Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, May 27, 2016

በሙርሌ ታጣቂዎች ታግተው በድርድር የተለቀቁ ህጻናት ለስነልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል ተባለ

በሙርሌ ታጣቂዎች ታግተው በድርድር የተለቀቁ ህጻናት ለስነልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል ተባለ

ኢሳት (ግንቦት 18 ፥ 2008)
ከጋምቤላ ክልል በታጠቁ የሙርሌ ጎሳ አባላት ተጠልፈው ወደደቡብ ሱዳን ከተወሰዱት በኋላ በድርድር የተለቀቁት ህጻናት፣ ወላጆቻቸውን በማጣታቸውና በጠለፋ ወቅት በማያውቋቸው ሰዎች እጅ በመውደቃቸው በስነልቦናዊ ቀውስ እንደተዳረጉ ተገለጸ። ከጥቃቱ ያመለጡና ልጆቻቸው ተጠልፈው ያልተመለሱላቸው ወላጆችም እንዲሁ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ተነግሯል።
ጃኒ የተባለ አንድ ህጻን ከተጠለፉበት ቀን ጀምሮ በአንድ ጎጆ ውስጥ ተቆፎበት ወተት ብቻ እየተሰጠው በከፍተኛ ሁኔታ በታጠቁ ሃይሎች ሲጠበቅ እንደነበር ለወላጆቹ መናገሩን ጠቅሶ ቢቢሲ ትናንት ረቡዕ ዘግቧል።
ከአንድ ቤት ውስጥ ከተጠለፉት 4 ህጻናት መካከል አንዱ የሆነው የ 11 አመቱ ጃኒ፣ ከደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በድርድር ቢለቀቅም ሁለት ወንድሞቹና አንድ እህቱ ግን እስካሁን የደረሱበት አለመታወቁን የህጻናቱ እናት ወ/ሮ ኒያርዳን ለቢቢሲ ተናግረዋል። “ልጆቼን በህይወቴ ደግሜ የማያቸው አይመስለኝም ነበር” ያሉት ወ/ሮ ኒያርዳን፣ ቀሪ ሶስት ልጆቻቸው ተለቀው ይመጣሉ ብለው ቀንና ሌሊት በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑት አራቱ ህጻናት ላሬ ከተባለው መንደር የተወሰዱት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች አካባቢውን በሃይል ከተቆጣጠሩ በኋላ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። አብዛኞቹ ወላጆች በደረሰባቸው ድንገተኛ ጥቃት የተገደሉ ቢሆንም፣ የተወሰኑት ወላጆች ግን ሸሽተው በማምለጥ ከጥቃቱ ለማምለጥ መቻላቸው በወቅቱ መዘገባችን ያወሳል።
ባለፈው ወር ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በኑዌር መንደሮች ላይ በወሰዱት ድንገተኛ የጥቃት እርምጃ 208 ሰዎችን ገድለው፣ 149 ህጻናትንና መጥለፋቸውንና 2000 የቀንድ ከብቶችን ነድተው እንደወሰዱ ዘግበን እንደነበር አይዘነጋም።
ባለፉት ሶስት ሳምንታት በድርድር ከተለቀቁት 53 ከሚሆኑት ህጻናት ውስጥ የሶስት አመት ህጻን ጭምር እንደሚገኝበትም ለማወቅ ተችሏል። እነዚህ ከቤተሰቦቻቸው በሃይል ተጠልፈው የተወሰዱ ህጻናት ሰውነታቸው ገርጥቶ በስነልቦናዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል። ይህም ስነልቦናዊ ጉዳት እድሜ ልካቸውን አብሯቸው ሊዘልቅ እንደሚችል ማይክ ቻርሌይ የተባሉ የዩኒሴፍ የህጻናት ጥበቃ ባለሙያ መናገራቸው ተመልክቷል።
ከጥቃቱ የተረፉ 22 ሺ የሚሆኑ ወላጆችም ቀያቸውን ትተው ተሰደዋል ፥ ወደቀያቸውን ለመመለስም ፍርሃት እንዳለባቸው ተናግረዋል።  ከጥቃቱ የተረፉት ኒያኩዎች ቦዝ የተባሉ አንዲት ሴት፣ “ወደ ቤቴ መመለስ አልፈልግም ፥ በዚያኑ ቀን ባለቤቴ ተገደለ፣ ሁለቱ ልጆቼ ተወሰዱብኝ ምን የቀረኝ ነገር አለ? ለምንስ እሄዳለሁ” ሲሉ በቀያቸው ምንም የቀራቸው ነገር እንደሌላቸውና ወደ አካባቢው ቢመለሱ ስነልቦናዊ ህመም እንደሚፈጥርባቸው ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials