Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, April 11, 2014

የኢትዮጵያ መንግስት በረዳት አብራሪ ኃይለመድህን አበራ ላይ ክስ መሰረተ



በተመስገን ደሳለኝEthiopian Airlines plane Co-Pilot Hailemedehin Abera Tagegn charged

-ከ253, 336 ከ42 ሳንቲም ዩሮ በላይ ኪሳራ ደርሷል ተብሏል

-የአእምሮ ችግር እንዳሌለበትም ተረጋግጧል

ፍትሕ ሚኒስቴር በረዳት አብራሪ ኃይለመድን አበራ ላይ የካቲት 9 ቀን 2006 ዓ.ም ሌሊት የበረራ ቁጥር ET 702 የሆንን ቦይንግ አውሮፕላንን ከእነ 202 ተሳፋሪዎቹ ወደ ሮም በሚበርበት ወቅት ጠልፎ ሲውዘርላንድ አሳርፏል በማለት በከፍተኛው ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ክስ መመስረቱን የፍትሕ ሚኒስቴር ምንጮቼ አረጋግጠውልኛል፡፡
በኃይለመድን ላይ የቀረበው ክስ ሁለት ሲሆን፤ የመጀመሪያው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 507/1/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ፡-
‹‹…በዋና አብራሪ ፓትዮዝ ባርቤሪ አማካኝነት ከአዲስ አበባ በሱዳን በኩል ወደ ጣሊያን ሀገር ሮም ከተማ መንገደኞችን ለማድረስ በማጓጓዝ ላይ እንዳለ ዋናው አብራሪው የበረራ መቆጣጠሪያውን ክፍል ከውስጥ በመቆለፍ፣ ያለፍቃድ እና በሕገ-ወጥ መንገድ አውሮፕላኑን በቁጥጥር ሥር በማድረግ የአውሮፕላኑ የበረራ ቡድን አባላት በሩን እንዲከፍት ሲጠይቁት አርፋችሁ የማትቀመጡ ከሆነ በአውሮፕላኑ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ በማስፈራራት፤ እንዲሁም የአውሮፕላኑን የመዳረሻ አቅጣጫ ያለአግባብ በማስቀየር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈቃድ ውጭ ወደ ስዊዘርላንድ አየር ክልል ውስጥ በመግባት ተሳፋሪዎች እና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ሕይወት እና ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጎ በመጨረሻ በጄነቭ ከተማ ውስጥ ያለመዳረሻው እንዲያርፍ በማድረጉ እና ተሳፋሪዎችን ለአደጋ በማጋለጡ በፈፀመው በሕገ-ወጥ መንገድ በጉዞ ላይ ያለን አውሮፕላን መያዝ ወይም ማገት›› የተከሰሰ መሆኑን ያትታል፡፡
በሁለተኛነት የተመሰረተብት ክስ ደግሞ በዚሁ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 508/1/ ላይ ያለውን መተላለፍ የሚል ሲሆን፤ ክሱም በአጭሩ እንዲህ ይላል፡-
‹‹…ያለፍቃድ እና በሕገ-ወጥ መንገድ አውሮፕላኑን በቁጥጥር ሥር በማድረግ የአውሮፕላኑ የበረራ ቡድን አባላት በሩን እንዲከፍተው ሲጠይቁት አርፋችሁ የማትቀመጡ ከሆነ በአውሮፕላኑ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ በማለት በማስፈራራት አውሮፕላኑን በድንገት እና በፍጥነት ሁለት ጊዜ ከፍ እና ዝቅ (dive) በማድረግ በአውሮፕላኑ ውስጥ ያሉትን የመንገደኞች ምግብ ማቅረቢያ ቁሳቁሶች እንዲገለባበጡ በማድረግ፣ የአውሮፕላኑን የመዳረሻ አቅጣጫ ያለአግባብ በማስቀየር፣ ከአትዮጵያ አየር መንገድ ፈቃድና እውቅና ውጭ ስዊዘርላንድ አየር ክልል ውስጥ በመግባት ስዊዘርላንድ ከተማ ጀኔቭ በመግባት አየር ላይ በማንዣበብ ከቆየ በኋላ እንዲያርፍ በማድረግ በፈፀመው በሕገ-ወጥ መንገድ በጉዞ ላይ ያለን አውሮፕላን አስጊ ሁኔታ ላይ መጣል ወንጀል ተከሷል፡፡››
በፌ/አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ወንድምአገኝ ፊርማ ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ማመልከቻ ከስ ቻርጁን ጨምሮ አስራ አንድ ገፅ ሲሆን፤ የዋና አብራሪው፣ የአምስት የበረራ አስተናጋጆች እና የአራት ሰዎች ስም ዝርዝር በመስክርነት ተገልፆአል፡፡ በሰነድ ማስረጃነት ደግሞ አየር መንገዱ በ27/6/06 ዓ.ም ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የጻፈው አራት ገጽ እና ሲቪል አቬየሽን በ21/6/06 ኃይለመድንን በተመለከተ የጻፈው ማብራሪያ ከነአባሪው ሁለት ገጽ ቀርቧል፡፡
የኃይለመድን አበራን የጤንነት ሁኔታ በተመለከተ አየር መንገዱ ለፌደራል ፖሊስ በላከው ደብዳቤ በስድስት ወር ውስጥ አምስት ጊዜ ያህል ለቀላል ሆድ ቁርጠት፣ ራስ-ምታት፣ ጉንፋንና ተቀምጥ ወደ ድርጅቱ ክሊንኪ ከመሄዱ ያለፈ ምን ችግር ያሌለበት ጠኔኛ እንደሆነ ገልፆአል፡፡ ሲቪል አቬሽንም በተመሳሳይ መልኩ በላከው ደብዳቤ አብራሪው አመታዊ የጤና ምርምራ አድርጎ እ.ኤ.አ. እስከ 22/12/2014 ዓ.ም ድረስ ጤነኛ መሆኑን ማረጋገጫ ሰርተፍኬቱን አድሶ እንደሰጠው አስታውቋል፡፡ አየር መንገዱ ከዚሁ ጋር አያይዞ ሁለት መቶ ሀምሳ ሶስት ሺህ፣ ሶስት መቶ ሰላሳ ስድስት ብር ከአራባ ሁለት ሳንቲም ዩሮ ኪሳራ እንደደረሰበት እና በቀጣይም ተጨማሪ ክፍያዎች እንደሚኖሩበት ገልፆአል፡፡ እንደ ምንጮቼ አገላለፅ መንግስት ክሱን በሚስጥር የያዘው ሲሆን፤ እስካሁንም በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎቹ ላይ ጉዳዩን በዜና እንዲገለፅ አላደረግም፡፡
የሆነው ሆኖ ዋናው ጥያቄ ኃይለመድን ጠለፋውን ባፈፀመበት ወቅት ‹‹እብድ›› (የአእምሮ ችግር ያለበት) ለማስመሰል የተደረገው ሙከረ ውሸት እንደሆነ በአየር መንገዱና በሲቪል አቬሽን ተፅፈው ከክሱ ጋር የተያያዙት ደብዳቤዎች በማረጋገጣቸው፣ የጠለፋው ምክንትያት ምንድን ነው? የሚለው ይመስለኛ፡፡ በርግጥ ምንም እንኳ ምክንያቱን አብራሪው በሲዊዘርላንድ ፍርድ ቤት ቀርቦ እሲኪናገር መጠበቅ እንዳለብኝ ባልዘነጋም፤ በግሌ እጅግ አፋኝና ነውረኛ የሆነው ሥርዓት ላይ ያለውን ተቃውሞ ለመግለፅ ያደረገው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ ኃይለመድንን ሊወቀስና ሊወገዝ የሚችልበት ነገር የለም፡፡ አየር መንገዱ የሕዝብ መሆኑ ባይካድም፤ በአሁኑ ወቅት የጥቂት ጉምቱ ባለሥልጣናት መፈንጫ እና ኪስ ማደለቢያ መሆኑ መዘንጋት የለበትምና፡፡
ከዚህ አንፃርም ከሀገር ውጪ ላሉ ወገኖቼ ሁለት መልዕክት ማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡ የመጀመሪያው የኃይለመድን ስልት ዞሮ ዞሮ በሰላማዊ ትግል ማዕቀፍ ውስጥ መውደቁ የማይቀር ነውና፣ ጉዳዩ በጀብደኝነት አሊያም የተሳፋሪዎችን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥልና ኃላፊነት በሚሰማው፣ ሙያውንም ሆነ የወሰደው እርምጃ የሚኖረውን ውጤት አስቀድሞ በሚያውቅ የተፈፀመ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ማሕበረሰቡ ላይ ግፊት በማድረግና ጉዳዩ ጭቆናን ከመቃወም ጋር እንደሚየያዝ በማሳመን ከተጠያቂነት የሚድንበትን መንገድ ማፈላለግ ላይ ማተኮር ሲሆን፤ ሁለተኛው ኢህአዴግ እስርኞችን በማሰቃየት ግንባር ቀደም በመሆኑ ተላልፎ እንዳይሰጠው ከጎኑ መቆም ማድረግ ላይ እንድታተኩሩ (ምናልባት ከክሱ ጋር የተያያዙ ማስረጃዎች የምትፈልጉ የሕግ ባለሙያዎች እዚህ ጋ በአታችመንት ከተቀመጡት ዶክመንቶች በተጨማሪ በኢሜል ልልክላችው እችላለሁ)
በመጨረሻም የግፍ አባት የሆነውን ነውረኛ ሥርዓት ለመቀየር (አማራጮቹ እየጠበቡ በመሄዳቸው) እንዲህ አይነት መንገዶችንም ግምት ውስጥ ማስገባት የግድ እንደሆነ መረደት ይኖርብናል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment

wanted officials