Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, December 6, 2014

ቴዲ አፍሮን ቦሌ ላይ ለምን አገቱት? – ክንፉ አሰፋ (ጋዜጠኛ) ከ ዘአበሻ የተወሰደ


ክንፉ አሰፋ
ወደ አውሮፓ የሚያስገባውን ቪዛ እና ትኬት ይዞ ከወዳጆቹ ጋር ጉዞውን ለመጀመር ወደ ቦሌ አለም-ዓቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ አቀና። እዚያው እንደደረሰ የተለመደው የፓስፖርትና ትኬት ቁጥጥር ተደረገ። ሁሉም የተሟላ ነበር። ቴዲ ሸኚዎቹን ተሰናብቶ ወደ ውስጥ ገባ። እለተ ሐሙስ፣ ህዳር 28 ቀን 2007 ዓ.ም.።
የአውሮፓው ኮንሰርት በፊንላንድ፣ ሄልሲንኪ ቅዳሜ፤ ህዳር 28 ቀን ይጀምራል። ፊንላንድና አካባቢው ያሉ የቴዲ አድናቂዎች ትኬት ቆርጠው አርቲስቱን በጉጉት እየተጠባበቁት ነው። የቴዲ አፍሮ ማናጀርም አቡጊዳ ባንድን ይዞ ሄልሲንኪ ላይ ለቅዳሜው ስራ በልምምድ ላይ ይገኛል።
ቴዲን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተሰናብተው የተመለሱ ወዳጆቹ አውሮፓ ደውለው አርቲስቱን ሄልሲንኪ ላይ እንዲቀበሉት ተናግረው ነበር። ነገሩ እነሱ እንዳሰቡት ግን አልነበረም። ዘግየት ብሎ ሌላ ነገር መጣ። ሰዎቹ ቦሌ ላይ አገቱት። በውድቅት ሌሊት ፓስፖርቱን ነጥቀው ወደ ቤቱ አሰናበቱትም። ይህንን ያደረጉበትን ምክንያትም አልነገሩትም። አስቀድመው ገና ከበሩ ላይ መከልከል ይችሉ ነበር።… ግን ማንገላታት ነበረባቸው። ስሜቱን ለመጉዳት መሞከር ነበረባቸው። ጉልበት እንዳላቸው ማሳየት ነበረባቸው። ፈላጭ፤ ቆራጭ መሆናቸውን ማሳወቅ ነበረባቸው። ቂመኞችና ተበቃዮችም መሆናቸውን መናገር ነበረባቸው። ….
ነገሩ ያልተጠበቀ ባይሆንም፤ ለቴዲ ጠበቆች ግራ ማጋባቱ አልቀረም። በነጋታው ጠበቆቹ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ነበረባቸው። ከፍርድ ቤት ያገኙት ምላሽ በቴዲ አፍሮ ላይ ምንም አይነት የማገጃ ትዕዛዝ ያለመኖሩን ነው። ከዚያም ወደ ኢሚግሬሽን ጉምሩክ እና ሌሎች ጉዳዩን የሚመለከቱ ቢሮዎች ሁሉ አመሩ። እዚያም የጉዞ ማገጃ አልተገኘም። ታዲያ ማን ይሆን ያዘዘው? የካዛንችዙ ስውር መንግስት ስራውን እንደገና ጀምሮ ይሆን?
ጉዳዩ ግራ ያጋባል። እርግጥ ነው። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ አንድ ተራ ካድሬ እንዲህ አይነት ተራ ወንጀል የሚፈጽምባት ሃገር ሆናለች። አንዳንድ ቦታዎች ላይ “መንግስት የለም እንዴ?” የሚያስብሉ ወንጀሎች እንደሚፈጽሙ ይሰማል። የቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚንስትር ዴዔታ የነበረው ኤርምያስ ለገሰ፤ በቅርቡ ባሳተመው “የመለስ ትሩፋቶች” የተሰኘ መጽሃፉ አዲስ አበባን ባለቤት አልባ ከተማ ብሏታል።
በልማታዊ አርቲስቶች እለት-ተለት የሚወደሰው ጸሃዩ መንግስት፤ ለልማት የተጋው መንግስት፣ ጭቆናን ያቆመው መንግስት፤ ለዜጎች መብትና ነጻነት የቆመ መንግስት፣ ሃገሪቱን ወደ እድገት እና ትራንስፎርሜሽን ጎዳና ላይ ያስኬደ መንግስት፣ የመቻቻል ባህልን ያመጣ መንግስት…. እንዴት ሆኖ የጥላቻ፣ የቂም እና የበቀል እርምጃ ሊወስድ ቻለ?
ልማታዊ አርቲስቶቻችን ይቅርታ አድርጉልኝና የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ሳይኖር ቁሳዊ ለውጥ ይመጣል ብሎ የነገራችሁ ማን ይሆን? አመለካከታችን ካላደገ፣ እድገት ይታሰብ ይሆን?
