የሙስሊሙን እንቅስቃሴ ‹‹ሽብር›› ለማስመሰል መንግስት የሚያደርገው ጥረት ሳንካዎቹን መሻገር አልቻለም!
በሐሰት ክስና በካንጋሮው ፍርድ ቤት ችሎት እየተንገላቱ ያሉት የህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ለአፍሪካ ሰብአዊና ህዝባዊ መብቶች ኮሚሽን ክስ ማስገባታቸውን የውስጥ ምንጮች ገለጹ!
በአፍሪካ ህብረት ስር ከ1987 ጀምሮ የተቋቋመውና ዋና መስሪያ ቤቱንም በጋምቢያዋ ባንጁል ያደረገው ይኸው ኮሚሽን በሂደት መንግስትን የጥፋተኝነት ብይን ካስተላለፈበት መሪዎቻችንን ጥፋተኛ እንደሆኑ አድርጎ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳመን ከፍተኛ ሳንካ እንደሚገጥመው ይጠበቃል፡፡
የኮሚሽኑ አባል አገራት ሰብአዊና ህዝባዊ መብቶችን በተመለከተ ግዴታቸውን መወጣት አለመወጣታቸውን መርምሮ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ያለው ይኸው ኮሚሽን አምነስቲንና ሂውማን ራይትስ ዎችን ከመሳሰሉ የሰብአዊ መብት አቀንቃኝ ድርጅቶች ስራ በተለየ መልኩ የሚሰጣቸው ብይኖች በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ከፍተኛ ክብደት የሚሰጣቸው ሲሆኑ መንግስት ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም በካንጋሮው ፍርድ ቤት የሀሰት ችሎት ሊፈጥር የሚፈልገው ‹‹ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ብሏቸዋል›› የሚል ስእል ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችልበትን እድል ሙሉ በሙሉ እንደሚዘጋበት ይታመናል፡፡ መንግስት ከለጋሽ አገራት በጀት ለመለመን በሚጠቀምበት ‹‹የዓለም አቀፍ ሽብር ስጋት አለብን›› ተረት ቅቡልነት ላይም የሚጋርጥበት አደጋ ቀላል እንዳልሆነ ይገመታል፡፡
ለኮሚሽኑ ከመሪዎቻችን ክስ ጋር በተያያዘ የቀረበለት አቤቱታ እስካሁን በእነሱም ሆነ በወከሉት ህዝበ ሙስሊም ላይ የደረሰውን በደል በስፋት የሚዘረዝር ሲሆን የመንግስት ካንጋሮ ፍርድ ቤትም ጉዳያቸውን በነጻነት ለማየት የሚችልበትን መዋቅራዊ አቅም የተነጠቀ በመሆኑ የአቤቱታው ሂደት በአጭሩ ታይቶ እንዲወሰንበት የሚጠይቅ ነው፡፡ አቤቱታው ሰላማዊውን የመብት እንቅስቃሴ በሐይል ለማዳፈን የተደረጉትን ሙከራዎችና በእስር ቤቶችም ውስጥ ሲፈጸምባቸው የቆየውን አሰቃቂ በደል በስፋት እንደሚያትት ምንጮቻችን አያይዘው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን በህዝበ ሙስሊሙ ላይ ሲወስድ የቆየውንና እየወሰደው ያለውን እርምጃ ዓለምአቀፍ ተቋማትና መንግስታት ሲያወግዙት የቆዩ መሆኑ ይታወሳል!
የሐሰት ከስ አይገዛንም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች ይቀጥላል!
No comments:
Post a Comment