Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, December 31, 2014

ሰበር ዜና – የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ተጠያቂው ሊቅና ኹለገቡ ባለሞያ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዐረፉ


‹‹ከአንድ ሊቅ በሚጠበቅ መልኩ በተጠያቂነት ደረጃ ሙሉ አገልግሎት በመስጠት መላ ዘመናቸውን አሳልፈዋል›› – የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዜና ሕይወት እና ዕረፍት
ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንና አገራችን ኢትዮጵያን በክህነት፣ በሊቅነት፣ በመምህርነት፣ በአስተዳደር እና በጸሐፊነት ሞያቸው በብቃትና በትጋት ሲያገለግሉ የኖሩት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዐረፉ፡፡
የሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ሞተ ዕረፍት የተሰማው÷ ዛሬ፣ እሑድ ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ ቀበና መካነ ሕይወት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ከሚገኘው መኖርያ ቤታቸው ነው፡፡
በመኖርያ ቤታቸው÷ በቤተ ሰዎቻቸውና በወዳጆቻቸው መካከል ያረፉት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል፣ ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ በበርካታ ዘርፎችና በተለያዩ የሓላፊነት ደረጃዎች ሲሠሩ ከኖሩበት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ከነበረባቸው ከፍተኛ የደም ግፊትና የነርቭ ሕመም ጋራ በተያያዘ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በጡረታ የተገለሉ ቢኾንም በመምሪያ ደረጃ የሊቃውንት ጉባኤ አባልነታቸው አገልግሎታቸውን ቀጥለው ቆይተዋል፡፡
ከዘመናችን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መካከል ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል በልዩነት የሚታወቁትና የሚታወሱት÷ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን (Liturgical Theology) ራሱን ችሎ የቆመ የትምህርት ዘርፍ (discipline) ኾኖ ጎልቶ እንዲወጣና በሥርዐተ ትምህርትም መርሐ ትምህርት ተቀርፆለት እንዲታወቅ÷ በምሁራን አነጋገር የራሱ ጉባኤ እና ወንበር እንዲኖረው÷ ባደረጉበት ጥረታቸውና ድካማቸው ነው፡፡
(ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. – ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)
ከትምህርት ቤትና ከመጻሕፍት ያገኙት ዕውቀት አራት ዓይና ያደረጋቸው ሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ በተጠያቂነት ደረጃ የሚገኙና አገልግሎታቸውም ሙሉ ነበር፡- ቀዳሽና መዘምር፤ ጋዜጠኛና ሰባኬ ወንጌል፤ ጸሐፊና ተርጓሚ፤ አስተዳዳሪና መምህር፤ የአውራጃ አብያተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፤ ኤርትራን ጨምሮ የአህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስምንት መምሪያዎች ምክትልና ዋና ሓላፊ፡፡
ሊቁ በሓላፊነት በተመደቡባቸው ቦታዎች ኹሉ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት÷ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተማር፤ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፤ ሰበካ ጉባኤያትንና ሰንበት ት/ቤቶችን ለማቋቋም፣ ለማደራጀትና ለማጠናከር፤ አገልጋዮች ካህናትን በትምህርትና ሥልጠና በማብቃት አስተዳደርን ለማሻሻልና ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያንን የውስጥ ድርጅት በንዋያተ ቅድሳትና በጽ/ቤት መገልገያዎች ለማሟላት እንደነበር ዜና ሕይወታቸው በስፋት አትቷል፡፡
የአብነት ት/ቤቶችን፣ የካህናት ማሠልጠኛዎችንና ኮሌጆችን በበላይነት በሚያስተባብረው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ለሦስት ጊዜያት በዋና ሓላፊነት ተመድበው የላቁ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ከእኒኽም በመንግሥት የተወረሱ 27 መንፈሳውያንና ዘመናውያን ት/ቤቶችን በተለይም የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲመለስ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሐሳብ በማቅረብና በቅ/ሲኖዶስ ከተወሰነም በኋላ የበኩላቸውን ክትትል በማድረግ መንፈሳዊ ኮሌጁ ለቤተ ክርስቲያናችን ተመልሷል፡፡
