Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, April 4, 2014

Anti gay demonstration to take place in Ethiopia ሚያዝያ 18 ቀን የፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሰላማዊ ሠልፍ እንዲካሄድ ተፈቀደ

የፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሰላማዊ ሠልፍ እንዲካሄድ ተፈቀደ

ባለፈው ዓመት ግብረ ሰዶማዊነትን ለመከላከል ሕዝብና መንግሥትን ለማስገንዘብ በኢትዮጵያ ግብረ ሰዶማዊያን ሕይወት ላይ ያተኮረ ዘጋቢ ፊልም ለሕዝብ ያበረከተው ወይንዬ አቡነ ተክለሀይማኖት የተሰኘ መንፈሳዊ ማኅበርና የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም፣ የፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያቀረቡት ጥያቄ መጋቢት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ይሁንታ ማግኘቱን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉ ሚያዝያ 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሁለት እስከ አምስት ሰዓት የሚካሔድ ሲሆን፣ አስተዳደሩ ፈቃድ የሰጠው ‹‹መጤ ባህልንና ግብረ ሰዶምን ለመከላከል›› በሚል እንደሆነ በደብዳቤ ተመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረምና ወይንዬ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ማኅበር ለአስተዳደሩ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ከሳምንታት በፊት ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት ሰላማዊ ሠልፉ ሌላ አጀንዳ ያላቸው አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳሚያስፈልግ በአስተዳደሩ ተገልጾላቸው እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ አሁንም ሰላማዊ ሠልፉ እንደተባለው የሌሎች አጀንዳዎች መንፀባረቂያ እንዳይሆን የተለያዩ የጥንቃቄ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ የማኅበረ ወይንዬ ሊቀመንበር መምህር ደረጀ ነጋሽ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሰላማዊ ሠልፉ አስተባባሪዎች ሠልፉን ለማካሄድ ለአስተደዳሩ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት እስከ ሁለት መቶ ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ  ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በሞንታርቦ በተለያዩ አካባቢዎች የጎዳና ላይ ቅስቀሳ በማድረግ፣ በፖስተሮችና በኢንተርኔት ጭምር ብዙዎች እንዲሳተፉ በማድረግ የተሳታፊዎችን ቁጥር ከተጠቀሰው  በላይ እንደሚያደርሱ አስረድተዋል፡፡
አስተባባሪዎቹ እንደገለጹት፣ የሰላማዊ ሠልፉ ዓላማ በአገሪቱ ግብረ ሰዶማዊነት አስከፊ ደረጃ ላይ እየደረሰ በመሆኑ መንግሥት ችግሩን በመረዳት ግብረ ሰዶማዊነትን የሚመለከቱ ሕጎችን ጠበቅ እንዲያደርግ ማስገንዘብ፣ ኅብረተሰቡም ችግሩን እንዲገነዘብ ማድረግ ነው፡፡
በሰላማዊ ሠልፉ ላይ እንቅስቃሴያቸውን ከመነሻው ሲደግፉ የነበሩ የተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎች ተወካዮችና የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችም እንደሚገኙ የገለጹት አስተባባሪዎቹ፣ ፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሰላማዊ ሠልፉ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በፌደራል ደረጃና በክልል ከተሞችም የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ግብረ ሰዶም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ሆነ በሌሎች ሕጎች የተከለከለና በወንጀል የሚያስቀጣ ሲሆን፣ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ መሠረት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ይቅርታ እንዳይሰጡ ዕገዳ ከተደረገባቸው የወንጀል ዓይነቶች አንዱ የግብረ ሰዶም ወንጀል ነው፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials