መቀመጫውን በእንግሊዝ ዋና ከተማ ለንደን ያደረገውና በአፍሪካ በኬንያ፣ በሴኔጋልና ቱኒዚያ ጽሕፈት ቤት ያለው ‹‹አርቲክል 19›› በጋዜጠኞች የመናገርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተሟጋች ተቋም ተመራማሪ የሆነው ኬንያዊው ፓትሪክ ሙታይ ኢትዮጵያ መግባት ተከለከሉ፡፡
ኬንያዊው ባለፈው ሐሙስ ዕለት ዓርብ አጥቢያ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ኅብረት ፕሬዚዳንት አቶ አንተነህ አብርሃ ለሪፖርተር ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡
ግለሰቡ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበትን ምክንያት ሲያብራሩ፣ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ቅዳሜና እሑድ በደብረዘይት ከተማ ይካሄድ የነበረ ሥልጠናን ለመስጠት ነበር፤›› በማለት ጠቁመው፣ ‹‹ነገር ግን እሱም ሆነ ሥልጠና የሚሰጣቸው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ አባላት ምንም ዓይነት ፈቃድ የሌላቸው ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን እርሳቸው ይህን ቢሉም በምሥረታ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ፕሬዚዳንት አቶ በትረ ያዕቆብ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ስለ ጉዳዩ ዝርዝር መረጃ የለኝም፡፡ ነገር ግን ግለሰቡ ባለፈው ቅዳሜና እሑድ ሥልጠና ይሰጡ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን ሥልጠናው የተዘጋጀው ለመድረኩ አባላት ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ጋዜጠኞች ነው፤›› በማለት ውንጀላውን አጣጥለውታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹እኛ አርቲክል 19 እንደማንኛውም ተቋም ነው የምናየው፡፡ ከተቋሙ ጋር ምንም ዓይነት የተለየ ግንኙነትም የለንም፤›› በማለት መድረኩን ከተቋሙ ጋር ለማያያዝ የሚደረገውን እንቅስቃሴ አጥብቀው ኮንነዋል፡፡
አቶ አንተነህ ግን የግለሰቡ አመጣጥ ትክክለኛ አለመሆኑን አውስተው፣ ‹‹አመጣጡ የቀለም አብዮት ለማስነሳት ከሚሠሩ አካላት ጋር በመተባበር ሥልጠና ለመስጠት ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይል ወደ መጡበት እንዲመለሱ ሲደረግ ጣልቃ ገብተው ለማረጋጋት መሞከራቸውንና በዚህም የተነሳ ወደ ኢትዮጵያ ሳይገቡ ሥልጠናውን ሰርዘው ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹አርቲክል 19 እ.ኤ.አ. በ1987 የተመሠረተ ተቋም ሲሆን፣ ከአውሮፓና ከአፍሪካ በተጨማሪ በባንግላዴሽ፣ በብራዚል፣ በሜክሲኮና በአሜሪካ ጽሕፈት ቤቶች ያሉት የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን ነው፡፡ ቡድኑ ሐሳብን በፃነት ከመግለጽ ጋር በተገናኘ ከሚሠሩ የተመድና ሌሎች ተቋማት ጋር በሚያዘጋጃቸው ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች፣ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን ወይም ደረጃዎችን በሚተነትኑ ኅትመቶቹ ሲታወቅ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት የሻከረ ነው፡፡