Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, December 31, 2014

የባህር ዳር መስዋዕትነት የማይቀረዉ ድል ዋስትና ነዉ ginbot7

ወያኔ በየአመቱ ህዳር ወር መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያን ብሄር ብረሰቦች ሰብስቦ ዘፈን የሚያስዘፍንበትን በዐል ሲያከብር በተደጋጋሚ ከሚያሳማቸዉ መፈክሮች አንዱ የብሄር ብሄረሰቦች መብትና እኩልነት በህገመንግስታችን ተከበረ የሚል እጅግ በጣም አሳሳች የሆነ መፈክር ነዉ። በእርግጥም ወያኔ ለይስሙላ ወረቀት ላይ ያሰፈረዉ ህገ መንግስት መግቢያዉ ላይ “እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብህረሰቦች፤ ህዝቦች በነጻ ፍላጎታችን የህግ የበላይነትና በራሳችን ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል” ይላል። መቼም ይህ ምንም በማያሻማ መልኩ ቁልጭ ብሎ የተቀመጠ ህገ መንግስታዊ አንቀጽ ሌላ ትርጉም ካልሰጡት በቀር የአማራንም ህዝብ ያጠቃልላል የሚል ሙሉ እምነት አለን። በዚህ ደግሞ የአማራን ክልል የማስተዳድረዉ እኔ ነኝ ባዩ ባዕዴንም የሚስማማ ይመስለናል። በተግባር ሲታይ ግን ይህ የወያኔ ህገ መንግስት ላይ ህዝብና መንግስት የሚተዳደሩበት ህግ ቀርቶ ህገ አራዊት እንኳን አይመስልም። ምክንያቱም በህገ አራዊት አሰራር ተመሳሳይ ዝሪያ ያላቸዉና በአ ያላቸዉ የዱር አራዊት ይከባበራሉ እንጂ አንዱ ሌላዉን አያጠፋም። ለምሳሌ አንበሳና አንበሳ ይረዳዳሉ ወይም አብረዉ አደን ይወጣሉ እንጂ እርስ በርስ አይተላለቁም፤ ነብርና አንበሳም ቢሆኑ በተገናኙ ቁጥር ተከባብረዉ ይተላለፋሉ እንጂ አንደ ወያኔ ብጤያቸዉን ባዩ ቁጥር አያጠቁም ወይም አይገድሉም።
ወረቀት ላይ የሰፈረዉን የወያኔ ህገ መንግስት የተመለከተ ሰዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዜጎች መብታቸዉና ነጻነታቸዉ ተከብሮ የሚኖሩ ሊመስለዉ ይችላል። በእርግጥም ይመስላል። ምክንያቱም የወያኔ ህገ መንግስት ችግሩ አጻጻፉ ላይ ወይም ይዘቱ ላይ ሳይሆን በተግባር አተራጓጎሙ ላይ ነዉ። በ1987 ዓም የፀደቀዉ የወያኔ ህገ መንግስት በተግባር ሲታይ ብሄሮች፤ ብህረሰቦችና ህዝቦች የሚለዉ ቦታ ደብዛዉ ጠፍቶ ሁሉም ነገር ወያኔ ወይም ህወሓት በሚለዉ ቃል ተተክቷል፤ ወይም ሁሉም የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ተጨፍለቀዉ የትግራይ ልህቃን ወይም የህወሓት ሎሌዎችና ተላላኪዎች ሆነዋል። ለዚህ ነዉ አገራችን ኢትዮጵያ ወያኔ ያሰኘዉን የሚያዝባት የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ አንገቱን ደፍቶ የሚታዘዝባት አገር የሆነችዉ።
ሌላዉ ወያኔ ህገ መንግስቱ ዉስጥ አስፍሮ በየቀኑ እንደቤቱ ዉስጥ ምንጣፍ ከሚረግጣቸዉ ህገ መንግስታዊ አንቀጾች ዉስጥ አንዱ አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ አንድ ነዉ። ይህ አንቀጽ ማንኛዉም ሰዉ ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሠላም የመሰብሰብና ሠላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ ሙሉ መብት አለዉ ይላል። ሆኖም የዚህን አንቀጽ ሙሉ ቃል ከወያኔ የየቀኑ አረመኔነት ጋር ስናነጻጽር አንቀጹ የተጻፈበትን ወረቀት ያክል እንኳን ክብደት የለዉም። ይህንን ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ሠላማዊ ሠልፍ ባደረገባቸዉ ቦታዎች ሁሉ ወያኔ በተከታታይ በወሰዳቸዉ አረመኔያዊ እርምጃዎችና በፈጸማቸዉ ሰቆቃዎች ተመልክተናል። ለምሳሌ ባለፈዉ አመት አምቦ ዉስጥ አሁን ከሰሞኑ ደግሞ ባህርዳር ዉስጥ ህገ መንግስታዊ መብታቸዉን ተጠቅመዉ ጥያቀያቸዉን ሠላማዊ ሰልፍ በማድረግ ያቀረቡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ህፃናት፤ ወጣቶች፤ አዋቅዎች ወንዶችና ሴቶች በአግዓዚ ነብሰ ገዳዮች ጥይት ተጨፍጭፈዋል።
ወያኔ በተደጋጋሚ ሠላም … ሠላም እያለ በአፉ ይናገር አንጂ ወያኔን ከሰላም ጋር የሚያገናኘዉም ሆነ ወያኔ ስለ ሰለም የሚያዉቀዉ ምንም ነገር የለም። እዉነቱን ለመናገር ኢትዮጵያ ዉስጥ ሠላማዊ ሠልፈኞችን የሚገድል፤ ሠላለማዊ ዜጋን አስሮ የሚደበድብና የሠላም መንገዶችን ሁሉ ቅርቅር አድረጎ የዘጋዉ ወያኔ ብቻ ነዉ። ሌላዉ ቀርቶ ወያኔ የሚያስበዉ፤ የሚያቅደዉና ዕቅዱን ወደ ተግባር የሚለዉጠዉ ከህዝብ ፈቃድና ፍላጎት ዉጭ ስለሆነ ልማት ብሎ የሚጀምራቸዉ ፕሮጀክቶች እንኳን የህዝብን ሠላም የሚያናጉና የሠላማዊ ዜጎችን ህይወት የሚቀጥፉ ጅምሮች ናቸዉ። ከሰሞኑ ደግሞ ባህር ዳር ዉስጥ እየታየ ያለዉ ህዝባዊ ቁጣ የዚሁ ወያኔ ልማት እያለ የቀሰቀሰዉ ህዝባዊ እሳት ዉጤት ነዉ።
ወያኔ እራሱን ልማታዊ መንግስት እያለ እየጠራ በሚወስዳቸዉ እርምጃዎች ሁሉ ከህዝብ ጋር መጋጨት ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። ደቡብ ኦሞ ዉስጥ ሙርሲዎች በልማት ስም ከመሬታቸዉ ተፈናቅለዋል፤ አንፈናቅለም ብለዉ የተፋጠጡት ደግሞ በግፍ ተጨፍጭፈዋል። ታሪካዊዉ ዋልድባ ገዳም ዉስጥ ገዳም አለም በቃኝ ያሉ ሰዎች መኖሪያ አንጂ የእርሻ ቦታ አይደለም ብለዉ የተናገሩ መነኮሳት ቆባቸዉን አንደደፉ በቆመጥና በሰደፍ ተደብድበዋል። ጋምቤላና አፋር ዉስጥም በልማት ስም ከመሬታችን አታፈናቅሉን ብለዉ አቤቱታ ያቀረቡ ገበሬዎች ታስረዋል፤ ተግዘዋል ተገድለዋል። ለመሆኑ ወያኔ ልማት ብሎ አንድ ፕሮጀክት በጀመረ ቁጥር ህዝብን የሚያግዝና የሚገድል ከሆነ ልማቱ የሚታቀደዉ ለማነዉ? በልማቱስ ተጠቃሚ የሚሆነዉ ማነዉ?
በያዝነዉ ታህሳስ ወር መግቢያ ላይ ባህር ዳር ዉስጥ የአራት ሰላማዊ ዜጎችን ህይወት የቀጠፈዉና አለም በቃኝ ብለዉ ለፈጣሪያቸዉ ያደሩትን መነኩሴ ጨምሮ ለአያሌ ሠላማዊ ዜጎች መቁሰልና መታሰር ምክንያት የሆነዉ ይሄዉ ወያኔ በልማት ስም የጀመረዉና የአካባቢዉን ህዝብ ፍላጎት ያላካተተዉ የወያኔ ፀረ ህዝብና ፀረ አገር እርምጃ ነዉ። በእርግጥም አሁንም ድረስ ያልበረደዉ የባህር ዳሩ ህዝባዊ ተቃዉሞ የተቀሰቀሰዉ ወያኔ የባህር ዳርና የአካባቢዉ ህብረተሰብ የጥምቀት በዐል የሚያከብርበትንና የቤ/ክርስቲያን ንብረት የሆነዉን የቅዱስ ታቦት ማደሪያ ቦታ መንገድና ሱቅ እሰራለሁ ብሎ ማፈራረስ በመጀመሩ ነዉ።
ይህ በልማት ስም ሐይማኖታዊ የማመለኪያ ቦታን የማፈራረስና የቤ/ክርስቲያንን መሬት የመቀማት ሴራ የተዉጠነጠነዉ በወያኔ ቢሆንም የወያኔ ተላላኪ በመሆን ይህንን ከፍተኛ ወንጀል በገዛ ወገኖቹና ለጥቅሙ ቆሜያለሁ በሚለዉ ህብረተሰብ ላይ የሚያሰፈጸመዉ ግን ባዕዴን ነዉ። ባዕዴን ከዚህ ቀደምም በተከታታይ እንደታየዉ አማራዉ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በግፍ ሲባረርና ሲፈናቀል አፉን ዘግቶ የተመለከተና የአማራን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ለወያኔ አሳልፎ የሰጠ ከሃዲ ድርጅት ነዉ። ባዕዴን ነኝ ብሎ እንደሚናገረዉ በእርግጥም ለአማራ ህዝብ መብትና ነጻነት መከበር የቆመ ድርጅት ቢሆን ኖሮ የለየለት የአማራ ህዝብ ጠላት የሆነዉ ህወሓት አያገባዉ ገብቶ በአማራ ህዝብ ጉዳይ ላይ ሲፈተፍት ዝም ብሎ አይመለከትም ነበር።
ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክና አንድነት ብቻ ሳይሆን ባህሉን ፤ወጉንና ሐይማኖቱን ጭምር እንዳልነበረ ለማድረግ ያላደረጉት ነገር የለም። የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤ/ክኢርሰቲያን ጳጳስ አንስተዉ ቅዱስ መንበራቸዉን እጁ በደም ለተጨማለቀ ካድሬ በመስጠት ጥንታዊት ቤ/ክርስቲያናችንን ለሁለት አንድትከፈል አድርገዋል። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሏቸዉ ከሰሞኑ ባህርዳር ዉስጥ ህዝብ ጥምቀተ በዐል የሚያከብርበትንና የቅዱስ ታቦት ማደሪያ የሆነዉን ቦታ ከቤ/ክርስቲያን ቀምተዉ የንግድ ቦታ ለማድረግ ሞክረዋል። የእስልምና እምነት ተከታዮችን በተመለከተም ህጋዊዉን መጂሊስ አፍርሰዉ በእነሱ ፍላጎት ብቻ የሚመራ አሻንጉሊት መጂሊስ በማቋቋማቸዉ ከህዝበ ሙስሊሙ ጋር የፈጠሩት ግጭት ዛሬም ድረስ እንደተቀጣጠለ ነዉ።
የወያኔ ነብሰ ገዳዮች አዲስ አበባ፤ አምቦ፤ ደቡብ ኦሞ፤ ጋምቤላ፤ አፋርና አሁን በቅርቡ ደግሞ ባ/ህርዳር ዉስጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸሙት አረመኔያዊ ጭፍጨፋ እነዚህ ሰዎች ስራቸዉ አገር መምራት ነዉ ወይስ ህዝበን እያደኑ መግደል ነዉ የሚያሰኝ ነዉ። በእርግጥም ወያኔ እስከዛሬ የገደላቸዉን ሰዎችና ሰዎቹን የገደለበትን ምክንያት ስንመለከት የወያኔ የሙሉ ግዜ ስራ አገር መምራት ሳይሆን ህዝብን ምክንያት እየፈከገ መጨፍጨፍ መሆኑን ያረጋግጥልናል። በተለይ በቅርቡ ባህርዳር ዉስጥ አለም በቃኝ ብለዉ ገዳም የገቡትን መነኩሴ በጥይት መትተዉ ማቁሰላቸዉን ስንመለከት ወያኔዎች የገነቡትን ዘረኛ ስርዐት ዕድሜ ለማራዘም ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉ በግልጽ ያመለክታል።
