የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከናጀሪያ ግብፅና ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ያልተከፈለው ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ በስራው ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን የድርጅቱ ሃላፊዎች ገለጹ።
አየር መንገዱ ለነዚህ ሃገራት በተለያዩ ጊዜያት የአየር ትኬትና ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች ሲሰጥ ቢቆይም ለአገልግሎቱ ክፍያ ሳይፈጸምለት በርካታ ጊዜያት መቆጠሩን ሮይተርስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ ተወልደ ገብረማሪያምን ዋቢ በማድረግ ማክሰኞ ዘግቧል።
አየር መንገዱ የተለያዩ አገልግሎትን ሲሰጣቸው የቆዩት ሃገራት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አጋጥሟቸው በመገኘቱ ምክንያት ክፍያውን ሊፈጽሙ እንዳልቻሉ ሃላፊው ለዜና አውታሩ አስረድተዋል።
የገንዘቡ ክፍያ መጓተት በስራችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖን አሳድሯል ሲሉ አቶ ተወልደ አክለው ገልጸዋል። ሁለቱ ሃገራት በስም ቢጠቀሱም ሌሎች ሃገራት ግን አልተገለጹም። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአንድ ወር በፊት ከአፍሪካ ልማት ባንክ የ150 ሚሊዮን ዶላር መውሰዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ኩባንያው ያልተከፈለው ገንዘብ በስራው ላይ ችግር መፍጠሩ ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ እገዳው የተነሳው የፕሬዚደንት ትራምፕ የጉዞ እገዳ በመንገደኞች ላይ ግራ መጋባት መፍጠሩን አስታውቀዋል።
ይሁንና ኩባንያው በድርጊቱ የተፈጠረበትን ተፅዕኖ አለመኖሩን የገለጸ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ዘጠኝ የየመን ዜጎች የእገዳው መጣልን ተከትሎ ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርጎ እንደነበር ሮይተርስ በዘገባው አስፍሯል። የአየር መንገዱ በፈረንጆቹ 2015/2016 አም አጠቃላይ ገቢው 10.3 እድገትን በማስመዝገብ 54.5 ቢሊዮን ብር መድረሱም ታውቋል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በሰባት ሃገራት ላይ የጣሉት እገዳ ከፍተኛ ተቃውሞን አስከትሎ ውሳኔው በፍርድ ቤት እንዲታገድ መደረጉ ይታወሳል።
ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ተከትሎ የመግቢያ ቪዛን ይዘው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ተደርገው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የሰባት ሃገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ በመግባት ላይ መሆናቸውን የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ይሁንና በፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ ይግባኝ የቀረበበት በመሆኑ ማክሰኞ ምሽት በካሊፎርኒያ ግዛት ሳንፍራንሲስኮ ከተማ የሚገኝ የይግባኝ ፍርድ ቤት በአሜሪካ የፍትህ ተቋምና በህግ አካላት የቀረበን የመከራከሪያ ነጥብ በማድመጥ በጉዳዩ ብይንን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካ የህግ አካላት ፕሬዚደንቱ ስልጣናቸው ተጠቅመው ያስተላለፉት ውሳኔ የሃገሪቱን ህግ የሚጻረር ነው በማለት የህግ ጥያቄን አንስተው ይገኛል።
No comments:
Post a Comment