Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, February 2, 2017

Internet Spy የኢንተርኔት የስለላ ወንጀል ክስ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በሚገኝ የይግባኝ ፍርድ ቤት ሊታይ መሆኑ ተገለጸ

የኢንተርኔት የስለላ ወንጀል ክስ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በሚገኝ የይግባኝ ፍርድ ቤት ሊታይ መሆኑ ተገለጸ
ኢሳት (ጥር 24 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ መንግስት ላይ በአንድ አሜሪካዊ ዜጋ የተመሰረተ የኢንተርኔት የስለላ ወንጀል ክስ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በሚገኝ የይግባኝ ፍርድ ቤት ሊታይ መሆኑ ተገለጸ።
ኪዳኔ ቪ የተባሉት አሜሪካዊ የቀረበውን ክስ በውክልና ይዞ የሚገኘው ኤሌክትሮኒክስ ፍሮንቴየር ፋውንዴሽን የተሰኘ ተቋም ክሱ እንዲቀጥል የሚያስችል የመከራከሪያ ውይይት ነገ ሃሙስ ለፍርድ ቤት እንደሚቀርብ አስታውቋል።
ጆንስ ዴይ ኤንድ ሮቢንስ ካፕላን የተሰኙ ሁለት የአሜሪካ የህግ አባላት የኢትዮጵያ መንግስት በግለሰቡ ላይ የፈጸመው የረቀቀ የቴክኖሎጂ የስለላ ድርጊት ከለላ ሊሰጠው የማይገባ እንዳልሆነ ለማስረዳት የተለያዩ ማስረጃዎችን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከሶስት አመታት በፊት በአሜሪካዊው ከሳሽ ላይ የተፈጸመው ይኸው የቴክኖሎጂ የስለላ ተግባር መቀመጫውን በካናዳ ባደረገው ሲቲዝን ላብ ኩባንያ ሊረጋገጥ መቻሉን ኤሌክትሮኒክስ ፍሮንቲየር ፋውንዴሽን ገልጿል።
ይሁንና ክሱ ቀርቦለት የነበረው የፌዴራል ፍርድ ቤት በውጭ ሃገር መንግስት በግለሰቡ ላይ የተፈጸመው ድርጊት ሊያስጠይቅ የሚችል አይደለም ሲል ባለፈው አመት ምላሽ መስጠቱን ለመረዳት ተችሏል።
ክሱ በይግባኝ ቤት እንዲታይ መከራከሪያቸውን የሚያቀርቡት ሁለቱ የህግ ተቋማት ማንኛውም የውጭ አገር መንግስት የአሜሪካዊ ዜጋን መሰለል እንዳማይችሉ የሚያስረዳ የህግ መከራከሪያን በማቅረብ ክሱ በይግባኝ እንዲታይ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸው ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት መቀመጫውን በጣሊያን ካደረገ አንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የኢንተርኔት የስለላ ድርጊት ለመፈጸመ የሚያስችሉ አገልግሎቶችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሲገዛ መቆየቱን ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ይኸው የረቂቅ የስለላ ተግባር የጋዜጠኞች እና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የግል የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን የመልዕክት ልውውጥ ለመከታተልና ለመቆጣጠር ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱን የካናዳው ሲቲዝን ላብ ኩባንያ ማረጋገጡን ለመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሲገለጽ ቆይቷል።
የመረጃው ይፋ መደረግ ተከትሎ የጣሊያኑ የቴክኖሎጂ ተቋም የኢትዮጵያ መንግስት አገልግሎቱን ሲያገኝ መቆየቱን ለህዝብ እንዲታወቅ አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የደህንነት አካላት ቴክኖሎጂውን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ጉዳዩ ሊደርስበት መቻሉን አመልክቷል።
ይኸው የጣሊያን ሃኪንግ ኩባንያ ለኢትዮጵያ ሲያቀርብ የነበረው ቴክኖሎጂ ለደህንነት አገልግሎት ብቻ የሚውል መሆኑን ገልጾ መንግስት ግን ቴክኖሎጂውን ለስለላ ድርጊት ማዋሉ ተገቢ እንዳልነበርም ምላሹን ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት አገልግሎቱን ከተፈለገበት አላማ ውጭ በመጠቀሙ ሳቢያ የጣሊያኑ ኩባንያ የደረሰውን ስምምነት እንዳቋረጠ ይፋ ማድረጉም ይታወሳል።
መኖሪያቸው በዚህ በአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት የሆነው ኪዳኔ ቪ፣ የስለላ ድርጊቱ ከተፈጸመባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ መሆናቸው ታውቋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials