የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ፕሮግራሙ ላይ በቀረበበት ክስ ተረታ! -በፕሮግራሙ ያስተላለፈውን ስም አጥፊ ዘገባ እንዲያርም ታዟል ! – ታምሩ ጽጌ
የኢትዮጵያ ሬዲየና ቴሌቪዥን ድርጅት ከኅዳር 16 እስከ 18 ቀን 2004 ዓ.ም. በተከታታይ ሦስት ክፍሎች ‹‹አኬልዳማ›› በሚል ባቀረበው ዘጋቢ ፕሮግራም፣ክብርና ዝናን የሚያጠፋ በድምፅ፣ በምስልና በጽሑፍ በተቀነባበረ መንገድ ስሙን እንዳጠፋው በመግለጽ፣ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በመሠረተበት የፍትሐ ብሔር ክስ ተረታ፡፡
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ዘጠነኛ የፍትሐ ብሔር ችሎት መጋቢት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ፣ አንድነት ፓርቲ መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም. ባቀረበው ክስ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትንና ፕሮግራሙን አቅርቧል በተባለው አቶ አብዲ ከማል ላይ ክስ መመሥረቱን አስታውሷል፡፡
አንድነት በክሱ እንዳብራራው፣ በዲስፕሊን ግድፈት ከፓርቲው የተባረሩትን፣ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁትንና በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኙትን ግለሰቦችና ተከሳሾች፣ የፓርቲው አባል እንደሆኑ አድርጐ በፕሮግራሙ ማሳየቱ አግባብ አለመሆኑን በክሱ አቅርቧል፡፡ ፓርቲውንና ሕጋዊ አባላቱን ሁከትና ብጥብጥ ፈጣሪዎች እንደሆኑ አድርገው ስም ማጥፋታቸውን አክሏል፡፡ ፓርቲውና ሕጋዊ አባሎቹ አሸባሪ ተብሎ በሕግ የተፈረጀው ግንቦት 7 የተባለው ድርጅት፣ በህቡዕ በፓርቲው ውስጥ ሰርጐ እንደገባና እንደተደራጀ እያወቁ ሽፋን እንደሰጡ አድርገው ማቅረባቸውን አንድነት በክሱ አካቶ አቅርቧል፡፡ ፓርቲውን ግንቦት 7 የተባለው ድርጅት ለህቡዕ አደረጃጀት እየተጠቀመበት መሆኑንና የፓርቲው አባል ያልሆኑትን ወይም አባል ለመሆናቸው ምርጫ ቦርድ ያላረጋገጠለትን የሰዎች ስም በመጥቀስ አባል እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ ተከሳሾቹ የፓርቲውን ስም ማጥፋታቸውን በመዘርዘር ለችሎቱ ክሱን ማቅረቡን ውሳኔው ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ ስም የሚያጠፋውን ፕሮግራም የሠሩት ሆን ብለው፣ አቅደውና አስበው፣ ፓርቲው በሌሎች ወገኖች እንዲጠላ፣ እንዲዋረድ፣ እንዲሳቅበት፣ ያለው ተወዳጅነት፣ እምነት፣ መልካም ዝና ወይም የወደፊት ዕድሉ እንዲበላሽ በማድረግ፣ በቀጣዩ ምርጫ ሕዝቡ ጥርጣሬና ውዥንብር ውስጥ ገብቶ ድምፅ እንዲያጣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያገኘውን የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ ለማዳከም በማሰብ የተፈጸመ መሆኑን አንድነት በክሱ ዘርዝሮ ማቅረቡን ክሱ ያብራራል፡፡
ድርጅቱና አቅራቢው የስም ማጥፋት ዘገባውን የሠሩት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 24(1) የመልካም ስም መከበር መብትን፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999 አንቀጽ 30(1) እና አንቀጽ 16(1)ሠን አንቀጽ 30(2)ን በመተላለፍ መሆኑንም የውሳኔው መዝገብ ይገልጻል፡፡ ሌላው ዘገባውን ከሠሩ በኋላ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 40(1)ለንም ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አንድነት በክሱ መጥቀሱንና የምስክሮችንም ስም ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡን ውሳኔው ያብራራል፡፡
ተከሳሹ ድርጅት በሰጠው ምላሽ ስም የማጥፋት ወይም የሐሰት ዘገባ አለመሥራቱን፣ በፕሮግራሙ የዘገበው እውነት መሆኑን፣ የማንንም ስም ለማጥፋት አቅዶ የሚንቀሳቀስ ተቋም አለመሆኑን፣ የፌዴራል መንግሥትና የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት በመሆኑ በሕግ የተጣለበትን እውነትን የመዘገብና ለሕዝብ መረጃ የማቅረብ ግዴታውን በአግባቡ የሚወጣ ተቋም መሆኑንም አስረድቷል፡፡
በፕሮግራሙ ያቀረበው ዘገባ እውነትና ትክክለኛ መሆኑን፣ ሁሉንም የሚመለከቱትን አዋጆች ባከበረና መሠረት ባደረገ መንገድ መሆኑን፣ ሕዝብ መረጃ የማግኘትን መብት መሠረት ባደረገ የሕግ አስከባሪ አካላት የወሰዷቸውን ዕርምጃዎች ምንነት ማሳወቅ ግዴታ ስላለበት፣ በተጨባጭ መረጃ ተደግፎ የቀረበ እንጂ የማንንም ስም ለማጥፋት ተብሎ የተላለፈ ፕሮግራም አለመሆኑን በምላሹ አካቷል፡፡ የከሳሽ መልካም ስምና ክብሩ የተጐዳበት ዘገባ አለማስተላለፉንም አክሏል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 40(1) መሠረት አንድነት ፓርቲ ስሜና ክብሬ ተጐድቷል የሚል ከሆነ፣ በቅድሚያ ጉዳቱን ማረጋገጥ እንዳለበት ገልጾ፣ ፓርቲው ስሙና ክብሩ ባለመጐዳቱ የላከውን ማስተባበያ እንዳልተቀበለው በመልሱ አስታውቋል፡፡
የአባላቱ መልካም ስም መጥፋቱን ገልጾ ፓርቲው የመሠረተውን ክስ በሚመለከት ተከሳሹ እንዳስረዳው፣ አባሎቹ እነማን እንደሆኑ ባለመግለጹና በዘገባው መሠረት የተፈጸመውን በደል አለማረጋገጡን በመጥቀስ ክሱ ውድቀ እንዲደረግለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ድርጅቱ ዘርዘር ያለ መከራከሪያ ነጥቦችን በማቅረብ የተመሠረተበትን ክስ ተቃውሟል፡፡
በሁለተኛነት የተከሰሰው አቶ አብዲ ከማል በበኩሉ ባቀረበው የመከራከሪያ ሐሳብ የፕሮግራሙ አዘጋጅ አለመሆኑን በመግለጽ፣ አቅራቢ መሆኑንና በአዋጅ 590/2000 መሠረት ፕሮግራም አቅራቢ የሚከሰስበት ኃላፊነት እንደሌለ በማስረዳት፣ የቀረበበትን ክስ በመቃወሙ ፍርድ ቤቱም ተቀብሎ ክሱን በመሰረዝ በነፃ አሰናብቶታል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በሦስት ክፍሎች ባቀረበው ‹‹አኬልዳማ›› ፕሮግራም የአንድነትን ስም አጥፍቷል ወይስ አላጠፋም? አጥፍቷል የሚባል ከሆነ በአዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 40(1) መሠረት ማስተባበል አለበት የለበትም? የሚሉ ጭብጦችን ይዞ መመርመሩን ውሳኔው ይገልጻል፡፡
‹‹አኬልዳማ›› ፕሮግራም ከኅዳር 16 እስከ 18 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ መቅረቡ አለማከራከሩን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡ አንድነት ከፓርቲው በሥነ ምግባር ጉድለት የተባረሩትን፣ በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁትንና አባል ያልሆኑትን ወይም አባል መሆናቸው በምርጫ ቦርድ ያልተረጋገጠውን የድርጅቱ አባል እንደሆኑ በማስመሰል ‹‹አኬልዳማ›› ፕሮግራም ላይ ዘግቧል የሚለውን ፍርድ ቤቱ በጥልቀት መመርመሩን በውሳኔው ገልጿል፡፡
ፓርቲው በቴሌቪዥን ዘገባው የፓርቲው አባል እንደሆኑ ተደርጐ ተዘግቧል ያላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ገልጾ በክሱ ባለማቅረቡ፣ ጥያቄው ለፍርድ ቤቱም ሆነ ለተከሳሽ ድርጅት አስቸጋሪ መሆኑንና በደፈናው መቅረቡ ተከራካሪ ወገን የመከራከር መብትንም የሚያጣብብ ሆኖ በማግኘቱ፣ የአንድነትን ክርክር ውድቅ ማድረጉን ውሳኔው ያሳያል፡፡ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 33 እና 231 ድንጋጌዎች መሠረት የቀረበ አለመሆኑንም ጠቁሟል፡፡
ፓርቲውንና ሕጋዊ አባላቱን በሕግ ከተፈረጀው ግንቦት 7 ጋር በህቡዕ ግንኙነት እንዳላቸው በማስመሰል፣ አመራሮቹ ግንቦት 7 በህቡዕ በፓርቲው ውስጥ ሰርጐ እንደገባና እንደተደራጀ እያወቁ ሽፋን ሰጥተዋልና ግንቦት 7 አንድነትን ለህቡዕ አደረጃጀት እየተጠቀመበት መሆኑን በመግለጽ፣ ፓርቲው የመሠረተውን ክስና ተከሳሽ ድርጅት ያቀረበው ምላሽ ፍርድ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ መመርመሩን ውሳኔው ያብራራል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ይረዳ ዘንድ ‹‹አኬልዳማ›› በሚል ርዕስ በሦስት ተከታታይ ክፍሎች የቀረበውን የቴሌቪዥን ዘገባ አስቀርቦ መመልከቱን በውሳኔው ገልጿል፡፡
