Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, February 26, 2017

ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ሌሎች የተቃዋሚ ድርጅት አመራሮች ላይ የቀረበው ክስ ፖለቲካዊ ነው ሲል ሂውማን ራይትስ ወች አስታወቀ

 ከሶስት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባላት ጋር ለመወያየት ወደ ቤልጅየም በመሄድ በኅብረቱ ፓርላማ በመገኘት ንግግር አድርገው ሲመለሱ የታሰሩት የ60 ዓመቱ ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ሌሎች የተቃዋሚ ድርጅት አባላት ላይ የቀረቡባቸው ክሶች ሕጋዊነት የሌላቸው ፖለቲካዊ ክሶች ናቸው ሲል የሂውማን ራይትስ ወች የምስራቅ አፍሪካ ዋና አጥኚ ፊሊክስ ሆርን ገልጸዋል። ባለፈው ሃሙስ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ፕ/ሮ ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ጃዋር መሀመድ፣ ኢሳት እና ኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች መከሰሳቸው የሚያመለክተው ገዥው ፓርቲ የሽብር ሕጉን ተገን በማድረግ የሰላማዊ ትግሉን ለማፈኛነት ተጠቅሞበታል ሲል በሪፖርቱ አመላክቷል።
ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዓመፅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ተገለዋል። ከአስር ሽህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ማእከላዊን ጨምሮ በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ታስረዋል። መንግስት ለሕዝባዊ ተቃውሞው ዘላቂ የመፍትሄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አስቸኳይ የጊዜ አዋጅ በማውጣት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መጣሱን የሚገልጸው ሂውማን ራይትስ ወች፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት ላይ ግድያ፣ እስራት እና ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች እየፈጸመ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ፖለቲካዊ የተሃድሶ ለውጦችን አደርጋለሁ ቢልም፣ እስካሁን ግን በተግባር የታዩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች የሉም። በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን በማሰር ሰላማዊ የትግል አማራጮች እንዲዘጉ ተደርገዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን እንዲሰፍን ገዥው ፓርቲ ፈቃደኝነት ማሳየት ከፈለገ በእስር ላይ የሚገኙትን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች በነጻ ሊለቃቸው ይገባል ሲል ሂውማን ራይትስ ወች አስታውቋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials