ሚያዚያ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቀድሞው የህወሃት አመራርና ነባር ታጋይ በአሁኑ ጊዜ በአረና ፓርቲ ውስጥ በከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ የሚገኙት ታዋቂው ፖለቲከኛና ጸሃፊ አቶ አስገደ ገብረስላሴ ለኢሳት እንደገለጹት በሰሜን ወሎ ዞን በሰቆጣ፣ ላሌበላ፣ ዋግና ሌሎችም አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው በተነሳው ከፍተኛ ረሃብ የተነሳ ቀያቸውን ጥለው ወደ መቀሌ፣ ሽሬ፣ አክሱምና ሁመራ መሰደዳቸውን ገልጸዋል።
“አርሶደሮችን ሲያነጋግሩ ከፍተኛ ረሃብ በመከሰቱ ለመሰደድ እንደተገደዱ ገልጸውልኛል” የሚሉት አቶ አስገደ፣ “እጅግ የሚያሳዝነው እነዚሁ ዜጎች በመቀሌ ጸጉረ ልውጦች ተብለው ህክምና እንኳን እየተነፈጉ ለከፍተኛ ስቃይ እየተዳረጉ ነው” ሲሉ አክለዋል።
በእርሻ ምርቱ ይታወቅ የነበረው የጃን አሞራ አካባቢም እንዲሁ በረሃብ በመጠቃቱ አርሶአደሮች በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ መቀሌ፣ ሁመራና ሱዳን እየተሰደዱ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አስገደ፣ የቤት ሰራተኛ ለመቅጠር ሲፈለግ ” ቢጠፋ ቢጠፋ ጃን አሞራ አጣችሁ” እስከመባል መድረሱን ተናግረዋል።
“በትግራይ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች አካባቢያቸውን እየለቀቁ ወደ ሳውድ አረቢያ፣ ሱዳንና ሌሎችም ቦታዎች እየተሰደዱ ነው” ያሉት አቶ አስገደ፣ አገሪቱ በችግር ምክንያት እየፈራረሰች መሆኑዋን ገልጸዋል።
ከሳውድ አረቢያ የተመለሱ የትግራይ ወጣቶች በስራ እጦት እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ብዙዎች ተመልሰው ወደ ሱዳንና ወደ ሌሎችም አገሮች እየተሰደዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በነበሩት መንግስታት ሳይቀር ያልታየ ችግር በዚህ ዘመም መከሰቱን የሚናገሩት አቶ አስገደ መንግስት 11 በመቶ አድገናል እያለ የሚናገረው በመሬት ላይ የሌለነ ነገር ነው ብለዋል።
በሰሜን ወሎ የገጠር ቦታዎችና በጃን አሞራ አካባቢ ስላለው ችግር የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሰካልንም።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በኑሮው ውድነት መማረራቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ይህ ነው የሚባል እርምጃ እስካሁን አልወሰደም፡
ከአቶ አስገደ ገብረስላሴ ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለመልልስ ሰሞኑን ይዘን እንደምንቀርብ ለመግለጽ እንወዳለን።
No comments:
Post a Comment