ወደ ጉዳዩ ስንመለስ፣ ከፊንላንድ በኋላ ሌሎች ስድስት የአውሮፓ ከተሞች ላይ ኮንሰርቶች ተዘጋጅተዋል። ፕሮሞተሮች ለመሰናዶው ብዙ ወጪ አውጥተዋል። የአርቲስቱ አድናቂዎችም አስቀድመው ትኬት ቆርጠዋል። ይህንን ካድሬዎቹ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ሁሉንም ማጉላላቱ፤ ከተቻለም ማደናቀፉ ደስታን ይሰጣቸዋል። እንዲህ አይነት የድፍረት ስሜት የሚመነጨው አርቲስቱን ሳይሆን ይልቁንም ሕዝብን በጅምላ ከማናቅ ነው። ሕዝብን ከመጥላት። እየገዙት ያሉትን ህዝብ መናቅና መጥላት የት ድረስ ሊያደርሳቸው እንደሚችል የምናየው ይሆናል። እንደ ሰብአዊ ፍጡር ሳይሆን እንደ እንስሳ የሚያስቡ እነዚህ የዘመናችን ጉዶች ሕዝብ የሚወደውን ነገር በሙሉ በመጥላት፤ የህዝብ አካል እንዳልሆኑ እይረጋገጡልን ነው። ከጫካ ከወጡ 21 አመታትን አስቆጥረዋል። አካላቸው ከጫካ ወጣ እንጂ አመለካከታቸው ግን እዛው እንደሆነ ድርጊታቸው ይነግረናል። ከሁለት ዓስርተ-ዓመት በኋላም ጥንት ከሚያስቡበት ከጫካው ህግ አልተላቀቁም።
ይህንን ትልቅ ሃገር እና ይህንን ትልቅ ሕዝብ እየመሩ ለምን እንደመንገስት ሊያስቡ እንደማይችሉ አይገባኝም። መንግስት ሆነው እንደግለሰብ ቂም ይይዛሉ። ቂም ይዘው እንደ ክፉ ሰው ይበቀላሉ። ሀገር ደግሞ በጥበብ እና በማስተዋል እንጂ፤ ከቶውንም በቂም እና በበቀል አትመራም። ይህንን የሚያደርጉ ሁሉ መጨረሻቸው ውድቀት፤ አወዳደቃቸውም የውርደት እንደሆነ ለደቂቃ አስተውለውት የሚያውቁ አይመስለኝም።
እንግዲህ ይህ ተራ ወንጀል በዚህ ድንቅ አርቲስት ላይ ሲፈጸም የመጀመርያ አይደለም። ከወራት በፊትም ወደ አሜሪካ ሊጓዝ ሲል የአየር መንገዱ ካድሬዎች ይዘው ብዙ አጉላልተውት ነበር። እርግጥ ነው ቴዲ አፍሮ ላይ ጥርሳቸውን ነክሰውበታል። ኤርምያስ ለገሰ፤ በ”መለስ ትሩፋቶች” መጽሃፉ ላይ የቴዲን ጉዳይ አንስቶ የገዢው ፓርቲ ሰዎች ይህንን አርቲስት እንዴት በክፉ አይን እንደሚመለከቱት ዳስሷል። ይህ አርቲስት ምናልባት በአንዲት ዜማ ተችቷቸው ይሆናል። እነሱም አላለፉትም። በፍትህ ስም የበቀል ዱላቸውን አሳርፈውበታል። ወህኒ ወርዷል። እስኪበቃቸውም ቀጥተውታል።
ቴዲ አፍሮ ግን ቂም አልቋጠረባቸውም። አሁንም የሚያቀነቅነው ስለ ፍቅር ነው። አሁንም የሚለው እንዲህ ነው። “ፍቅር ያሸንፋል!”
እነዚህ ሰዎች ሃያ ሁለት አመታት ሙሉ ከጥፋት አለመማራቸው ብቻ አይደለም የሚደንቀው። በአንድ ግለሰብ ምክንያት ከሚሊዮኖች ጋር እንደሚላተሙ አለማሰተዋላቸውም የሚገርም ነው። ለሟቹ ፓትሪያርክ ሲሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኦርቶዶክስ ምዕመናን ጋር ተቃርነው ነበር። አንድ የሙስሊም መጅሊስ መሪን ለመያዝ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሙስሊም ምዕመናን ጋር ጠፋጥተዋል።
ዛሬ አንድ ቴዲን ቢያንገላትቱት፣ ቢያግቱትም ሆነ ፓስፖርቱን ቢነጥቁት ለግዜውም ቢሆን የአድናቂዎቹን ስሜት ሊጎዱት ይችሉ ይሆናል። ይህ ድርጊታቸው ቴዲ አፍሮን ቅንጣት ያህል አይጎዳውም። ይልቁንም የበለጠ ተወዳጅ እና የበለጠ ጀግና ያደርገዋል። ከዚህ የፖለቲካ ንግድ እነሱ የሚያተርፉት ነገር ቢኖር የህዝብ ጥላቻን ነው። የቴዲን መታገት የሰሙ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ሳይቀሩ እንዲህ ሲሉ ተደመጡ፤ “አሁንስ አበዙት… ሃገራችንን እንድንጠላ አደረጉን….” ካድሬዎቹ ማህበራዊ ድረ-ገጾችን ቢጎበኙ የህዝቡን ስሜት ያነብቡ ነበር።
በሕዝብ አመኔታ ሳይሆን ይልቁንም በጆሮ ጠቢዎችና በመሳርያ በመተማመን እስካሁን ስልጣን ላይ ላላችሁት ገዢዎች ግን አንድ የምለው አለኝ። የፈረንሳዩ አንባገነን ናፖሊዮን ቦናፓርት የነበረውን ሰራዊት እስተውሉ። ይህ ግዙፍ እና የሰለጠነ ሰራዊት በህዝብ እንደ አሸዋ ተበተነ። የግብጹ ሆስኒ ሙባረክ ያልታሰበ እና ያልታለመ ውድቀት የመጣው እንዲሁ በመሳርያ ከመተማመን እና ህዝብን ከመናቅ ነበር። ይህ አስደንጋጭ ትዕይንት ለእናንተ ትምህርት ካልሰጣቸሁ የሱ እጣ ፈንታ ይጠብቃችኋል። መቶ አመት የቆየ አንባገነን ገዢ በታሪክ አላየንም።
Like ·  · 

No comments:

Post a Comment

wanted officials