Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, February 27, 2017

የአውሮፓ ፓርላማ አባላት በሱዳን በኢትዮጵያውያን ላይ የተላለፈውን ግርፋትና እስር ተከትሎ ለሃገሪቱ የሚሰጠው ድጋፍ እንዲቋረጥ ጠየቁ


ኢሳት (የካቲት 20 ፥ 2009)
የሱዳን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰሞኑን በኢትዮጵያውያን እና ኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ ያስተላለፈውን የግርፋት እና የእስር ቅጣት ተከትሎ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ለሃገሪቱ ስደተኞችን ለመደገፍ የሚሰጣት ድጋፍ እንዲቋረጥ ጠየቁ።
በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራዊያን ስደተኞች በሱዳን መንግስት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንደሚፈጸምባቸውና ድርጊቱ ሱዳን ከአውሮፓ ህብረት ጋር በቅርቡ የደረሰችውን ስምምነት የሚጻረር እንደሆነ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት መግለጻቸውን ዘጋርዲያን ጋዜጣ ሰኞ ዘግቧል።
የአውሮፓ ፓርላማ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ባርባር ሎችቢህለር ባለፈው ሳምንት የሱዳን ፍርድ ቤት ስደተኞች በግርፋት እንዲቀጡ ያስተላለፈው ውሳኔ ምርመራ እንዲካሄድበት አሳስበዋል።
ከለላን ፍለጋ በሱዳን የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የሁለቱ ሃገራት ዜጎች እየተፈጸመባቸው ካለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተጨማሪ ወደሃገራቸው ያለፍላጎታቸው እንዲሄዱ መደረጉንም ዘጋርዲያን ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።
በቅርቡ አብዛኞቹን ኢትዮጵያውያን የሆኑ 65 የኢትዮጵያና የኤርትራ ስደተኞች በትከሻቸውና በውስጥ እግራቸው ላይ ግርፋት እንደተፈጸመባቸው ጋዜጣው የህግ አካላትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ከስደተኞቹ መካከል 40ዎቹ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን፣ የግርፋት ቅጣት የተላለፈባቸው ስደተኞች 800 የአሜሪካን ዶላር ቅጣት እንደተጣለባቸውም ታውቋል። ይሁንና የሱዳን መንግስት በስደተኞቹ ላይ እየፈጸመ ያለው ድርጊት በአውሮፓ ፓርላማ አባላትና በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።
የአውሮፓ ህብረት ሱዳን ሃገሩን ተጠቅመው ወደ ተለያዩ ሃገራት የሚሰደዱ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ለምታደርገው ጥረት ወደ 100 ሚሊዮን አካባቢ የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ ዙሮች ለመስጠት ስምምነት ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ሃገሪቱ በስደተኞች ላይ እየወሰደችው ባለው ኢሰብዓዊ ድርጊት ቅሬታቸው እየገለጹ ያሉ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ህብረቱ የገንዘብ ድጋፉን እንዲያቋርጥ ጥሪን አቅርበዋል። የፓርላማ አባሏ ባርባራ ህብረቱ በአስቸኳይ ምርመራውን እንዲያካሄድ እና አቋሙን ግልፅ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ጁዲን ሳርጀንቲን የተባሉ ሌላ የፓርላማ አባል በተያዘው ሳምንት ተመሳሳይ ጥያቄያቸውን ለፓርላማው እንደሚያቀርቡ ለዘጋርዲያን ጋዜጣ ገልጸዋል።
የሱዳን መንግስት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እየገረፈና እያሰረ እንዲሁም ያለፍላጎታቸው ወደ ሃገራቸው እየመለሰ ባለበት ወቅት ለሃገሪቱ የምንሰጠው ድጋፍ ህጋዊነቱ አጠያያቂ ነው ሲሉ የፓርላማ አባሏ አክለው ተናገረዋል። ስማቸው መግልጽ ያልፈለጉና በሱዳን የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተወካዮች በበኩላቸው ሱዳን በስደተኞች ላይ እየወሰደችው ያለው ወከባ እየተባባሰ መምጣቱን አስረድተዋል።
የሱዳን መንግስት በቅርቡ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የደረሰውን ስምምነት ውጤት ያስገኘ ለማስመሰል በሃገሪቱ በሚገኙ ስደተኞች ላይ ከመጠን ያለፈ የሃይል ዕርምጃን እየወሰደ እንደሚገኝ እነዚሁ አካላት አክለው አስረድተዋል።
የሱዳን መንግስት ለመኖሪያ ፈቃድ አገልግሎት የሚያስከፍለው ክፍያ እንዲጨምር ማድረጉን ተከትሎ በካርቱም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ክፍያው ፍትሃዊ እንዲሆን ጥረት እንዲያደርግላቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል። ይሁንና በኤምባሲው ፊት ለፊት ሲካሄድ የነበረው ጥያቄ ለደህንነት ስጋት ነው በሚል የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች በስፍራው እንዲሰማሩ መደረጉን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለመገናኛ ተቋማት ሲገልጹ ቆይተዋል።
እነዚሁ የሱዳን የጸጥታ አባላት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለእስር መደረጋቸውን እና ከ40 የሚጠልጡትም የግርፋት ቅጣት እንደተበየነባቸው ሱዳን ትሪቢዩን መዘገቡ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials