Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, May 11, 2016

ሰበር ዜና – የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ: ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለፓትርያርኩ የጻፈውን ጽሑፍ በማተሙ በጠቅ/ቤተ ክህነቱ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ተከሠሠ

 ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለፓትርያርኩ የጻፈውን ጽሑፍ በማተሙ በጠቅ/ቤተ ክህነቱ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ተከሠሠ


Daniel Kibret Views on Sendek
  • ከስም ማጥፋት ወንጀል በተጨማሪ የ100 ሺሕ ብር የፍትሐ ብሔር ክሥ አቤቱታም ቀርቧል
  • ግንቦት 17 እና 26 ቀን በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት ይቀርባል
  • የሕግ አገልግሎት መምሪያው የጉዳዩ አያያዝ እና የክሡ አቀራረብ ጥያቄ አሥነስቷል
*                *                *
ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ለማረጋገጥ እንደተቻለው፤ የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፥ ማክሰኞ፣ ግንቦት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዋና ሓላፊ አማካይነት የክሥ ጽሕፈቱ ደርሶታል፡፡
በክሥ ጽሕፈቱ እንደተገለጸው፥ ከሣሹ፣ የሕግ አገልግሎት መምሪያው ዋና ሓላፊ እና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ወኪል አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት ሲኾኑ፤ ተከሣሹ ደግሞ፤ የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ ናቸው፡፡
የክሡ ምክንያት፣ ጋዜጣው በ11ኛ ዓመት ቁጥር 551 ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. እትሙ፣ “ፓትርያርኩ፡- ለኢትዮጵያ የደኅንነት፣ ለምእመናን የድኅነት ሥጋት” በሚል ርእስ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተጻፈውን ጽሑፍ እንዲታተም በመፍቀዱ እና በማተሙ እንደኾነተጠቅሷል፡፡
በ2000 ዓ.ም. በወጣው የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ዐዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 43(7) መሠረት የቀረበ መኾኑ በተገለጸውየወንጀል ክሥ፤ ጋዜጣው በተጠቀሰው እትም ገጽ 20፤ በ1996 ዓ.ም. በወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 43(1)(ሀ) እና 613(3) ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ አሠራር ጥላሸት የሚቀባ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ፓትርያርክ ስም የሚያጠፋ እንዲኹም በመልካም ስም እና ዝናቸው ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ ሕዝበ ክርስቲያኑ የቤተ ክህነቱን ተቋማዊ አሠራር እንዳይቀበል ለማድረግ ኾን ተብሎ የተጻፈ እንደኾነ ተገልጧል፡፡
ጽሑፉን በስድስት ነጥቦች በመክፈል ተፈጽሟል ያለውን የስም ማጥፋት ወንጀል ዝርዝር ሲያስረዳም፡-
  1. “… ምእመናንን የሚያጸና ጉባኤ ሊዘጋጅ ነው ሲሏቸው፤ ሕዝቡ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጣ ነው ሲሏቸው፤ ወጣቱ ትውልድ ቤተ ክርስቲያኑን ለማገልገል እየተጋ ነው ሲሏቸው፤ ዲያስጶራው ሕዝብ በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ሆነ ሲሏቸው፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚገልጥ ዐውደ ርእይ ሊዘጋጅ ነው ሲሏቸው፤ መንፈሳዊ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ሊቀርብ ነው ሲሏቸው ያን ጊዜ ብዕራቸውን ይዘው ለማገድና ለመክሠሥ ይነቃሉ፡፡ የፓትርያርኩ ብዕር ግን ምእመናንን የሚያጽናና ጦማር ለመጻፍ የሚጨበጥ አይደለም፡፡ እንደ ጠንቋይ ብዕር ለማፍዘዝና ለማደንገዝ እንጂ፡፡” በማለት በተቋሟ የሚጻፉ ደብዳቤዎች ተቀባይነት እንዳይኖራቸው በመቀስቀስ፤
  2. “የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ የገዛ ልጆችዎን ያወያዩ ሲሏቸው በራቸውን ጠርቅመው የሚዘጉ ፓትርያርክ በታሪክ የሚጀመሪያው መኾን አለባቸው፡፡ በሱራፊ ነበልባል የተዘጋች ገነት ስትከፈት በፓትርያርክ የተዘጋች የቤተ ክህነት በር ልትከፈት አልቻለችም፡፡”በማለት የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ አስተዳደር እንደተዘጋና ህልውና እንደሌላት በማስቆጠር ሐሰተኛ ወሬ በመንዛት፤
  3. “ዐውደ ርእዩ የማይደረግበት በቂ ምክንያት ከነበረ ቢያንስ ከሳምንት በፊት መግለጥ ይቻል ነበር፡፡ ዓላማው ግን ማበሳጨት፣ ዐመፅ ማስነሣት፣ ተስፋ ማስቆረጥና ምእመናንን ወደማይፈልጉት መሥመር መውሰድ ነው፡፡” በማለት በመንግሥታዊ አሠራር የታገደን ዐውደ ርእይ በቤተ ክህነቱ የታገደ አስመስሎ በማቅረብ ሕዝበ ክርስቲያኑን ለዐመፅ ለማነሣሣት ስውር ቅስቀሳ በማድረግ፤
  4. “የዚኽች ሀገር ሰላም አይፈለግም? ምእመናን ሀገር እንደሌላቸውና መብት እንደሌላቸው ራሳቸውን እንዲቆጥሩ ይፈለጋል? ‹ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል› እንዲል ሀገሪቱ ያለባት ችግር አይበቃትም? ተጨማሪ ችግር ማምረት ይፈለጋል?” በማለት ሀገሪቱን ሰላም አልባ አድርጎ ከመቁጠሩም በላይ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሀገር ደኅንነት ስጋት አድርጎ በመሣል፤
  5. “እውነት መንግሥት በስሙ የሚሠራውን ያውቀዋል፤ ካወቀውስ ዝም ይላል? ቤተ ክህነቱ በሚያመጣው ዳፋ መከራ ለመቀበልስ ዝግጁ ነው?” በማለት የቤተ ክህነቱን አጠቃላይ መልካም ስም እና ዝና ጥላሸት በመቀባት፤
  6. “የገዛ ፓትርያርካችን ለእኛ ለምእመናን ድኅነትን እንዳናገኝ ስጋት ኾነውብናል፡፡ የታገሡትን ኹሉ ለክፋት በማነሣሣት ደግሞ ለሀገሪቱ ደኅንነት ሥጋት እየኾኑ ነው፡፡” የሚል ይዘት ያለው ጽሑፍ እንዲታተም በመፍቀድ እንዲታተም ያደረገ በመኾኑ በፈጸመው የስም ማጥፋት ወንጀል መከሠሡን ያትታል፡፡
Ferew Abebe, Editor-in-chief
ሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ
የክሥ መጥሪያውም፤ ዋና አዘጋጁ ግንቦት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ኹለተኛ ወንጀል ችሎት ጠዋት 3፡00 ላይ እንዲቀርብ ማዘዙ ታውቋል፡፡
የሕግ አገልግሎት መምሪያው፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣“የዳንኤል እይታዎች” በተሰኘው የጡመራ መድረኩ(ብሎጉ) ለመጀመሪያ ጊዜ ዓርብ፣ መጋቢት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. የጦመረውን ጽሑፍ፣ ጋዜጣው በመጋቢት 21 ቀን እትሙ ቀድቶ በማውጣቱ ተፈጽሟል ባለው የስም ማጥፋት ወንጀል የብር 100‚000(አንድ መቶ ሺሕ ብር) የኅሊና ጉዳት ካሳ እንዲከፈለው ይወሰንለት ዘንድ የፍትሐ ብሔር ክሥም አቅርቧል፡፡
“በጥንታዊ እና ታሪካዊ እንዲኹም የሀገር ውለታ በኾነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ ለተፈጸመብን የስም ማጥፋት እና ክብረ ነክ ስድብ፣ በዐዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 41(1) እና (2) መሠረት ክቡር ፍ/ቤቱ ተመጣጣኝ እና አግባብነት ያለው የኅሊና ጉዳት ካሳ ብር 100‚000 እንዲከፈለን እንዲወስንልን እንጠይቃለን፡፡” ይላል – በቁጥር ሕ/አ/47/08 በቀን 18/08/08 ዓ.ም. ለፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት የቀረበው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሕግ አገልግሎት መምሪያ የክሥ ማመልከቻ፡፡ ጋዜጣውንና ኹለት የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ሠራተኞችም በሰነድ እና በሰው ማስረጃነት ጠቅሷል፡፡
የጋዜጣው ዋና አዘጋጅም፣ ክሡን ለመስማት ግንቦት 18 እና መልስ ለመስጠት ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ 2ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ረፋድ 4፡00 ላይ እንዲቀርብ መታዘዙ ታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials