Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, February 14, 2017

በደሴ የሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ በደህንነቶች ተገደሉ ተባለ



በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ ሰኞ በ6/06/2009 ዓ.ም አንጋፋው ሰላማዊ ታጋይ አቶ ጋሹ ጌታሁን በመኪና ተገጭቶ ህይወቱ አለፈ፡፡

አቶ ጋሹ ጌታሁን ከሚሰራበት የደሴ ከተማ ገቢዎች ፅ/ቤት ሲወጣ ፤ አብረሀም የተባለ የመቀሌ ነዋሪ የቻይና ዜጎችን ይዞ ወደ መቀሌ ሲያሽከረክረው በነበረ፣ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 A43458 አ.አ ፣ ንብረትነቱ የስኳር ኮርፖሬሽን የሆነ ፣ ቪ 8 መኪና በአሰቃቂ ሁኔታ ተገጭቶ ህይወቱ ወዲያውኑ ሊያልፍ እንደቻለና የቀብር ስነ ስርአቱም ማክሰኞ እለት በደሴ ከተማ ስላሴ ቤተክርስቲያን ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት መፈፀሙን ፤ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

አቶ ጋሹ በቀድሞው አንባሰል አውራጃ ሚልዋ ቀበሌ የተወለደ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሀይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ አቶ ጋሹ ጌታሁን በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን የመጀመሪያ ድግሪ ያለውና ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ ህይወቱን እስካጣበት እለት በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሀገሩንና ህዝቡን ሲያገለግል ቆይቷል፡፡

ህልመኛውና ቆራጡ ሰላማዊ ታጋይ ጋሹ ጌታሁን የቀድሞው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አባል በመሆን የፖለቲካ ተሳትፎውን የጀመረ ሲሆን በ1997 ዓ.ም በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ ለመሆን በቅቷል፡፡

በመቀጠልም በቀድሞው አንድነት ፓርቲ የዞን ሰብሳቢና በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥም የዞኑ ስራ አስፈፃሚ በመሆን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ለሀገርና ለህዝቡ ነፃነት በሰላማዊ መንገድ ሲታገል የነበረ ፤ አንደበተ ርትዑና ቆራጥ ሰላማዊ ታጋይ ነበር፡፡

አቶ ጋሹ በሰላማዊ ትግሉ ሂደት ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያስተናገደና በፅናት የተወጣ ድንቅ የህዝብ ልጅ ሲሆን ፤ የናፈቃትን ነፃነትና ዴሞክራሲ እውን ሆና ሳያይ፤ ቤተሰቡን በትኖ ህይወቱን ሊያጣ ችሏል፡፡

ጋሹ ጌታሁን የሁለት ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ሲሆን የቤተሰቡም ብቸኛ አስተዳዳሪ ነበረ፡፡ የጋሹን ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ የቀጠፈው የመኪና አደጋ ፤ ‹‹ በአጋጣሚ ወይስ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ›› የሚለውን ለማጣራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከስፍራው ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ ከመኪናው ዘመናዊነት አንፃር አስከሬኑን ከ50 ሜትር በላይ በጎማው ይዞ መጓዙና ከአስፋልት ዳር ላይ ተጠልፎ መገጨቱ ፣ የአደጋውን ሁኔታ አጠራጣሪ እንዳደረገው ቤተሠቦቹ ገልፇል፡፡

ታጋይ ጓዳችን ጋሹ ጌታነህ ፣ አራት ልጆቹን በሚያገኘው ወርሀዊ ገቢ የሚያስተዳድር ሲሆን በአሁኑ ሰአት ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሂዋን ያልደረሱ ልጆቹና መላው ቤተሠቡ ህልውና አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ ለማወቅ ተችሏል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials