ሠማያዊ ፓርቲ እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድነት መድረክ በመፍጠር ሰላማዊ ሰልፍ ከህዳር 27/2007 ዓ.ም እስከ ህዳር 28/2007 ዓ/ም ለማድረግ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልፀው የሐገሪቱ ህዝብ በቦታው በመገኘት ድምፁን እንዲያሠማ ባሳወቁት መሠረት የኢትዮጵያ መምህራን ድምፅ ይሠማ ጊዜያዊ ኮሚቴ እና የማህበሩ አባላት በሠላማዊ ሠልፉ ላይ ከሌላው የሐገራችን ህዝብ ጋር በመሆን ድምፃችንን እንደምናሠማ እየገለፅን ለሠላማዊ ሠልፉ መሣካት የበኩላችንን ደርሻም ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን ስንገልጽ በዚህ በጨለማ ዘመን ኃላፊነት ወስደው ይህንን ታላቅ ሠለማዊ ሠልፍ ላዘጋጁት የሠለማዊ ሠልፉ አዘጋጆች ምስጋናችንን በማቅረብ ነው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያን እያስተዳደሩ ሳይሆን እየገዙ ያሉት ብዙሀኑ ባለስልጣናት ከትምህርት አለም እርቀው ወደ ትግል የገቡ እና አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እና የተሻለ ንቃተ ህሊና ያለው ሰው እንዳይፈጠር ትግል ላይ ናቸው በተለይ ለመምህራንና ባጠቃላይ ለትምህርት ስርአቱ ያላቸው ጥላቻ ላቅ ያለ ነው ይህንን እንኳን ስላልተማሩ ነው ብለን እንዳናልፈው የስርአቱ አመራሮች እና አጃቢዎች አለማወቃቸውንም ሊደብቁ ፍቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ሟቹ መለስ ዜናዊ በህይወት ያለው ተፈራ ዋልዋ መምህራኑን ለማሰደብ አፋቸውን ከፍተው ባዶነታቸውን በነጻ ሲያስኮሞኩሙን ኖረዋል፡
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መምህር እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ ጥርስ ውስጥ ከገቡት መካከል ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ገዢው የወያኔ ቡድን ጠንካራውን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በማፍረስ ተለጣፊ ማህበር ከማቋቋም አልፎ ታላላቅ የማህበራችንን አመራሮች ከአሰፋ ማሩ ጀምሮ በመግደል በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያዊው መምህር ሊነሱ የሚችሉ ተቃውሞችን ለማፈን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል በ2004 እንኳን የደመወዝ ጭማሪን ተከትሎ በተነሳው የመምህራን ጥያቄ መብታችን ይከበር ያሉ የማህበራችንን አባላት ከስራ ማባረር ጀምሮ ለእስር መዳረጉ የሚታወስ ሲሆን ይህም ሳያንስ በወቅቱ ከአንድ የሐገር መሪ ነኝ ከሚል ግለሠብ የማይጠበቅ ንግግር ከቀድሞው የሐገራችን አምባገነን ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በሐገራችን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስማታችን ይታወሳል ይህ በወያኔ አመራች ዘንድ ያለውን ከፍተኛ ንቀት እና ፍርሐት የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ውስጣዊ ፍርሀት የተነሳ በርካታ መስራት የሚችሉ እና ሀገሪቱን ሊቀይሩ ምሁራንን እንዲሰደዱ በማድረግ ያልተሰደዱትን ደግሞ በማሰር እና በማንገላታት የመምህርነትን ሙያን እንደማሰሪያ ብሎም አነስተኛ ደመወዝ በመክፈል የመምህራኑ አእምሮ በማጀት ወሬ እንዲጨናነቅ ማድረጉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡
ከሰሞኑም ይህንን ውስጣዊ ፍራቻውን ለካድሬዎቹ በመመሪያ መልክ በመስጠት በየት/ቤቱ የሚገኙ የገዢው ፓርቲ አባላት ያልሆኑ መምህራንን ስማቸውን ከተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በማያያዝ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ሲያቀርብባቸው ሰንብቷል በተለይ የግንቦት ሰባት እና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቹህ በማለት በየእለቱ ዛቻ የሚደርስባቸው መምህራን ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው በተለይ ከሰሞኑ የአባይ መዋጮ እንደአዲስ ለማስከፈል የሚደረገውን ጥረት ተከትሎ በተነሳው የመምህራን ጥያቄ በመምህራን ላይ የሚደርሰው መከራ እና ግፍ መጠኑ ጨምሯል፡፡
ስለሆነም የዚህ የኢትዮጵያ መምህራን ድምፅ ይሰማ ጊዜያዊ ኮሚቴ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ለትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩን ቢያሳውቅም እልባት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ የትምህርት ሚኒስቴሩም ለጉዳዩ እልባት ከመስጠት ይልቅ የአባዬን ወደእምዬ እንዲሉ በኮሚቴው አባላት ላይ ወቀሳ እና ማስፈራሪያ አቅርቧል ይኸውም ወትሮውም በትምህርት ሚኒስቴር ላይ አመኔታ ያልነበረውን ኮሚቴ ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ከሚታገሉ ሌሎች የሙያ ማህበራት እና ፓርቲዎች ጎን እንዲሠለፍ አድርጎታል በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ መምህራን ድምፅ ይሰማ ኮሚቴ አባላት በሰልፉ ላይ እንደምንገኝ ቃል እየገባን ሌላው የሀገራችን መምህርም ከጎናችን በመሆን በሠላማዊ ሠልፉ ላይ ይገኝ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ድምጽ ይሠማ ጊዜያዊ ኮሚቴ
ህዳር 21/2007
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