መንግስት ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከአትላስ ኩባንያ ከተወሰደ በኋላ በኩባንያው ስር የነበሩ የባለሃብቶች ድርሻ ማሽቆልቆሉ ተገለጸ
ኢሳት (ግንቦት 18 ፥ 2008)
በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግስት ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ከቁጠባ ሂሳቡ እንደተወሰደበት ያስታወቀው የብሪታኒያው ኩባንያ ድርጊቱን ተከትሎ በኩባንያው ስር ለኢንቨስትመንት ፍላጎት የነበራቸው ባለሃብቶች ድርሻ ማሽቆልቆሉ ገለጸ።
ይኸው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በሽርክና በብርጭቆ ማምረት ላይ ተሰማርቶ የነበረው ኩባንያ በስሩ ኢንቨስት በማድረግ ፍላጎት የነበራቸው አካላት ድርሻ ከ30 በመቶ መቀነሱን ይፋ አድርጓል።
አትላስ አፍሪካ የተሰኘው ኩባንያ በሽርክና አብሮት የሚሰራው ድርጅት ከዚህ ቀደም ከታክስ ክፍያ ጋር በተያያዘ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ውዝግብ ውስጥ መቆየቱን አውስቷል።
ይሁንና፣ ኩባንያው ሽርክናውን ከጀመረ በኋላ የታክስ ክፍያው እሱን እንደማይመለከተው መግባባት ቢኖርም፣ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በህገወጥ መንገድ 2.4 ሚሊዮን ዶላርን ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሂሳቡ ውስጥ መውሰዱን አመልክቷል።
በኩባንያውና በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎም በኩባንያው ስር በሃገሪቱ ኢንቨስት ለማድረግ የነበራቸው አካላት እምነት ማጣታቸውንና ድርሻውም 30 በመቶ እንደቀነሱ ድርጅቱ በድረገጹ ላይ አስፍሯል።
በህገወጥ መንገድ ተወስዶብኛል ያለውን ገንዘብ ለማስመለስም፣ ኩባንያው ፖለቲካዊና ዲፕሎማቲክ አማራጮችን እየወሰደ መሆኑንም በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።
አትላስ አፍሪካን ኢንተርፕራይዝ ሃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ቲፕ [TEAP] ከተሰኘ ሃገር በቀል ኩባንያ ጋር ሽርክና በመግባት ለዳሽን ቢራ ብርጭቆዎችን እያመረተ እንደሚገኝ ታውቋል።
በሌሎች ተመሳሳይ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንደነበረው የገለጸው ኩባንያው 2.4 ሚሊዮን ዶላሩ ከመንግስት ጋር ተደርጎ የነበረን ስምምነት የሚሰጥ ተግባር እንደሆነም አክሎ አመልክቷል።
የኩባንያውን ቅሬታ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን ድረስ የተሰጠ ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ኩባንያው የተለያዩ አማራጮችን እየተከተለ እንደሆነም አመልክቷል።
No comments:
Post a Comment