ህዳር 27 እና 28/2007 ዓ.ም በ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ተዘጋጅቶ ለነበረው የአዳር ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ የቅስቀሳ በራሪ ወረቅት ሲበትን ለእስር የተዳረገው የሰማያዊ ፓርቲ አባል በፌደራል አቃቤ ህግ ለቀረበበት ክስ ያቀረበው መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ተደረገ፡፡
ዛሬ ታህሳስ 14/2007 ዓ.ም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው አቶ ሲሳይ ዘርፉ ‹‹…‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ› ለመላው ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ….ተብሎ የተጻፈበት በራሪ ወረቀቶች ለህብረተሰቡ ሲያከፋፍል እጅ ከፈንጅ በመያዙ በፈጸመው የሐሰት ወሬን በማውራት ህዝቡን ማነሳሳት ወንጀል…›› በፌደራል አቃቤ ህግ መከሰሱ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን ክስ ለመቃወም ያቀረበው የጽሑፍ መቃወሚያ በፍርድ ቤቱ ውድቅ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህም አቃቤ ህግ በተከሳሽ ላይ ምስክሮቹን አቅርቦ ለታህሳስ 23 ቀን 2007 ዓ.ም እንዲያሰማ ተፈቅዶለታል፡፡
ተከሳሹ አቶ ሲሳይ ዘርፉ ለቀረበበት ክስ በጽሑፍ መከላከያው ላይ፣ ‹‹…መረጃ ማሰራጨት ህገ-መንግስታዊ መብቴ ነው፤ ያሰራጨሁት መረጃም የሐሰት ወሬ ሳይሆን በህግ ተመዝግበው ሰላማዊ ትግል እያደረጉ ያሉ ፓርቲዎች ያዘጋጁትን መረጃ ነው…›› በማለት አስፍሮ በነጻ እንዲያሰናብተው ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ ‹‹የመንግስትን ስም ማጥፋት በወንጀል ያስጠይቃል…›› በሚል ከአቃቤ ህግ የቀረበለትን ሀሳብ ተቀብሎ ተከሳሹ አቶ ሲሳይ ላይ ምስክሮች እንዲሰሙበት በይኗል፡፡
አቶ ሲሳይ ዘርፉ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለበት ዕለት ጀምሮ ዋስትናው ተነፍጎ ቀደም ብሎ በፖሊስ ጣቢያና አሁን ደግሞ ቂሊንጦ እስር ቤት በእስር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሰማያዊ ፓርቲ በአቶ ሲሳይ ዘርፉ የዋስትና ጉዳይ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውቋል፡፡