Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, May 31, 2016

ሲውዲናዊቷ የኢትዮጵያውያን መብት ተሟጋች ሜሎዲ ሰንድበርግ (በማህሌት ፋንታሁን) Melody the Swedish Human right Activist for Ethiopia

በማህሌት ፋንታሁን
የመጀመሪያ ዲግሪዋን ሳይኮሎጂ ነው ያጠናችው። ከዛ በኋላም የህክምና ሳይንስ በተለይም የአእምሮ ህክምናን ተምራለች። በሙያዋም የአእምሮ ህሙማንን በማከም ታገለግላለች። በአለም ላይ በእስር ለሚገኙ ዘጋቢዎች እና ፎቶግራፈሮችን በገንዘብ ለመደገፍ የተቋቋመው ቃሊቲ ፋውንዴሽን የቦርድ አባል ናት። የመሳል፣ ፎቶግራፍ የማንሳት እና የመፃፍ ድንቅ ተሰጥኦ አላት -ስዊድናዊቷ ሜሎዲ ሰንድበርግ (Melody Sundberg)። ሜሎዲ የ27 አመት ወጣት እና ባለትዳርም ናት።
Melody Sundberg, Founder of Untold Stories
ስለ ሜሎዲ መጀመሪያ ያወቅኩት እስር ቤት ሆኜ ነው። የኔን እና ሌሎች አብረውኝ የታሰሩ ጓደኞቼን እንደሳለችን (sketch እንዳደረገች) እና ስእሎቹም በማህበራዊ ሚዲያ በሰፊው እየተሰራጩ መሆናቸውን ከቤተሰቦቼ ሰማሁ። በወቅቱ የተሰማኝን ስሜት በቃላት ማስቀመጥ ይከብደኛል። የህሊና እስረኛን ከሚጠቅሙነገሮች አንዱ አለመረሳት/ መታወስ ነው። እኛም እንዳንረሳ በየጊዜው በምትለቀው ፅሁፎቿ እና ስእሎቿ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጋለች። ከእስር ከወጣሁ በኋላ ከሜሎዲ ጋር በኢንቦክስ ስናወራ ህልም ህልም ነው የመሰለኝ። ከገፀ-ባህሪ ጋር የማወራ አይነት ነገር። እርግጠኛ ነኝ እየጮኸችላቸው ያሉ አሁን በእስር ያሉ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም የህሊና እስረኞች ተፈተው ከሜሎዲ ጋር የሚያወሩበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።
እኛ ከተፈታን በኋላም ስራዋን ቀጥላለች ሜሎዲ። Untold Stories [http://www.untoldstoriesonline.com] በሚል ድረ ገፅ እና የፌስቡክ ፔጅ ተነግሮ የማያልቀውን በኢትዮጵያውያን ላይ በገዛ መንግስታቸው የደረሰባቸውን/እየደረሰባቸው ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እና በደል ለአለም እያሰማች ነው። ያልተነገሩ እና ያልተሰሙ ታሪኮችን ቋንቋና ባህል ሳይገድባት መረጃዎችን አድና ማግኘቷ በጣም ይገርመኛል። ስለ ሜሎዲ ስራዎች እንዲ ባጭሩ ተወርቶ የሚያልቅ አይደለም። ባጭሩ ሜሎዲ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ከምንል ኢትዮጵያውያን በላይ ስለኢትዮጵያውያን መበደል እና መጨቆን እያጋለጠች የምትገኝ፤ ምስጋና እና ክብር የሚገባት ድንቅ ሰው ናት ።
ውዷ ሜሎዲ እነሆ የከበረ ምስጋናዬ ይድረስሽ! ያሰብሽው ሁሉ ይሳካልሽ!

No comments:

Post a Comment

wanted officials