በመምሪያ ደረጃ የሊቃውንት ጉባኤ አባል ኾነው ከተመደቡበት ጥቅምት ወር ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው መዳረሻ ከሌሎች ሊቃውንት ጋራ በመኾን ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል÷ ቤተ ክርስቲያናችን የራስዋ የተጣራ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኖራት 81 ቅዱሳት መጻሕፍትን በግእዝ ቋንቋ መሠረትነት አርመውና አስተካክለው ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ ለካህናትና ምእመናን በሴሚናር ሲያሰለጥኑበት የቆዩት የቃለ ዐዋዲ ደንብ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሻሻል የበኩላቸውን ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት›› መጽሐፍ ከሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጋራ በአንድነት አዘጋጅተው ለምእመናን እንዲዳረስ አድርገዋል፡፡ በርካታ የቅዱሳን ገድላትና የመላእክት ድርሳናት ከግእዝ ወደ አማርኛ ቋንቋ መልሰዋል፡፡
የቤተ ክህነት ሥነ ጽሕፈት ኮሚቴ አባል በመኾን በዐበይት የቤተ ክርስቲያን በዓላት በሚወጡ ኅትመቶችና በሚሠራጩ የሬዲዮ መግለጫዎች በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎችና በምርምር የተደገፉ፤ አንባቢንና አድማጭን የሚያረኩ በርካታ ጽሑፎችን በማቅረብ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ ታላቅ ምሁር ነበሩ፡፡ በግል አዘጋጅተው ካሳተሟቸው መጻሕፍት መካከል ‹‹ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን››፤ ‹‹ሳታዩት የምትወዱት›› በሚል ለትምህርትና ለተግሣጽ ባሰራጯቸው ሥራዎቻቸው ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ለነገረ ሃይማኖት መጠበቅ ተከራክረዋል፤ ተሟግተዋል፡፡ በተለይም ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን በኮሌጅ ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ ራሱን ችሎ የቆመ የትምህርት ክፍል ኾኖ እንዲሰጥ ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ አድርገዋል፤ መጽሐፉም በኮሌጆችና በካህናት ማሠልጠኛዎች ለመምህራንና ለተማሪዎች መመሪያና ማጣቀሻ ኾኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አገልግሎት ዓለም አቀፋዊም ነበር፡፡ ከግንቦት ፲፬ – ፴ ቀን ፲፱፻፸፯ ዓ.ም. የያሬዳዊ ማሕሌትን ዐውደ ትርኢት በምዕራብ ጀርመን ለማሳየት ከተመረጡት ሊቃውንት አንዱ በመኾን የማሕሌታችንን ሥርዐት አሳይተው ተመልሰዋል፡፡ እ.አ.አ ከሐምሌ ፱ – ፲፭ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. ‹‹ክርስቶስን ዛሬ መስበክ›› በሚል ርእስ በእስክንድርያ በተደረገው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ የቤተ ክርስቲያናችን መልእክተኛ በመኾን ጥንታዊ እምነቷንና ሥርዐቷን በቃልም በጽሑፍም በመግለጥ ተሳትፈዋል፡፡ በየመንና በጅቡቲ ለሚኖሩ ምእመናን ለበርካታ ጊዜ እየተመላለሱ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡፡
* * *
ከደግ ቤተሰብ ተገኝተው በመልካም አስተዳደግ የወጡት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ በትዳራቸውም የጋብቻ ጽናት ምሳሌነታቸውን በተግባር ያረጋገጡ ናቸው፡፡ ጥር ፲፪ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. በተክሊልና በሥርዐተ ቁርባን ካገቧቸው የሕግ ባለቤታቸው ወ/ሮ ድጋፍ ወርቅ ፈቄ ጋራ የ፶ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ የጋብቻ በዓላቸውን ከኹለት ዓመት በፊት አክብረው ነበር፡፡ ስምንት ልጆችንና ዐሥር የልጅ ልጆችን አፍርተውም ለወግ ለማዕርግ አብቅተዋል፡፡
ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል በሢመተ ክህነት÷ በ፲፱፻፵፩ ዓ.ም. ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማዕርገ ዲቁና፤ ሰኔ ፲፩ ቀን ፲፱፻፶፱ ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ሢመተ ቅስና ተቀብለዋል፡፡ የትምህርት ዝግጅታቸው በዜማ፣ በአቋቋም፣ በቅኔና በነገረ ሃይማኖት ላይ ያተኮረ ኾኖ ትርጓሜ መጻሕፍትንና የቤተ ክርስቲያን ታሪክን ከተለያዩ ሊቃውንት በመማር ምስጢር አደላድለዋል፡፡ በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም. ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በከፍተኛ የነገረ መለኰት ትምህርት የቴዎሎጂ ዲፕሎማ ተቀብለዋል፡፡ በቅድስት ሥላሴ ት/ቤት እና በዳግማዊ ምኒልክ የአንደኛና የኹለተኛ ደረጃ ት/ቤት ትምህርታቸውን ተምረው አጠናቀዋል፡፡
* * *
‹‹በዕለተ ሰንበትና በዐበይት በዓላት እየቀደሱና እያወደሱ፣ በሥራ ቀናት በቢሮ እየሠሩ፣ ለምእመናን ወንጌል እየሰበኩ፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆችና በካህናት ማሠልጠኛዎች እያስተማሩና እያሠለጠኑ ከአንድ ሊቅ በሚጠበቅ መልኩ በተጠያቂነት ደረጃ በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ ሙሉ አገልግሎት ሲያበረክቱ ኑረዋል፡፡

    ዕረፍቱ ለሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ (ሚያዝያ 19 ቀን 1929 – ታኅሣሥ 19 ቀን 2007 ዓ.ም.)
በቀድሞው የሸዋ ክፍለ ሀገር በይፋት አውራጃ በማፉድ ወረዳ በደብረ ምሥራቅ ሾተል ዓምባ በኣታ ለማርያም አጥቢያ ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ ስማቸው ክንፈ ገብርኤል፤ ያረፉትም የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዋናው በዓል በሚከበርበት በታኅሣሥ ገብርኤል፤ ኹሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ለነፍሳቸው ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ያድልልን፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን ይስጥልን፤ በእርሳቸው እግር ምሁራንን እንዲተካልን ፈጣሪን በጸሎት እንለምነዋለን፡፡››
ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ
፩. ልደትና ልህቀት
ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ሚያዝያ 19 ቀን 1929 ዓ.ም. ከአባታቸው ከአቶ አልታዬ ናደውና ከእናታቸው ከወ/ሮ በለጥሻቸው እርዳቸው በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሀገር በይፋት አውራጃ በማፉድ ወረዳ በደብረ ምሥራቅ ሾተል ዓምባ በኣታ ለማርያም አጥቢያ ተወለዱ፡፡ የሕፃንነት ጊዜአቸውን በቤተሰቦቻቸው በመልካም አስተዳደግ ካሳለፉና የሕፃንነት ደረጃ ካለፉ በኋላ እንደ አገሩ ልማድ ቤተሰቦቻቸውን በመርዳት ለአባትና እናታቸው እየታዘዙና እያገለገሉ አደጉ፡፡
፪. ትምህርትና መዋዕለ ውርዝውና
ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዕድሜአቸው ለትምህርት እንደ ደረሰ ለመንፈሳዊ ትምህርት ባላቸው ዝንባሌ በትውልድ ሀገራቸው በደብረ ምሥራቅ ሾተል ዓምባ በኣታ ለማርያም፡- ከመምሬ መሸሻ ካሳዬ ፊደል፣ ንባብና ጽሕፈት፤ ከአለቃ ተሰማ ወልደ ጊዮርጊስ ዜማና አቋቋም በሚገባ ተምረው አጠናቀዋል፡፡
ከዚኽ በኋላ በ1948 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥተው በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም መንፈሳዊ ት/ቤት ገብተው፡- ከሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃን ወልደ ኪሮስ የአማርኛ ሰዋስው፤ ከመጋቤ ምስጢር ጌራ ወርቅ ጥበቡና ከመልአከ አርያም ይትባረክ መርሻ ቅኔና የግእዝ ቋንቋ ከነአገባቡ በሚገባ ተምረውና አደላድለው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡ በተጨማሪም በዚኹ ት/ቤት ከቀኝ ጌታ ሞገስ ሥዩምና ከሊቀ ጠበብት ሐረገ ወይን ደምሴ የአቋቋም ትምህርታቸውን አስፋፍተው ተምረዋል፡፡
ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ለትምህርት የነበራቸው ፍላጎት ከፍተኛ የነበረ በመኾኑ በተማሯቸው ልዩ ልዩ ትምህርቶች ሳይወሰኑ፡- ከአለቃ አዘዘ መጻሕፍተ ብሉያት፤ ከመ/ር ሙሉጌታ መጻሕፍተ ሐዲሳት፤ ከመልአከ ሰላም ሳሙኤል ተረፈና ከሊቀ ሥልጣናት ኤልያስ (በኋላ ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ) ነገረ ሃይማኖት(ዶግማ)፤ ከመ/ር ወንድም አገኘኹ እና ከአለቃ ይኩኖ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ከዶክተር አበበ እና ከረዳት ፕሮፌሰር ሉሌ መልአኩ እንዲኹም ከአለቃ ወልደ ኢየሱስ የዓለም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሚገባ ተምረዋል፡፡
በ1951 ዓ.ም. በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብተው በኮሌጁ የሚሰጠውን ከፍተኛ የነገረ መለኰት ትምህርት ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ተምረው በ1953 ዓ.ም. ከግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ እጅ የቴዎሎጂ ዲፕሎማ ተቀብለው የግእዝ የአማርኛ ቋንቋና የነገረ ሃይማኖት መምህር ኾነው ተመርቀዋል፡፡
የዘመናዊ ትምህርትን በሚመለከትም በዚኹ በቅድስት ሥላሴ ት/ቤትና በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት የአንደኛና የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረው አጠናቀዋል፡፡
ሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ በጉባኤ ያልሰሟቸውና በግል ያላነበቧቸው መጻሕፍት የሉም ብንል ማጋነን አይኾንም፡፡ በዚኽም መሠረት ከትምህርት ቤትና ከመጻሕፍት ያገኙት ዕውቀት ሙሉዕ በኩለሄ፣ አራት ዓይና ስለአደረጋቸው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በተጠያቂነት ደረጃ ሙሉ አገልግሎት በመስጠት መላ ዘመናቸውን እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል፡፡
፫. ሢመተ ክህነትና አገልግሎት
በ1941 ዓ.ም. ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የዲቁና ማዕርግ ተቀብለው የተወለዱባትን የሾተል ዓምባ በኣታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን፤ የተማሩባትን የታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም በቅዳሴ፣ በመዘምርነትና በስብከተ ወንጌል ዘርፍ አገልግለዋል፡፡
በ1954 ዓ.ም. የመንዝና ይፋት አውራጃ ቤተ ክህነት ሰባኬ ወንጌል ኾነው እየተዘዋወሩ በማስተማር ሐዋርያዊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ በዚኹ ጊዜም በደብረ ሲና መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት አቋቁመዋል፡፡
በዚያው በ1954 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሬዲዮ ትምህርት እንድትሰጥ መንግሥት ሲፈቅድ፣ ቀደም ሲል ተመርቀው ለወንጌል አገልግሎት ከተሰማሩት ሊቃውንት መካከል ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ አንዱ በመኾን ተመርጠው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የታሪክና ድርሰት ክፍል ባልደረባ ኾነው ለዐሥር ዓመታት ያኽል የወንጌልን ቃል በምሥራች ሬዲዮ፣ በጋዜጣና በመጽሔት በማሰራጨት ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገርና ለወገን ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡
በ1956 ዓ.ም. በሬዲዮ ሲተላለፍ የነበረው ያሬዳዊ ዜማና መዝሙር ሓላፊ፤ በ1958 ዓ.ም. የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ፤ በ1960 ዓ.ም. የጠይቆ መረዳት መርሐ ግብር አዘጋጅ፤ በ1961 ዓ.ም. የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ የድርሰትና ሥነ ጽሑፍ ክፍል ሓላፊ በመኾን መንፈሳዊ አገልግሎት በስፋትና በብቃት ሰጥተዋል፡፡ የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበሩበት ጊዜም የጋዜጣውን ሥነ ጽሕፈትና ቴክኒክ በማሻሻል ዘመናዊ ውበት እንዲኖረው፣ የጋዜጣ መልእክና ቅርፅ እንዲይዝ በማድረጋቸው የጋዜጣው 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል በተከበረበት በ1962 ዓ.ም. በወቅቱ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ከነበሩት ከክቡር ንቡረ እድ ድሜጥሮስ እጅ ሽልማትና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቶአቸዋል፡፡
ሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ለቤተ ክርስቲያን የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ፍጹም ሐሳብና ዕቅድ ስለነበራቸው ሰኔ 11 ቀን 1959 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ሊቀ ጳጳስ ሢመተ ቅስና ተቀብለው በዕለተ ሰንበትና በዐበይት በዓላት እየቀደሱና እያወደሱ፣ በሥራ ቀናት በቢሮ እየሠሩ፣ ለምእመናን ወንጌል እየሰበኩ፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆችና በካህናት ማሠልጠኛዎች እያስተማሩና እያሠለጠኑ ከአንድ ሊቅ በሚጠበቅ መልኩ የድርሻቸውን ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ በአዲስ አበባና በመላ ኢትዮጵያ እየተዛወሩ ሲያበረክቱ ኑረዋል፡፡
በ1966 ዓ.ም. በሸዋ ሀገረ ስብከት የየረርና ከረዩ አውራጃ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ በመኾን ተሹመው በነበረበት ወቅት የናዝሬት ካህናት ማሠልጠኛን በራስ አገዝ መርሐ ግብር ከፍተው ካህናትን በማሠልጠን ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በማስተማር ተዳክሞ የነበረውን ሰበካ ጉባኤ እንደገና በማቋቋምና በማጠናከር በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሰንበት ት/ቤቶችን በማቋቋም በፈጸሙት ሐዋርያዊ ተግባር የአውራጃው ካህናትና ምእመናን ምን ጊዜም ሲያስታውሷቸው ይኖራሉ፡፡
በ1967 ዓ.ም. የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ጸሐፊ ኾነው እንዲሠሩ ተመድበው የነበሩ ሲኾን ከዚኹ ሓላፊነታቸው በተጨማሪ የቀበና መካነ ሕይወት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ኾነው እንዲሠሩ በታኅሣሥ ወር 1967 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ተሹመዋል፡፡ በዚኹ ሓላፊነታቸው የሰበካውን ምእመናን በማስተባበር ፈርሶ የነበረውን ሰበካ ጉባኤ በማቋቋምና በማደራጀት፣ የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳደር በማሻሻል በነፃ ያገለግሉ ለነበሩት የደብሩ ካህናት በጀት በማስፈቀድ የወር ደመወዝተኞች እንዲኾኑ አድርገዋል፤ የቤተ ክርስቲያኑን የውስጥ ድርጅት፣ የጎደሉ ንዋያተ ቅድሳትን፣ አልባሳትንና መጻሕፍትን በማሟላት እንዲኹም ጽ/ቤቱን በማቋቋምና በማደራጀት ለቤተ ክርስቲያን የዕድገት መሠረት ጥለዋል፡፡
ይህንኑ የአስተዳደር ሓላፊነት እንደያዙ በጥር ወር 1968 ዓ.ም. የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ (መጋቤ ካህናት) ተብለው ተሹመው አገልግለዋል፡፡
በጥቅምት ወር 1969 ዓ.ም. የኤርትራ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በሰኔ ወር 1969 ዓ.ም. የካፋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው በመሾም በየአብያተ ክርስቲያናቱ ተዳክሞ የነበረውን ሰበካ ጉባኤ በማቋቋምና በማደራጀት አስተዳደሩን በማሻሻል ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በማስተማርና በተለይም ሥርዐተ ቅዳሴው በልዩ ሥርዐት እንዲመራ በማድረግ ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡
በ1971 ዓ.ም. የጠቅላይ ቤተ ክህነት ትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ምክትል ሓላፊ፤ በ1972 ዓ.ም. ሊቀ ካህናት ተብለው በመሾም የአዲስ አበባ ደቡብ አውራጃ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ኾነው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ተሹመው ቃለ ዐዋዲውን ለካህናትና ምእመናን በሴሚናር በማስጠናትና የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር በማስተማር ሰበካ ጉባኤን በሚገባ አደራጅተው ለአኹኑ ውጤት ያበቁ የቤተ ክርስቲያናችን ባለውለታ አባት ነበሩ፡፡
በ1976 ዓ.ም. የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር መምሪያ ምክትል ሓላፊ፤ በ1978 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የገንዘብና ንብረት አስተዳደር መምሪያ ምክትል ሓላፊ፤ በ1979 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የቁጥጥር አገልግሎት ተ/መምሪያ ሓላፊ፤ በ1980 ዓ.ም. የበጀትና ንብረት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ፤ በ1983 ዓ.ም. የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊ፤ በ1987 ዓ.ም. የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምክትል ዲን በመኾን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡
ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል፣ ሐምሌ 1983 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ሓላፊ ኾነው በተመደቡበት ወቅት በደርግ መንግሥት የተወረሱና የቤተ ክርስቲያን ንብረት የኾኑ 27 መንፈሳውያንና ዘመናውያን ት/ቤቶች ለቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ አድርገዋል፤ እንዲኹም የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲመለስ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስና ለቅዱስ ሲኖዶስ ሐሳብ በማቅረብና በመከታተል ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖ ጥያቄው ለመንግሥት እንዲቀርብ የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል፤ መንፈሳዊ ኮሌጁም በቅዱስነታቸው ያላሰለሰ ክትትል ለቤተ ክርስቲያናችን ተመልሷል፡፡
የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አገልግሎት ዓለም አቀፋዊም ነበር፡፡ ከግንቦት ፲፬ – ፴ ቀን ፲፱፻፸፯ ዓ.ም. የያሬዳዊ ማሕሌትን ዐውደ ትርኢት በምዕራብ ጀርመን ለማሳየት ከተመረጡት ሊቃውንት አንዱ በመኾን የማሕሌታችንን ሥርዐት አሳይተው ተመልሰዋል፡፡ እ.አ.አ ከሐምሌ ፱ – ፲፭ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. ‹‹ክርስቶስን ዛሬ መስበክ›› በሚል ርእስ በእስክንድርያ በተደረገው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ የቤተ ክርስቲያናችን መልእክተኛ በመኾን ጥንታዊ እምነቷንና ሥርዐቷን በቃልም በጽሑፍም በመግለጥ ተሳትፈዋል፡፡ በየመንና በጅቡቲ ለሚኖሩ ምእመናን ለበርካታ ጊዜ እየተመላለሱ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡
በነሐሴ 1987 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ መልካም ፈቃድ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች÷ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንና ነገረ መለኰት አስተምረዋል፤ ሰብከዋል፡፡ በዚኽም አገልግሎታቸው ፑና ከሚገኘው የቅዱስ ቶማስ ቤተ ክርስቲያን ስጦታና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በጥቅምት 1988 ዓ.ም. የሊቃውንት ጉባኤ አባል ኾነው በመመደብ ከሌሎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጋራ በመኾን የቃለ ዐዋዲ ደንብ አሻሽለዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት›› በሚል ርእስ መጽሐፍ አዘጋጅተው ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ ‹‹በዐድዋ ጦርነትና ድል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድርሻ›› በሚል ርእስ ለዐድዋ ድል ፻ኛ ዓመት መታሰቢያ መጽሐፍ አዘጋጅተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራስዋ የተጣራ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኖራት ከሌሎች የሊቃውንት ጉባኤ ባልደረቦቻቸው ጋር በጋራ በመኾን 81 ቅዱሳት መጻሕፍትን በግእዝ ቋንቋ መሠረትነት አርመውና አስተካክለው ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ሥርዐተ አምልኮ›› የተሰኘውን መጽሐፍ ከሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጋራ በአንድነት በማዘጋጀት ለምእመናን እንዲዳረስ አድርገዋል፡፡
የቤተ ክህነት ሥነ ጽሕፈት ኮሚቴ አባል በመኾን በዐበይት የቤተ ክርስቲያን በዓላት በሚወጡ ኅትመቶችና በሚሠራጩ የሬዲዮ መግለጫዎች በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎችና በምርምር የተደገፉ፤ አንባቢንና አድማጭን የሚያረኩ በርካታ ጽሑፎችን በማቅረብ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ ታላቅ ምሁር ነበሩ፡፡
ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል በግል አዘጋጅተው ካሳተሟቸው መጻሕፍት መካከል ‹‹ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን››፤ ‹‹ሳታዩት የምትወዱት›› የተሰኙና በዚኽ ጽሑፍ ያልተጠቀሱ ለትምህርትና ተግሣጽ በሚጠቅሙ እጅግ በርካታ ሥራዎቻቸው ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ለነገረ ሃይማኖት መጠበቅ ተከራክረዋል፤ ተሟግተዋል፡፡ በተለይም ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን በኮሌጅ ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ ራሱን ችሎ የቆመ የትምህርት ክፍል ኾኖ እንዲሰጥ ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ አድርገዋል፤ መጽሐፋቸውም በኮሌጆችና በካህናት ማሠልጠኛዎች ለመምህራንና ለተማሪዎች መመሪያና ማጣቀሻ ኾኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፈ ሲኖዶስ፣ በፍትሐ ነገሥት በሌሎችም የሥርዓት መጻሕፍት በሰፊው ተወስኖ ተጽፎዋል፡፡ ይኹን እንጂ ምእመናን ጥልቅና ምጡቅ የኾነውን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በመጠኑም ቢኾን ለመማርና ለማስተማር፣ ለማወቅና ሥርዓቱን ለመፈጸም እንዲችሉ በማሰብ ይህ ‹‹ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን›› መጽሐፍ በአስተዋፅኦ መልክ (በማውጣጣት) ተዘጋጅቷል፡፡
መጽሐፉ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና ምስጢር በቅድሚያ አመሠራረቱን መነሻውን፣ ከዚያም አመጣጡንና ታሪኩን፣ አሠራሩንና አፈጻጸሙን ይገልጣል፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር መጽሐፉ የገለጠው ሰባቱ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እንዲኹም ሥርዐተ ቤተ መቅደስ እና ሥርዐተ ጸሎት ኹሉ በመጻሕፍተ ብሉያት፣ በመጻሕፍተ ሐዲሳት፣ በመጽሐፈ ሲኖዶስ እና በፍትሐ ነገሥት የተሠራውንና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተወሰነውን እንጂ ከዚያ ምንጭነት የማያልፍ የማይወጣ ስለኾነ ‹‹ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ /ከመጽሐፉ መግቢያ የተወሰደ/
በትርጉም ደረጃ በርካታ የቅዱሳን ገድላትና የመላእክት ድርሳናት ከግእዝ ወደ አማርኛ ቋንቋ መልሰዋል፡፡ በተጨማሪም በግራ ጌታ ኃይለ ጊዮርጊስ በግእዝ የተዘጋጀ የልዑል ራስ መኰንን እና የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዜና መዋዕል በልዕልት ተናኘ ወርቅ አሳሳቢነት ከግእዝ ወደ አማርኛ ቋንቋ መልሰዋል፡፡
ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ የሕግ ባለቤታቸው የኾኑትን ወ/ሮ ድጋፍ ወርቅ ፈቄን በተክሊልና በሥርዐተ ቁርባን ጥር 12 ቀን 1955 ዓ.ም. አግብተው አራት ወንዶችና አራት ሴቶች ልጆች እንዲኹም 10 የልጅ ልጆችን አፍርተውና አስተምረው ለማዕርግ አብቅተዋል፡፡ የ50ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ የጋብቻ በዓላቸውን ከኹለት ዓመታት በፊት አክብረው የጋብቻ ጽናት ምሳሌነታቸውን በተግባር አረጋግጠዋል፡፡
ዜና ዕረፍት
    ከጥቂት ዓመታት ወዲኽ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ78 ዓመታቸው ከሚወዱት ቤተሰባቸውና የመንፈስ ልጆቻቸው ተለይተው ታኅሣሥ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከዚኽ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡
    ሥርዓተ ቀብራቸውም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ልጆቻቸውና ዘመዶቻቸው በተገኙበት ታኅሣሥ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር ተፈጽሟል፡፡
    ኹሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ለነፍሳቸው ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን እንዲያድልልንና ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጥልን በእርሳቸውም እግር ምሁር እንዲተካልን ፈጣሪን በጸሎት እንለምነዋለን፡፡
    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment

wanted officials