በቦረና እና በጉጂ ጎሳዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ወደ ሌሎች አካባቢዎችም እየተዛመተ ነው
ሚያዚያ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከትናንት በስቲያ በቦረና ዞን መልካ ሶዳ ወረዳ ሃሎ ቀበሌ 2 የጉጂ ተወላጆች ተገድለው መገኘታቸውን ተከትሎ የመልካ ሶዳ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተቃውሞ አሰምተዋል። ተማሪዎቹ ከትምህርት ቤት በመውጣት ታፔላዎችን እየነቃቀሉ መጣላቸውን፣ የወረዳው አስተዳዳሪን መኪና በድንጋይ መሰባበራቸውን እንዲሁም አቶ ቡርቃ ደምቢ የተባሉትን የወረዳው የኦህዴድ መሰረታዊ ድርጅት አደራጅን መደብደባቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ተማሪዎቹ ድርጊቱን ሲፈጽሙ የወረዳው ፖሊስ በተማሪዎች ላይ እርምጃ እንዳይወስድ ወላጆች ከፖሊስ ጋር ተፋጠው ለሰአታት ያሳለፉ ሲሆን፣ ማምሻውን የፌደራል ፖሊስ በብዛት በመምጣት አካባቢውን ተቆጣጥሯል። ተገድለው ከተገኙት መካከል አንዱ መምህር መሆኑም ታውቋል።
ከነገሌ ቦረና ስያሜ ጋር በተያያዘ የተነሳው ግጭት ሌሎች ዞኖችንም እያዳረሰ መሄዱ ያሳሰባቸው ነዋሪዎች መንግስት ችግሩን ለመፍታት ያሳየውን ቸልተኝነት እየተቹ ነው።
አገር ሽማግሌዎች ቀደም ብሎ ጉዳዩን ለመንግስት ሲያሳስቡ እንደነበር የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ መንግስት በተለይም የክልሉ ርእሰ መስተዳድር በተለያዩ ጊዜዎች አቋማቸውን መቀያየራቸውን አሁን ለተፈጠረው ችግር መንስኤ ሆነዋል ።
በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳው ባለስልጣናትን ለማነጋጋር ያደረግነው ሙከራ አልተሰካም።
No comments:
Post a Comment