንግስት ሚዲያ ገልጸዋል።
የድርጅቱ የዲፓ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጁ ይህንን ያህል ንብረት ያወደመውን የእሳት አደጋ መንስኤ ምን እንደሆነ ከማሳወቅ ተቆጥበዋል።
ስራ በሌለበት ለቅዳሜ አጥቢያ አርብ ሌሊት በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከሌሊቱ ዘጠኝ 9 ሰአት በዚሁ ጋራዥና በእቃ ማከማቻው ላይ እንዴት እሳት ሊነሳ ይችላል የሚል የጥርጣሬ ጥያቄዎች እየተበራከቱ ቢገኙም የከተማው ፓሊስ ቢሮም ሆነ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ጉዳዩን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።
ከሌሊቱ ዘጠኝ 9 ሰአት በጋራዡና በእቃ ማከማቻው ላይ የተነሳው እሳትን ለመቆጣጠር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኤጄንሲ ሰራተኞች በቦታው ተገኝተው እንደነበረም ተዘግቧል።
በተከሰተው የእሳት አደጋ ምንም አይነት የህይወት መጥፋት እንዳልተከሰተ ተገልጻል።
አባይ ሚዲያ ዜና በዘርይሁን ሹመቴ
No comments:
Post a Comment