በተላለፉት ዘገባዎች ውስጥ የአንድነት ፓርቲን ስም ተከትለው የሚነሱ ስምንት ነጥቦችን ለማግኘት መቻሉን በውሳኔው ዘርዝሮ አቅርቧቸዋል፡፡ በመሆኑም የአንድነት ፓርቲም ሆነ አመራርና አባላቱ በክሱ እንደዘረዘረው በሕግ ከተፈረጀው ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በዘገባው መተላለፉ የሚያከራክር አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ በሰጠው የውሳኔ ዝርዝር ውስጥ አካቶታል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 24(1) መሠረት ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት እንዳለው መደንገጉን የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ፣ አንድነት ፓርቲ መልካም ስሙ ሊከበርለት እንደሚገባ በውሳኔው አስፍሯል፡፡
አንድ ሰው በንግግሮቹ፣ በጽሑፎቹ፣ በሌላ ዓይነት አድራጐቶቹ በሕይወት ያለውን የአንደኛውን ሰው ስም በማጥፋት፣ ሰው እንዲጠላው፣ እንዲያዋርደው፣ እንዲሳቅበትና በእሱ ላይ ያለው እምነትና መልካም ዝናውና የወደፊት ዕድሉ እንዲበላሽ ያደረገ ሰው፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2044 መሠረት ጥፋተኛ እንደሚባል ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ጠቁሟል፡፡ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተረጋገጠበትን ሰው ተጠርጣሪም ቢሆን እንኳ፣ በሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል ሠርቷል ማለት ስም ማጥፋት እንደሆነ በፍትሐ ብሔር ሕግ 2109(ሀ) መደንገጉን ፍርድ ቤቱ ጠቅሶ፣ አንድነትን የሽብር ሁከትና ብጥብጥ ፈጣሪ፣ እንዲሁም በሕግ አሸባሪ ከተባሉ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ያለው ከመሆን አልፎ የሽብር ተልዕኳቸውን እንዲያሳኩ አመቻች የሆነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድረጅት መግለጹን በውሳኔው አስፍሯል፡፡
ተከሳሽ ድርጅት በጠቀሳቸው የሽብር፣ የሁከትና የብጥብጥ ፈጣሪ መሆንና በሕግ አሸባሪ በመባል ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር ሆኖ መገኘት፣ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5፣ 6 እና 7 መሠረት በወንጀል ሊያስቀጣ እንደሚችል የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ ድርጊቱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በአንድነት ፓርቲ ላይ ዘገባ ማስተላለፍ የፍትሐ ብሔር ሕግ 2044 እንዲፈጸምበት ከማድረግም በተጨማሪ፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ 2109(ሀ) መሠረት ተከሳሽ ስም ማጥፋቱን የሚያረጋግጥ መሆኑን በውሳኔው አረጋግጧል፡፡
ተከሳሹ ያስተላለፈው ዘገባ እውነትና በመረጃ የተደገፈ መሆኑን ገልጾ ያቀረበው መከራከሪያን ፍርድ ቤቱ ውድቅ ማድረጉን፣ የከሳሹ የክስ አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግ ተከሳሽ መጠየቁ የሕግ ድጋፍ እንደሌለው፣ ተከሳች በአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 24(1)ን፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ 533/1999 አንቀጽ 30(1)ንና አንቀጽ 30(2)ንና የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000ን የተላለፈ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አብራርቷል፡፡
በመሆኑም በአዋጅ 590/2000 መሠረት ከሳሽ በ‹‹አኬልዳማ›› የቴሌቪዥን ፕሮግራም ዘገባ ስሙ የጠፋበትን ማስተባበያ ዘገባ የሚያርም መልስ በቴሌቪዥን ጣቢያው እንዲያስተባብል ፍርድ ቤቱ መፍረዱን መጋቢት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ዝርዝር ውሳኔ አስታውቋል፡፡
No comments:
Post a Comment