አለማችን ዛሬም ብዙ ጨቋኝ መሪዎች የሚኖሩባት የአምባገነኖች መድረክ ናት፤ ሆኖም ህዝብ በተቃወማቸዉና በሠላማዊ ሠልፍ ቁጥዉን በገለጸ ቁጥር እንደ ወያኔ ያለ ምንም ማመንታት ሀዝብን በጥይት የሚጨፈጭፍ አረመኔያዊ አገዛዝ የለም። እዚህ ላይ አንድ ፍጹም ግራ የሚያጋባ ነገር አለ፤ እሱም ወያኔ ሠላማዊ ሰለፍኞችን በጥይት የሚጨፈጭፈዉ ሆን ብሎ ህዝብን የሚያስቆጡና የሚያነሳሱ ፀር ህዝብና ፀረ አገር እርምጃዎችን እየወሰደ ነዉ። ለምሳሌ ብዙዎቹን የወያኔ ጭፍጨፋዎች ትተን ሰሞኑን ባህርዳር ላይ የደረሰዉን እልቂት ብቻ ብንመለከት ህዝባዊ ቁጣዉ የተቀሰቀሰዉ ወያኔ ካልጠፋ ቦታ የቅዱስ ታቦት ማደሪያ የሆነዉን ቦታ አፍርሶ የሸቀጣ ሸቀጥ መሸጯ ቦታ ለማድረግ በመሞከሩ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሀይማኖቱ ሲነካ ወይም ሀይማኖታዊ ስርዐቱና ልምዱ ጣልቃ ሲገባባቸዉ እጅግ በጣም የሚቆጣና ተኝቶ የማያድር ህዝብ ነዉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ህዝብ ቤ/ክርስቲያኑ አላግባብ ከፈረሰበትና ጥምቀት፤ ገና፤ ፋሲካ፤ ቡሄ፤ ቅዱስ ዮሐንስና ደመራን የመሳሰሉ ሀይማኖታዊ ስርዐቶቹንና ልምዶቹን በለመደበት ግዜና ቦታ እንዳያከብር ከተከለከለ፤ በከልካዮቹ ላይ መነሳት ብቻ ሳይሆን እነሱን ከማጥፋት የማይመለስ ህዝብ ነዉ። ዛሬ አገር ቤትም ሆነ በዉጭ አገሮች የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ አይኖቹን ወደ ባህር ዳር ያዞረዉና እኛም ዉቧ የባህርዳር ከተማ የወያኔ መጨረሻ የተጀመረባት ከተማ ናት ብለን አፋችንን ሞልተን የምንናገረዉ ይህንን ስለምንረዳ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔን ግፍና መከራ ከ23 አመታት በላይ ተሸክሞ ኖሯል። በእነዚህ ሃያ ሦስት አመታት ዉስጥ ሠላማዊ ኢትዮጵያዉያን በየመንገዱና በየአደባባዩ እንደ ዱር እንስሳ እየታደኑ ተገድለዋል። አዲስ አበባ፤ አምቦ፤ አዋሳ፤ደቡብ ኦሞ፤ አፋር፤ ጋምቤላ፤ አርሲ ገደብ አሳሳና ኮፈሌ ዉስጥ አሁን ከሰሞኑ ደግሞ ባህር ዳር ዉስጥ የንጹህ ኢትዮጵያዉያን ደም በግፍ እንደ ጎርፍ ሲፈስ ተመለክተናል። ወያኔንና ዘረኛ ስርዐቱን አስወግደን ኢትዮጵያን የህዝቦቿ አገር ካላደርግናት በቀር ወያኔ ስራዉ መግደል ነዉና እሱ እየገደለ እኛም የእያንዳንዳችን ተራ እስኪደርስ ድረስ ወያኔ የገደለዉን እየቀበርን መኖራችን የማይቀር ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! ያለህ አማራጭ አንድ ብቻ ነዉ፤ እሱም ሁሌ እየሞትክና እየቀበርክ ከምትኖር ከወያኔ ጋር ፉት ለፊት ተጋፍጠህ እንዳባቶችህ የክብር ሞት ሙትና ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህ ህይወት ሁንላቸዉ። አንተ በአንድነት ተነስተህ ፊትህን ወደ ወያኔ ካዞርክ ወያኔ እንደ ጉም በንኖ የሚጠፋ ገለባ ነዉ። ወያኔ እየረገጠ የሚገዛህና የሚገድልህ አንተኑ እንደ ሀይል በመጠቀም ነዉና ለወያኔ አልገዛም በል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ በያዝነዉ የሞትና የሽረት አመት ወያኔን ለማስወገድ ከዉጭም ከዉስጥም በሚደረገዉ ትግል ዉስጥ ድርሻህን ተወጣ። ድል ምንግዜም ያንተ ነዉና . . . . አይዞህ፤ በርታ ዝመት!

No comments:

Post a Comment

wanted officials