(በኤልሳቤጥ ግርማ ከኖርዌይ)
በዚህ በያዝነው ወር በየዓመቱ ስለግንቦት 20 በተለያየ መልኩ ይሰበካል፣ ይገለጻል። ለሀገራችን ኢትዮጵያ ታምራዊ ለውጥ እንዳስመሰገበ ሁሉ ወሩን ሙሉ ሲተረክ መስማት እንደ ሀገራዊ መዝሙር የተለመደ ሆኗል:: በተለይ የሥርዓቱ ባለቤቶችና ደጋፊዎች ምስኪኑን ሕብረትሰብ ሳይቀር በማስገደድ ቀኗን “ልዩ ቀን” “የድል ቀን” “የስኬት ቀን” በማለት ሰይመው በአስረሽ ምችው ሲከበር ማየት ድፍን 25 ዓመታትን አስቆጠረ።
ጀግናው የኢህአዲግ ሰራዊት ደርግ ኢሰፓ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬዲዮ ጣቢያ ተቆጣጥሮታል ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሦስት ብለው እንዳበሰሩን በእርግጥ ለጥቂቶች ግንቦት 20 የድል ቀን ነው:: ምክንያቱም ሀገሪቱን በአንባገነናዊ አገዛዝ ለማስተዳደርና የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት መሰረት የጣሉባት እና የአስራ ሰባት ዓመት የልፋት ዋጋቸውን ያገኙባት ልዩ ቀን ናትና:: በዚች ቀን ህብረተሰቡን በምስጢራዊ የአገዛዝ ስልት ለማስተዳደርና ስልጣናቸውን ዘላለማዊ ለማድረግ የነበራቸው ሕልም እውን የሆነባት ቀን ናትና በልዩ አከባበር ቢያከብሯት ሲያንሳት እንጂ አይበዛባትም::
ጀግናው የኢህአዲግ ሰራዊት ደርግ ኢሰፓ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬዲዮ ጣቢያ ተቆጣጥሮታል ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሦስት ብለው እንዳበሰሩን በእርግጥ ለጥቂቶች ግንቦት 20 የድል ቀን ነው:: ምክንያቱም ሀገሪቱን በአንባገነናዊ አገዛዝ ለማስተዳደርና የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት መሰረት የጣሉባት እና የአስራ ሰባት ዓመት የልፋት ዋጋቸውን ያገኙባት ልዩ ቀን ናትና:: በዚች ቀን ህብረተሰቡን በምስጢራዊ የአገዛዝ ስልት ለማስተዳደርና ስልጣናቸውን ዘላለማዊ ለማድረግ የነበራቸው ሕልም እውን የሆነባት ቀን ናትና በልዩ አከባበር ቢያከብሯት ሲያንሳት እንጂ አይበዛባትም::
የተወሰኑ የስራዓቱ አቀንቃኞችም ስለቀኗ መልካምነትና ከዚያች ቀን በኃላ አገራችን ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና የገስገሰች፣ የዜጎች አኩልነት የተረጋገጠባት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ ሰባዊ መብቶች የተከበሩባት፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የታየባት፣ ህብረተሰቡን በእኩል የሚያስተዳድር መንግስትና ሕግ መንግስት የተመሰረተባት አገር እንድትሆን ግንቦት 20 ታሪካዊ የድል አሻራ እንደጣለች በኩራት አፋቸውን መልተው ይናገራሉ:: ይባስ ብለው ከውጭ ወራሪ ወይም ቅኝ ግዛት ኢትዮጵያን ነፃ ያወጧት ይመስል ግንቦት 20ን የነፃነት/ሀገራዊ ቀን ለማድርግ የሚሞክሩ ብልጣብልጥ የስራዓቱ ደንገጡሮችም አሉ::
በእርግጥ የደርግ አንባገነን መንግስት የአጼ ኃይለ ስላሴ መንግስትን ገርስሦ በምትኩ ወታደራዊ ጁንታ በመመስረት ስሙን በመቀያየር አገዛዙ ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን በብዙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በተለይ ሀገሪቱን መለወጥ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡትን 60 ሚኒስተሮች በመረሸን፣ ነጭና ቀይ ሽብር በማለት ሀገር ተረካቢ ትውልድን በማስጨፍጨፉ የኢትዮጵያ ህዝብ የደርግን ስርዓት አንቅሮ ተፍቶት ነበር። የለውጥ ያለሽ ብሎ በመጮህ ከደርግ አረመኔያዊ የጭካኔ አገዛዝ ነጻ ሊያወጣው የሚችል መለኮታዊ ኃይል እስኪፈልግ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ለውጥ ፈላጊ ሆነ።
ህወሓት የህዝቡን ብሶትና እሮሮ ተጠቅሞ 17 ዓመት ጫካ ውስጥ ያረገዘውን መርዝ ለመርጨት ግንቦት 20 ደርግን ገርስሦ በትረ ስልጣኑን ጨበጠ። እዚህ ላይ ወያኔ የደርግን ስርዓት ሳያይና በትንሹም ቢሆን ለውጥ እንዲመጣ ጥረት ሳያደርግ ለትግል ወደ ጫካ መግባቱ ሀገራዊ ለውጥ አሳስቦት ሳይሆን የብሄር ፖለቲካ ጥማት እንደሆነ በትክክል መገንዘብ ይቻላል፤እያየነውም ነው። የብሄር ፖለቲካ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችን ለምታስተናግድ ሀገር ቀርቶ ለየትኛውም የአለም ሀገራት የማይበጅ መሆኑ የታወቀ ነው። ኢትዮጵያም የከፋፍለህ ግዛውና የጎሳ ፖለቲካ እንደማይጠቅማት ከዘመነ መሣፍንት ትምህርት ቀስማ ነበር። ዳሩ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የደርግን ሥርዓት ጥላቻና ሽሽት ዘረኛው ወያኔን ግንቦት 20 በሩን ከፍቶ እጁን ዘርግቶ ተቀበለ።
ወያኔዎች የደርግን ሥርዓት ገርስሰው መንግስቱ ኃይለ ማርያምን ወደ ዝምባብዌ ካስኮበለሉ በኋላ ሥልጣናቸውን ለማጽናት የይስሙላ ህገ መንግሥት አርቅቀው አጸደቁ። ለተወሰኑ ዓመታትም የነጻነት በርን ለመከፈትና ስላምና መረጋጋትን ለማስፈን የመጡ እስኪመስል ድረስ ሰላምን ሰበኩ። ከደርግ ጋር ንክኪ አላቸው ተብሎ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በሙሉ እስር ቤት ወረወሯቸው። ከገጠር እስከ ከተማ ህብረተሰቡ ለራሱ መጠበቂያ ብሎ የገዛዉን ትጥቅ ሳይቀር በሙሉ አስፈቱ። የኢትዮጵያ ህዝብ ግንቦት 20 በየዓመቱ “የድል ቀን” እያለ እንዲዘምር ተደረገ።
በእውኑ ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ ምኑ ነው? ይህ ጥያቄ በተለያየ መልኩ በሁላችንም አይዕምሮ ውስጥ እንደሚመላለስ እርግጠኛ ነኝ። መልሳችን ግን በራሳችን ምዕናባዊ እይታ ስለምንመለከተው የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ግን ከሁለት አማራጮች ሊዘል አይችልም። ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔዎች እንደሚሉት “የድል ቀን” ወይም ብዙዎች እንደሚስማሙበት “የውድቀት ቀን” መሆን አለበት። ወያኔዎችና ደጋፊዎቻቸው ግንቦት 20ን “የድል ቀን” ማለታቸው በእርግጥም ትክክል ናቸው። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የአንባገነን ስልጣናቸውን ያፀኑበት እና በሦስቱም ዘርፍ ማለትም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩበት ቀን ነውና።
እውነታው ሲገለጥ ግን ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ የውድቀት እና የውርደት ቀን እንጂ በምንም መመዘኛ የድል ቀን ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ለአንድ ሀገር የድል ቀን ሲባል ዜጎቿ እኩል ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል በጎ አጋጣሚ ወይም የኩራት ምንጪ ሲፈጠር ብቻ ነው። ግንቦት 20 ግን ከዚህ በተቃራኒው መሆኑን ግልጽ ሊያደርግ የሚችል ብዙ ማሳያዎች ከመኖሩም ባሻገር በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ችግር ዘርዝሮ መናገር ይቻላል።
“የድል ቀን ሆይ የት ነሽ?ምንጭሽስ ከቶ ከወደየት ይገኛል?”
የኢትዮጵያ ህዝብ ከግንቦት 20 የተቀበላቸውን ገጸ እርግማኖች ለማሳያ ያክል እንደሚከተለው እናያለን፤
የኢትዮጵያ ህዝብ ከግንቦት 20 የተቀበላቸውን ገጸ እርግማኖች ለማሳያ ያክል እንደሚከተለው እናያለን፤
የብሄር ፖለቲካ የተፀነሰበት
የህወሓት ማፍያ ቡድን ገና ከጅምሩ ሃገራዊ ፍቅር ሰንቆ እንዳልመጣ ከስሙ መረዳት ይቻላል። የትግራይ ነጻ አውጪ ቡድን ብሎ መሰየሙ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ እንዳልቆመ ለመረዳት ነብይነት አያሻውም ነበር። የከፋፍለህ ግዛው መርህን በማንፌስቶው ይፋ አድርጎ ይንቀሳቀስ እንደነበር ሰነዶች ህያው ማስረጃ ናቸው። ለስልጣን ማራዘሚያ በዋናነት የተጠቀመበት ዋናና ትልቁ አጀንዳ የብሄር ፖለቲካን ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ካልሆነ በስተቀር ከስልጣን ሊወርድ የሚችልበት ምንም አይነት አጋጣሚ እንደሌለ በሚገባ ያውቃልና። የብሄር ፖለቲካ እያራመደ እርስበርሳችን እንዳንተማመን በብሄር ለያይቶናል። ይሄ የናንተ መሬት ነው፣ ይህ ደግሞ የነሱ ነው ወዘተ እያለ በቡድን ከፋፍሎናል። በብሄሮች መካከል መግባባት እንዳይኖር እነእገሌ እንዲህ አደረጓቹህ፣ ታሪካችሁ እንዲህ ነው በማለት መጀመርያ መምጣት ያለበት ብሄር ነው ወዘተ እያለ የብሄር ጥላቻ እንዲሰፍን ሀውልት ሰርቶልናል። አንድ ዜጋ ኢትዮጵያዊ ነኝ ከማለት ይልቅ በውሸት የብሄር እኩልነት ስም ኦሮሞ፣አማራ፣ ጉራጌ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ እያለ በየቦታው እራሱን እያዋረደ እርስ በእርሳችን በጥላቻ እንድንናቆር ማድረጉ የወያኔ የብሄር ፖለቲካ ውጤት ነው። ስለዚህም ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ የድል ቀን ሳይሆን የብሄር ፖለቲካ የተፀነሰበት የውርደት ቀን ነው። “የድል ቀን ሆይ የት ነሽ?ምንጭሽስ ከቶ ከወደየት ይገኛል?”
ትውልድ ገዳይ ሥርዓተ ትምህርት የተቀረጸበት
ትምህርት ቤቶች ለአንድ ሀገር ተተኪ ዜጋ ፈጣሪ ተቋም እንደመሆናቸው መጠን የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ፣ ታሪክንና ባህልን ከማሳወቅ ባለፈም በማንነት ላይ የተመሰረተ ጥራት ያለው ዜጋ ለማፍራት የሚቀረጸው ሥራተ ትምህርት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ነገር ግን ወያኔ የቀረጸው ሥርዓተ ትምህርት ግን ትውልድን ገዳይና የተማሪዎችን አይዕምሮ ለምርምርና ጥናት የማይጋብዝ ዘላቂና አስተማማኝ ያልሆነ ጥራት የጎደለው ሥርዓተ ትምህርት ነው። ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎችን በጥሩ ሥነ ምግባርና ባህልን ከማሳዎቅ አንጻር አስተምሯቸው ዝቅተኛና ከዚህ ግባ የማይባል መሆኑ ለትውልዱ መጥፋት ሌላው የወያኔ የስርዓቱ ውጤት ነው። ትምህርት ቤቶችን ስንመለከት ከተቀረጸላቸው ሥርዓተ ት/ት ጀምሮ ትውልድን ለመቅረጽ ቀርቶ በዜግነት ደረጃም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚናገር ትውልድ እንዲጠፋ በማድረግ ረገድ ግንቦት 20 የራሷን ጥቁር ጠባሳ ጥላለች። አንዳንድ የዘመነ ወያኔ ተማሪዎች የሀገረን ታሪክ በሚገባ ካለማዎቅ የተነሳ ቅኝ ግዛት በተገዛን ኑሮ ሲሉ መስማት የሥርዓተ ትምህርት ውድቀቱን ማሳያ አንዱ መንገድ ነው።
የሃገር ዳር ድንበር የተደፈረበት
አንድ ሀገር የድል ቀን የምታከብር ከሆነ ለሀገርና ለህዝብ የሚቆረቆር መንግሥት አላት ማለት ነው። መንግሥት ካለ ደግሞ የሃገር ሉዓላዊነት ተጠብቆ፣ ታሪኳ ሳይበረዝና ሳይፋለስ ለትውልድ መተላለፍ ይችላል ማለት ነው። ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ግን የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ዳር ድንበሯ የተደፈረባት፣ ወደቧን ያጣችበትና ታሪኳ የተበረዘበት ዘመን ነው። ድሮ አባቶቻችን ቅኝ አንገዛም በማለት ታሪካችንና ባህላችን ሊበረዝ ከቶ አይችልም ብለው አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው፣ ውድ ህይወታቸውን ሰውተው ዳር ድንበሯን ከነሙሉ ክብሯ ያቆዩልንን ሀገር ወያኔ ለአረብና ህንድ ባለሃብቶች ማቀራመቱ ሳያንሰው ሱዳን የድርሻሽን ውሰጅ ብለው በመማጸን ላይ እንደሆኑ ስንሰማ በእውነትም ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ የውርደትና የውድቀት ቀን ነው። ዜጎቿ በሄዱበት ሞትና እንግልቱ ሳያንሳቸው በእራሳቸው ሀገር በሌላ ዜጋ እንደ እንስሳ ደማቸው ሲፈስና ህጻናት በገፍ ተግዘው ሲሄዱ ከማየት በላይ ምን የተለየ ውርደትና ውድቀት ይኖራል። “የድል ቀን ሆይ የት ነሽ?ምንጭሽስ ከቶ ከወደየት ይገኛል?”
ህዝቦቿ ለሞት፣ለስርና በስደት ለውርደት የተዳረጉበት
በወያኔ አገዛዝ ከ1983 እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከግንቦት ወር ጀምረን በግፍ ውድ ህይወታቸውን በስውርና በአደባባይ የተቀሰፉ፣ ለስር፣ ለእንግልትና ለስደት የተዳረጉ ዜጎችን የሰማይ አምላክ ይቁጠራቸው እንጂ በአኃዝ ማስቀመጥ እጅጉን ይዘገንናል። ተፈጥሯዊና ሰባዊ መብቶች በይፋ ተገርስሰዋል። የስርዓቱ አባል፣ ደጋፊና አገልጋይ ካልሆነ በስተቀር በሀገሩ ምድር ቀና ብሎ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀት እና የመስራት መብቶች ፈጽመው መገደባቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ወያኔዎች ግንቦት 20ን የድል ቀን ብለው ማክበር ከጀመሩ ጀምሮ በሀገሪቱ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የግፍ ጽዋ ሞልቶ ፈሷል። ህዝቦቿ በሄዱበት ሁሉ የውርደት ካባ እየተከናነቡ ተቆርቋሪ ያጣ ዜጋ በመሆኑ ዋይታና ልቅሶው ከመቸውም በላይ ጨምሯል። “የድል ቀን ሆይ የት ነሽ?ምንጭሽስ ከቶ ከወደየት ይገኛል?”
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አገራችን የተለያየ መልክና መገለጫ ያላቸው በርካታ መንግሥታትን ያስተናገደች አገር ብትሆንም ለዘመናት ታሪኳን፣ ባህሏን፣ እምነቷን፣ አንድነቷን፣ ድል አድራጊነትን እና ዳር ድንበሯን ጠብቃ አስጠብቃ የኖረች እና መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ እንግዳ ተቀባይነትን፣ ዘርንና ጎሳን መሰረት ሳታደርግ ለዘመናት የቆየች የጀግኖች አገር ነበረች። ነገር ግን ግንቦት 20 የለገሰን የአሳርና የግፍ ፍሬዎች በቀላሉ የማይሽሩ እኩይ ተግባር ናቸውና ታሪካዊ አገራችንን አደጋ ላይ ጥሏታል። ስለሆም ጊዜ ሳንሰጥ “የድል ቀን” የሚለውን ተረት ተረት ወደ ጎን በመተው በአንድነትና በህብረት ዛሬውኑ የውርደትን ቀን ወደ የድልና የክብር ቀን ሊቀየር ይገባል። ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ የድል ቀን ሳይሆን የሞት፣የውድቀትና የውርደት ቀን ተብሎ ይስተካከል!ምነው ሽዋ! ድንቄም የድል ቀን…………
No comments:
Post a Comment