Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, December 23, 2014

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን አስጠነቀቁ

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን አስጠነቀቁ

ታኀሳስ ፲፫(አስራ ሦስትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ፓርላማ አሸባሪ ብሎ ከፈረጃቸው ድርጅቶች ጋር በቀጥታ እየተገናኙ የሀገራችንን ጥቅምና ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አሉ ሲሉ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ዛሬ በጽ/ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የፓለቲካ ፓርቲ አባላት እየታሰሩ መሆናቸውን አስመልክቶ በቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አሸባሪ ከሚባሉ ቡድኖች በቀጥታ እየተገናኙና እያቀዱ ሀገር ለማሸበር እየዶለቱ የሚውሉ ሃይሎች መሆናቸውን በመጥቀስ መንግስት ይህንን እያየ ዝም አይልም ብለዋል፡፡
ሀገራችን እንደአንዳንድ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት እዚህም እዚያም ቦምብ የሚፈነዳባት ሀገር እንድትሆን አንፈልግም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፣  መንግስት በሕጋዊነት በተመሰረቱ ፓርቲዎች ውስጥ ከሽብር ቡድኖች ጋር የሚተባበሩ ግለሰብ መሪዎች ስላሉ የፓርቲው አባላት መሪዎቻችን ለምን ታሰሩ ብለው ሊጠይቁ አይገባም በማለት ተናግረዋል፡፡ አመራሮቹ የታሰሩት ከሽብር ቡድኖቹ ጋር የተነጋገሩትን በድርጊት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ሕግና ስርዓትን ማስከበሩ ተገቢ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ መንግስትን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት የልማት ሥራዎች በሚከናወኑበት ቦታዎች ሰልፍ አካሂዳለሁ በማለት መንግስትን ለመፈታተን መሞከራቸውን ያስታወሱት ጠ/ሚኒስትሩ ይህ እንደማያዋጣ በተደጋጋሚ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡
ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን በሶስት ከፍሎ እንደሚያያቸው የጠቀሱት አቶ ኃይለማርያም እነሱም በአግባቡ የጨዋታ ሕጉን አውቀው ለመንቀሳቀስ የሚጥሩ መኖራቸውንና እነዚህ ተጠናክረው ቢቀጥሉ የመንግስት ፍላጎት መሆኑን፣ ሁለተኛዎቹ ወጣገባ የሚሉ መኖራቸውንና ይህን ቢያስተካክሉ ጥሩ አቁዋም እንደሚኖራቸው፣ ሶስተኛዎቹ  የውጪ ሃይሎች የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ የሆኑ፣ የአመጽና ብጥብጥ ውይይትና ስብሰባ ሲያካሂዱ የሚከርሙና ለሀገሪቱ ፖለቲካ ፋይዳ የሌላቸው መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ጠ/ሚኒስትሩ ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለመወያየት የሚያቀርቡትን ጥያቄዎች በተመለከተም ተጠይቀው መጀመሪያ የስነምግባር ደንቡን መፈረም እንዳለባቸውና በዚሁ መሰረት ውይይት ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ሰሞኑን በባህዳር ከተማ ከእምነት ጋር ተያይዞ በተደረገ ሰልፍ ላይ የሞቱና የቆሰሉ ሰዎች በተመለከተም ተጠይቀው ሁኔታው እንደሚጣራና በጸጥታ ሃይሎች በኩል ጥፋት ካለ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials