Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, May 12, 2016

የዛሬው የኢትዮጵያ ችግር ተጠያቂው ማን ነው – ሰርጸ ደስታ

ብዙ ጊዜ ሳስተውል በተለይ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ለነገሮች ተወቀሽ የሚሆኑት በስልጣን ላይ ያሉና የነበሩ ግለሰቦች ወይም የእነሱ አገዛዝ ብቻ ናቸው፡፡ በተቃራኒው እነዚህን ባለስልጣናትና አገዛዛቸውን የተቃወመ ብዙ ጊዜ ይወደሳል፡፡ በታሪክ ውስጥም ትልቅ እይታ ተሰጥቷቸው የሚነሱት ገዥና ተቃዋሚ ጎራ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ከታሪክ እንደምናየው እነዚህ ሁለቱም የየራሳቸው ጉድለት ያለባቸው ማስተዋላቸውን ስሜታዊነትና እኔ እበልጥ የሸፈነባቸው፣ ውሳኔዎቻቸውና ድርጊቶቻቸውም የራሳቸውን ምኞት እንጂ የአገርንና ሕዝብን የማይወክል ነው፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱ ውጭ ሆነው ግን በሰከነ አስተሳሰብና ፍልስፍና ከቀደሙና ካሉ ነባራዊ ነገሮች ተንተርሰው የነገሮችን መጻኢ ሁኔታ የሚተነብዩና አቅጣጫንም መሆን በሚገባው የሚጠቁሙ ቦታ አይሰጣቸውም፡፡ ኢትዮጵያ በተለይም ከ50ዎቹና 60ዎቹ ጀምሮ እስከዛሬም ድረስ የራሳቸው ስሜት፣ ዝናን፣ ስልጣንና ገንዘብ ያሳበዳቸው የአገርና ሕዝብ ጉዳይ ከአእምሮአቸው የነጠፉ ሰዎች ሀሳብና ፍላጎት መመራቷ ብቻም ሳይሆን ለወደፊት የእነዚሁ ልክፍቶች ሰለባ መሆኗ አእምሮ ላለው ያማል፡፡ ሕዝብና አገር መነገጃ ሆነዋል፡፡ እባካችሁ ይሄ ነገር አይሆንም ብለው የነበሩ ዛሬ በሕይወት የሉም ካሉም ዝም እንዲሉ ተደርገዋል፡፡
እንደእኔ አስተሳሰብ ከ50ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እስከ 70ዎቹ መጀመሪያ ባሉት እንቅስቃሴዎች ተሳተፍኩ እያለ እንደ ትልቅ ነገር የራሱን ዝና ዛሬም ድረስ እየነገረን ያለው ትውልድ ትልቅ የአእምሮ መዛባት ችግር የገጠመው ነው ባይ ነኝ፡፡ እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ ከዚህ ትውልድ አስተሳሰብ ያፈነገጠ ሁሉ እንደ እብድ እየታየ ዝጋ ይባላል ወይም የሚያስፈራ መስሎ ከታየም ለዘላለሙ ይሸኛል፡፡ ዛሬ በዋነኝነት አገርንም የሚመራው፣ እንደተቃዋሚም የሚንቀሳቀሰው የዛ ትውልድ ነው፡፡ ጥሩና ትክክል የሚያስቡት አሁንም እድል አልቀናቻቸውም፡፡ እና ማን እያሰበ አገርና ሕዝብ ሠላም ሊሆኑ እንደሚችሉ ሳስብ ግራ እጋባለሁ፡፡UDJ-Ethiopia.jpg
የዛን ትውልድ እንዳንድ ባሕሪያት ለመጠቆም
  1. ስብዕና የሌለው ጨካኝ
  2. እምነት ከአላቸው ወላጆች ተወልዶ ሐይማኖት የሌለው ከሀዲ
  3. ተቃዋሚሕን አጥፋ ነገ ሊያጠፋሕ ይችላል በሚል ፍልስፍና የተለከፈ ፈሪና ተጠራጣሪ
  4. ራሱን ምሁርና አዋቂ ያደረገ በሌሎች ፍልስፍና የባርነት አዘቅት የወደቀ
  5. የሌሎችን የሚናፍቅ መሠረቱን ያላወቀ
  6. የአገርና ሕዝብን ለራሱ ጥቅም መሳሪያ ያደረገ የሕዝብና አገር ጠላት
  7. ራሱን ዝነኛ ለማድረግ እስከሞት ድረስ የሚንፈራገጥ
  8. አመክንዮ (ሎጂክ) የሚባል ነገር የሌለው ግትርና ነባራዊ ነገሮችን ለማሰብ አምቢ ያለ
  9. ውሸታምና ውሸትንም በመደጋገም እውነትን ከሰው አእምሮ የሚያምከን የመሳሰሉት
ይህ ከላይ የዘረዘረኩት የእኔ እይታ እንጂ ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡  በእኔ ግንዛቤ ስልጣን ላይ ወጣም አልወጣም፣ ተቃዋሚ ሆነ ገዥ ተማርኩ የሚለው አብዛኛው የዛ ትውልድ  ዛሬ ኢትዮጵያ ለገባችበት ምስቅልቅል ተጠያቂ ነው ባይ ነኝ፡፡ የቀደመውም በኋላም የመጣው ግን ሙሉ በሙሉ ነጻ ነው ማለቴ አይደለም፡፡
ዛሬ የምንሰማው አብዛኛው ድምጽ ንጉሱን በወቅቱ የተቃወመው የዛ ትውልድ ስለሆነ በወቅቱ እውነታው ምን እንደነበር መረዳትም ያስቸግራል፡፡ የንጉሱ የአገዛዝ ዘመን ብዙ ጉድለቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ አልጠራጠርም፡፡ በእርግጥም እነዚያ ጉድለቶች በወቅታቸው አለመደፈናቸው ምክነያት ሆነው ዛሬ ድረስ ለቀጠለው የአገርና ሕዝብ ጉዳይ የማይገባው በዛ ትውልድ እጅ አገር እንደወደቀች አምናለሁ፡፡  ከእነዚህ አንዱን መሬትን እንውሰድ፡፡ የመሬት ይዞታ ጉዳይ የንጉሱ ፍላጎት ብቻም ሊሆን እንደማይችል እገምታለሁ፡፡ ይልቁንም የአደገኛ ባላባቶች ለጉዳዩ መላላትን ያለማሳየትና በሕዝብ ላይ በፈጸሙት የአገዛዝ ጫና እንጂ፡፡ ሆኖም በቆይ የሄ ጉዳይ በሌላ መልኩም ቢሆን እልባት እንደሚያገኝና ንጉሱም ለዛ ያሰቡበት ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ዓለም ላይ ብዙ አገራት የመሬትን ይዞታ ጉዳይ የፈቱት እኛ በሄድንበት መንገድ አይደለም፡፡ ይልቁንስ እኛ የተከተልነውን አይነት መንገድ የተከተለ ለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንደውም መሬት በእነዛው ድሮ በነበሩ ባለመሬቶች እንደ ተያዘ ነው ለውጡ ከአንዱ የምጣኔ ሀበት እድገት ወደሌላው የተሸጋገረው፡፡ የፊውዳሉን የአገዛዝ ሥርዓትም እጅግ ያከፋነው እኛ እንጂ ከሌሎች አገራት የከፋ ሆኖ አይመስለኝም፡፡ የሥርዓት ሽግግራቸው ግን እንደ እኛ ሥር ነቀል አይደለም፡፡ ሌላ ቀርቶ የታወቁ አብዮቶች የተካሄደባቸው አገራት ድሮ የነበረውን ሙሉ በሙሉ የለወጠም አይደለም፡፡ ዛሬም ድረስ የዛ ሥርዓታቸው ቅሪት ይዘው እየተጓዙ ነው፡፡  ሥር ነቀል የተባለለት የእኛው ግን የታሰበውንም ለውጥ ሳያመጣ የአገርን መሠረት ያናጋ እስካሁንም በሁለት እግር መቆም የላስቻለን፣ ይልቁንም እየከፋ የመጣ ነው፡፡
ከመሬት ውጭ ያሉ ለውጦች ጭራሽ አገርንና ሕዝብ የማይፈልጓቸው ያ ትውልድ ለራሱ እንዲመቸው ሆን ብሎ ያመጣብን አደጋዎች እንደሆኑ በደንብ ከውጤታቸው እያየን ነው፡፡ የፌደራሊዝም ጥያቄ፣ የብሔረሰብ ጥያቄ፣ የሴቶች፣ የወጣቶች ወዘተ የሚባሉት ሁሉ የአገርና ሕዝብ ሳይሆኑ ያ ትውልድ ለራሱ እንዲመቸው ያመጣብን መርዞች ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አገርና ሕዝብ ፍትሕን፣ መልካም አስተዳደርን፣ ድህንነትንና ልማትን ነው የሚፈልገው፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እኔ በአደኩበት ሥፍራና ሁኔታ ብዙም ያልተረዳሁት ግን የብሔረሰብን ጥያቄ የመሳሰሉ ጉዳዮች በሌላ አካባቢ የሕዝብ ጉዳይ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ኋላ ግን እድሉ ገጥሞኝ አገሪቱን ሙሉ በሙሉም ባይሆን ቢያንስ ከግማሽ በላይ በተለያይ አጋጣሚዎች ስንቀሳቀስ እንዳየሁት የብሔረሰብ ጥያቄ ከነጭርሱም የሕዝብ ችግር አልነበረም፡፡ ይልቁም ሕዝብ በተለይ በእድሜ ጸና ያሉ አረጋውያን ይሄ አሁን በእናንተ ዘመን የመጣብን ችግር ነው እያለ ያመጣባቸውን ትውልድ ሲወቅስ እናስተውላለን፡፡ ልብ በሉ መፍትሔ የተባለው ሲጀምር ችግሩ በሌለበት ነው አሳዛኙ ደግሞ ላልነበረ ችግር መፍትሄ በሚል በሕዝብ ዘንድ ግን ችግር የሆነውን መተግበር ነው፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ ብትሄዱ በሚኖርበት አካባቢ ሕዝቡ ባሕሉንም፣ ቋንቋውንም እንደልቡ ነው የሚጠቀመው፡፡ በቋንቋውና በባሕሉ የሚያፍር ሕዝብ አልገጠመኝም፡፡ ችግሩ ከተለያየ ሕዝብ ወጥተው ት/ቤት የተገኛኙ ተማሪዎች እንደነበር አሰብኩ፡፡ እዛው ት/ቤት ተወልዶ አብሯቸው ዩኒቨርሲቲ የዘለቀ የበታችነትና የበላይነት ስሜት የብሔረሰብ የምትል ጥያቄ እንዳመጣ ተረዳሁ፡፡ ጥያቄው የሕዝብ እንዳልሆነም፡፡ በቅርቡ ከኤስቢኤስ ራዲዮ ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት ፕ/ር ዓለም ሀብቱ ጥያቄው ከእነጭርሱ የኤርትራን ሕዝብ ለመደገፍ በሚል እንደተነሳ ይነግሩናል፡፡
አየር ላይ ከዋለ የቆየ ቢሆንም እኔ በዚህ ሳምንት ያየሁት የሚከተለው ሊንክ ላይ የምንሰማው ሰው(ሥሙን ማወቅ አልቻልኩም፣ ከይቅርታ ጋር የተናጋሪውን ሥም የሚያውቅ ቢነግረኝ እላለሁ) አስበው የነበረውን ሁሉ ሲናገረው ስሰማ ከማሰብም አልፈው ብዙ የለፉ እንደነበሩ አስቤ እራሴንም ታዘብኩ፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=sz3M9jiwx0w
ተናጋሪው በ60ዎቹ እንቅስቃሴ ተሳታፊ የሆነ ዕድሜ ያለው አይመስልም፡፡ የሚያወራው ግን የሟች ጠ/ሚኒስቴርን መለስን ጨምሮ አብዛኛው የስልሳዎቹ ለሆኑት ተሰብሳቢዎች ነው፡፡ ተናጋሪው እኔ ነብይም ወልይም አደለሁም ይላል፡፡ ልሆን የሚችለውን አደጋ ግን ከሩቅ ሆኖ ወደፊት መተንበይ ነብይ አለመሆኑ አላገደውም፡፡ የሚናገረውም  በዘመናት ከአያቸው ነባራዊ እውነታዎችና ልምዶቹን መሠረት አድርጎ እንጂ ጥሩ ተናጋሪ ለመባል፣ ለመደነቅ አይደለም፡፡ እንዲያ ሲሆን በእርግጥም ነብይም ባይሆኑ ወደፊቱን መተንበይ ይቻላል፡፡ አእምሮ ውሸት አይናርምና፡፡ የ60 ትውልድ ትሩፋት የሆነው የብሔረሰብን ጥያቄን በሚል አቶ መለስን ጨምሮ ብዙ የ60ዎቹ የሚመሩት ኢሕአዴግ በፖሊሲ አስፍረው የጎሳ ፌደራሊዝም የተገበሩት ፖሊሲ ቆይቶ ችግር ሊሆን እንደሚችል ተናጋሪው ከመጠቆምም አልፎ እየደጋገመ አስጠንቅቋል፡፡ ይህ ተናጋሪ እንደ 60ዎቹ ትውልድ የማንነት ጥያቄና የበታችነት ስሜት ፈጽሞ አይታይበትም፡፡ የሚናገረው በሙሉ ልብና ፍጹም በተረጋጋ ሁኔታ ፊት ለፊት ነው፡፡ በብሔረሰብ ሥም የተደራጁ አሸን የሆኑት የፖለቲካ ድርጅቶቻችን መሪዎች አሁንም ልክ ነን ይሉናል፡፡ እረ እንደውም የዚሁ የ50-60ዎቹ ምሁራንም እንዲሁ እንደሚያስቡ እናደምጣለን፡፡ በኤሰቢኤስ ራዲዮ የሰማናቸው ፕ/ር ገብሩ ታረቅ በጎሰኝነት ላይ የተመሠረተውን የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም አሁን ሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ ለአገሪቱ ያበረከተው ትልቅ ለውጥ ሲሉ ኢሕአዴግን ያወድሉ፡፡ ኢሕአዴግ አሁን የገጠሙት ፈተናዎች መሠረቱ ይህን የመሠለ የፌደራል ሥርዓት ዘርግቶ ሥርዓት ላይ አለማዋሉ ነው ሲሉ ይመክራሉ፡፡ ገብሩን በወቅቱ ስለሰጡት ቃለ መጠይቅ ብዙ ቦታ እንደወደድኩላቸው ባለፈው ጽሑፌ ተናግሬአለሁ፡፡ የአገርና ሕዝብ አደጋ ሆኖ የሚታየውን ብሔርን መሠረት ያደረገውን ኢትዮጵያን የበከፋፈለ የኢሕአዴግን ፌደራሊዝም ማወደሳቸው ግን መስሏቸው ነው ብሎ ለማለፍ እንኳን ይከብዳል፡፡ ገብሩ ምሁር ናቸው፣ በዚህ ላይ ሂደቱን የሚያስተውሉና የሚከታተሉ የታሪክ ምሁር፣ ከዛም በላይ አሁን እየሆነ ያለው ነባራዊ እውነታ ምስክር ሆኖ ሁሉ በግልጽ የሚረዳውን ችግር ሆን ብለው የሕዝብን ግንዛቤ ለማንሻፈፍ ምሁርነታቸውን ተጠቅመው የተናገሩት እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ ከተሳሳቱ ችግር የለውም፡፡ እኔም አሁንም አላለሁ ገብሩ ተሳስተዋል፡፡ ሆን ብለው ከሆነ ግን ይቅርታ እንዲጠይቁንም እፈልጋለሁ፡፡ ካለሆነ እባብ ሞኝን ሁለት ጊዜ ነደፈው አንዴ ሳያውቅ ሌላ ጊዜ መንገድ ከጓደኛው ጋር ሲሄድ የነደፈኝ ነገር ይሄ ነው ብሎ  ተጠቅልሎ የተኛውን እባብ በጣቱ እይነካ ለጓደኛው ሲያሳይ ነደፈው ይባላል፡፡ ከላይ የምታዩት ተናጋሪና ብዙ ሌሎች ቀድሞም ሊሆን የሚችለውን በደንብ እንረዳው ነበር፡፡ ዛሬ ግን በአየን የሚታየውን እውነት ሁሉም ይረዳዋል፡፡
የኢሕዴግና ደርግ የ60ዎቹ ትውልድ ሥርዓት ተደምሮ ዛሬ ንጉሱ መሪ ከሆኑባቸው 43 ዓመት ጋር እኩል ሆኗል፡፡ በአገር ላይ ያመጡት እድገት ግን የንጉሱን ዘመን ያሕል አይደለም፡፡ ይህን ሥል አሁንም እንዳይንሻፈፍ ኢሕአዴግ ብዙ ለውጥ እንዳመጣ ይታሰባል በእርግጥም ከደርግ በተሻለ ለውጥ ለማመጣቱ አያከራክርም፡፡ ከንጉሱ ዘመን ጋር ግን ሲወዳደር ለውጡ ደካማ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ልብ በሉ ንጉሱ ከምንም ተነስተው ብዙ ዛሬ ድረስ የምናያቸውን ዘመናዊ ልማቶች እንደሰሩ እናስተውል፡፡ አዋሳና ባሕርዳርን ጨምሮ ሌሎች ከተሞች ንጉሱ የመሠረቷቸው ብቻም ሳይሆን በዘመናዊ ፕላን እንዲያድጉ መሠረት ጥለዋል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ዛሬ ድረስ ውብ ሆነው የምናያቸው ሕንጻዎች በንጉሱ ዘመን የተሠሩ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ብዙ ሰው የሚያደንቀው የኢሕአዴግ ዘመን የአዲስ አበባ ሕንጻዎች ምን አልባትም ለወደፊት የከተማው ችግር እንዳይሆኑ እሰጋለሁ፡፡ ጥንካሬአቸውና ሌላ ጥራታቸው በእድሜ ብዛት የሚያደረሰው ጉዳት እንዳለ ሆኖ እየተጠቀሙት ያለው መስታወት ጨረሮችን ወደሕዝብና አካባቢው በመርጨት ለጤና አልፎም እጽዋትን ጨምሮ ሌላ ሕይወት ላይ አደጋ ሊሆን ይችላል ሲሉ የሚያስጠቅቁም አሉ፡፡ መስታወት መሆኑ ሳይሆን የመስታዎቶቹ ጥራት ደረጃ ነው፡፡ የሕንጻዎቹን ጥራት ግን አሁንም ሰንበት ባሉት እያየንው ያለ ነው፡፡ በንጉሱ ጊዜ የተሰሩት ዘመን አልፎ ዛሬም ድረስ ውበታቸውን እናደንቃለን፡፡ ዛሬ የሚሰራው ግን ከ10 ዓመት በኋላ ብናየው መስታወቶቹ ረግፈው፣ ግድግዳው ተንዶ ሊታይ ሁሉ ይችላል፡፡ በዚህ ላይ ብዙዎቹ ፕላናቸው ራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ ለማስተዋል የብሔራዊ ባንክን ጨምሮ፣ ፖስታ ቤትን፣ ለገሀር፣ መስቀልአደባባይ አራት ኪሎ፣ መዘጋጃ ቤት የመሳሰሉትን የንጉሱን ዘመን ሕንፃዎች አስተውሉ፡፡
ሌላው አድስ አበባ ውስጥ በቅርብ በቻይና ከተበረከተልን የጥሩነሽ ዲባባ ቤጂንግ ሆስፒታል ውጭ ሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች መንጉሱ የተሰሩ መሆኑን ስንቶቻችን ታዝበናል;
ከአዲስ አበባ ውጭም የዘመናው የግል እርሻዎችን ጨምሮ ብዙ ልማቶች በንጉሱ ዘመን የተሳካላቸው ነበሩ፡፡ አሁንም ደርግን ልረሳው ነው፡፡ ምን እንደሰራም አይገባኝም፡፡ ኢሕአዴግ በተለይ ከ10ዓመት በኋላ ብዙ መንገድንና የጤና ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ጥሩ ለውጥ አምጥቷል ከሚሉት ነኝ፡፡ ከዜሮ ከተነሱት ከንጉሱ ጋር ግን ሲወዳደር ብልጫ ካለውም ብዙ የሚባል አይመስለኝም፡፡ በመንገድ ግን ግልጽ የሆነ ብልጫ አለው ባይ ነኝ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አስመልክቶ አሁን ቁጥሩ እምርታ ያለው ቢሆንም ብዛቱን በቅርብ ነው የሠራቸው፡፡ መገንባታቸው መልካም ሆኖ ዕቅድ ላይ ተመስርቶ ለመሆኑ እጠራጠራለሁ፡፡ ኢሕአዴግ ልማት የሚሰራው የአገራዊ ኃላፊነት ግዴታው እንደሆነ  አውቆ ሳይሆን የሄን ሠራሁ፣ ይሄን አደረኩላችሁ በሚል ለምርጫ ወይም ለመወደስ ነው የሚመስለው፡፡ ይህ አገርና ሕዝብን የማይወክለው 60ዎቹ ትውልድ አይነተኛ ባሕሪው ነው፡፡ ትንሽንም ትልቁንም እያጋነነ ማውራት ያበዛል፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ማለት እንዳልሆነ ማሰብ የሚችሉ ባለስልጣናት የሉትም፡፡  በዚሁም ምክነያት ሥራዎች ታቅደው አይሰሩም ወጫቸውም ከተፈጥሮ ወጭያቸው በላይ ነው፡፡  ዛሬ ጥራታቸው ባይሟላም ግን መሠራታቸው በራሱ ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡
ይህ ሁሉ ማወዳደር ግን እዛው እዛው እንጂ ኢትዮጵያን ከሌላ አገር ጋር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ከሌሎች ጋር በሚለው ስንመጣ የንጉሱ ዘምን አገሪቱን ከብዙ ዛሬ በኢኮኖሚ አልፈዋት ከሄዱ በላይ የሚያሰፍር ነው፡፡  እንደውም ኢትዮጵያ በንጉሱ ዘመን ከአፍሪካ አገራት ጋር ሳይሆን ትልቅ ሥም ካላቸው እንደ ጃፓን ካሉ አገራት ጋር አኩል የሆነችበትም ወቅት ነበር፡፡ እርግጥ የጃፓን ኢኮኖሚ በሁለተኛው አለም ጦርነት ወድሞ ነው፡፡ አፍሪካ አገራት በወቅቱ አብዛኞቹ ቅኝ ስለነበሩ መወዳደርም አይችሉም፡፡ የሆነ ሆኖ አገሪቱ አሁን ካለችበት በተሻለ በኢኮኖሚ ከአለም አገራት ተወዳዳሪ እንደነበረች አይካድም፡፡ ደርግ ይውደም እያለ ሁሉንም ማወደም ነበር፡፡ በኢሕዴግ የመጣብን ልክፍት ደግሞ እድገቱ ባይካድም ግነቱ አሁን እያሳፈረን መጥቷል፡፡ ኢሕአዴግ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በየአመቱ በሁለት ዲጂት እያደገ መሆኑን ለ10 ዓመታት ቢያወራም አገሪቱ አንድም እከሌ የምንለውን አገር በኢኮኖሚ ስትበልጠው አልሰማንም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደውም ሌሎችም አዎ እያሉ እኛው የምንነግራቸውን ይሁንላችሁ አይነት ይነግሩናል፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ራስን ከመግደል አሳንሼ አላየውም፡፡ የአገር እድገት በሕዝብ አኗኗር ላይ እራሱ በሚፈጥረው መገለጥ ይታያል፡፡ አሁን የደረሰብንን ድርቅ ጨምሮ አገሩን እየለቀቀ  በሞት በረሃዎች ሳይቀር የሚሰደደውን ዜጋ፣ በብዙ የአገሪቱ ነዋሪዎች የሚታየውንደ ድህነት መረዳት የማይችሉ ራሳቸው በዘረፉት የአገርና ሕዝብ ንብረት የደለቡ የ60ዎቹ ትውልድ ባለስልጣኖችና አባሮቻቸው እድገቱን የሚያዩት በራሳቸው ኑሮ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡
በአጠቃላይ በእኔ ግንዛቤ ያ የ50-60ዎቹ ትውልድ ብዙ አስተሳሰቡ የግል ምኞትና ጥቅም ያየለበት፣ ካልሆነም ሌሎችን መሆን የሚናፍቅ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የማይወክል አስተሳሰብ ያለው ነው ባይ ነኝ፡፡ አሁንም ቢሆን ተቃዋሚም በሉት ገዥው ፕለቲካ የሚመራው በዚህ ትውልድ መሆኑ የአገርና ሕዝብ ጉዳይ መፍትሔ አለማግኘቱ ሳያነስ ከግዜ ወደጊዜ እከፋ መሄዱ አሳሳቢ ነው ባይ ነኝ፡፡ ዛሬ 25 ዓመት የሆነው ትውልድ ደግሞ የ60ዎቹ ትውልድ ያመረተው እንደሆነ ጭምር ሳስብ ስጋቴ የጎላል፡፡ በመሀል ያለው ተውልድ የተሻለ ይሆን; ይህ የእኔ ሐሳብ ነው ሌሎችስ ምን ይላሉ;

እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ሕዝቦቿን ይጠብቅ! አሜን!

ሰርጸ ደስታ

No comments:

Post a Comment

wanted officials