የብሪታኒያ መንግስት ለኢትዮጵያ የጸጥታና የዲፕሎማቲክ አባላት ስልጠና እንዲያገኙ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ምርመራ እንዲካሄድበት የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ጠየቀ።
የብሪታኒያ የፓርላማ አባላት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር እንዲፈቱ ዘመቻን እያካሄዱ ባለበት ወቅት የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ በመስጠት ላይ ያለው ይኸው ድጋፍ “አሳፋሪ” ነው ሲል ሪፕሪቭ የተሰኘ ተቋም ተቃውሞን አቅርቧል።
ከተለያዩ አለም አቀፍ አካላት የቀረበን ጥያቄ ተከትሎ የብሪታኒያ አለም አቀፍ የልማት ትብብር ለኢትዮጵያ የጸጥታ እና የደህንነት አባላት የሚሰጠው የስልጠና ድጋፍ ከሁለት አመት በፊት እንዲቀር ማድረጉ ይታወሳል።
ይሁንና ከወራት በፊት የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ እና መከላከያ ሚኒስትሮች የሚከታተሉት የግጭት የመረጋጋትና የደህንነት ድጋፍ የሚል ፕሮግራም የተጀመረ ሲሆን በዚሁ ዕድል ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እየሆነች እንደሆነ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ገልጿል።
የብሪታኒያ ህግ በሚፈቅደው ደንብ በመጠቀም ይህንኑ መረጃ መመልከት እንደተቻለ ያስታወቀው ሪፕሪቭ ተቋም፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ፣ የሰራዊት አባላት የፍትህ አካላት እንዲሁም የዲፕሎማቲክ አባላት በዚሁ አዲስ ፕሮግራም ስልጠና እንዲያገኙ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አረጋግጧል።
የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን መስሪያ ቤታቸው ድጋፍን ለምን እንደቀጠለ ማብራሪያ እንዲሰጡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ምክትል ሃላፊ ሃሪየት ማክኩሎች (Harriet McCulloch) መጠየቃቸውን The Sun የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
“ኢትዮጵያ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይን ዕልባት ባልሰጠችበት በዚሁ ወቅት የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሃገሪቱ ድጋፍ ማድረጉ አሳፋሪ ነው” ሲሉ ሃላፊዋ አክለው ገልጸዋል።
የአዲሱ ፕሮግራም መጀመርን ተከትሎ በተያዘው ወር የብሪታኒያ ፓርላማ የብሄራዊ ደህንነት ክፍል በአዲስ መልክ የተጀመረው ድጋፍ መሰረታዊ ግልፅነት የጎደለው ነው በማለት ሪፖርት አውጥቶ እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል። ይኸው ፕሮጄክት ብሪታኒያ ጥያቄን ሊያስነሱ በሚችሉ የመብት ጥሰቶች ውስጥ ተሳታፊ እንድትሆን የማድረግ አደጋ እንዳለውም የፓርላማ አባላት ስጋታቸውን አቅርበዋል።
የብሪታኒያ አለም ቀፍ የዕርዳታ ትብብር ከጥቂት አመታት በፊት ለኢትዮጵያ ሲሰጥ በቆየው ተመሳሳይ የትምህርት ድጋፍ 90 በመቶ የሚሆኑት የደህንነትና የስለላ ሃላፊዎች የእድሉ ተጠቃሚ እንደነበሩ ታውቋል።
ካለፈው ወር ጀምሮ ከ50 የሚበልጡ የብሪታኒያ የፓርላማ አባላት የሃገሪቱ መንግስት በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ላይ እርምጃን እንዲወስድ አዲስ ዘመቻ መክፈታቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ቆይተዋል።
No comments:
Post a Comment