ከጠዋቱ ጤዛ እስከ ምሽቱ ቁር
አንጋው ተገኝ በሠላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ያለ ወጣት ነው። ፀጉሩን ያጎፍራል። ሲናገር በብዙ ነገሮች እየተደነቀ ነው። አንጋው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የሰሜን ጎንደር አብረሃ ጅራ ወረዳ ኃላፊ በመሆን እጅግ ፈታኝ ጊዜያትን አሳልፏል። የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የሀገሪቱ ክፍሎች መንቀሳቀስ የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ መሆኑን ደጋግሞ ይናገራል። የፓርቲው አመራር ሁኖ በሠራበት ወቅት ፓርቲ ስብሰባ እንኳን ማድረግ እጅግ ከባድ መሆኑን ያስታውሳል። ፖሊስና የደኅንነት ኃይሎች አመራሮቹን እየተከታተሉ ሲያስጨንቋቸው ‹የፓርቲው ሥራ ከሚቆም በሚል አንገረብ ወንዝ ወርደን እየዋኘን እንሰበሰብ ነበር› ይላል። እየዋኘን ሰው ወደኛ በመጣ ቁጥር እየተበታተንን፤ ሰው ራቅ ሲልልን ደግሞ እዛው ውኃው ውስጥ ሰብሰብ ብለን እየተንሳፈፍን ነበር ስብሰባ የምናደርገው የሚለው አንጋው በፓርቲ እንቅስቃሴ ምክንያት ስድስት ጊዜ ከሥራ ተባሮ ስድስት ጊዜ መመለሱን ሲገልጽ አንዳንዴ በሕይወት መቆየቴም ለኔ ግርም ይለኛል እያለ ነው። ይባስ ብሎ በሠላማዊ ትግል ቆርቦ በዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የነበረው አንጋው ተገኝ የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ሳይቀርብበት አሁን ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት አለህ በሚል ምክንያት በመጨረሻ ለእስር የተዳረገ ሲሆን፤ እስር ቤት ሁኖም የታገለለትና የደከመለት አንድነት ፓርቲ ሲፈርስና በእሱ አባባል ‹መፈንቅለ አመራር› ሲካሄድበት ተመልክቶ ያዝናል። ለዚህ ሁሉ መሆን አንጋው ተጠያቂ የሚያደርገው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን ነው። ‹ሕግ የማይገዛው መንግሥት› እያለ ሁሌም ይገረማል። ይህ የኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ችግር የገዥው ፓርቲ ቅጥ ማጣት ነው ከሚሉት ወገን የሚቀርበው ሐሳብ ትክክለኛ ተምሳሌት ነው።
ከዚህ አሳዛኝ ኹነት መለስ ብለን አርብ ሚያዚያ 28፣ 2008 ከጠዋቱ 4፡30 እስከ 5፡30 ድረስ በአንድ ሰዓት ውስጥ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጆች ለጽሑፉ ግብዓት የሚሆን መረጃ ለማግኘት በማሰብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ መሠረት እንዲሁ አለፍ አለፍ እያልን በአሁኑ ወቅት በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ከሚገኙ ሰባ አምስት ፓርቲዎች መካከል የሃያ አምስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች የስልክ አድራሻ ላይ ስልክ የደወልን ሲሆን፤ ከሃያ አምስቱ ሙከራዎች መካከል ሁለቱን ስልኮች ያነሱልን ሕፃናት ሲሆኑ፣ የሰባቱ ስልክ ቢጠራም አይነሳም፤ የዐሥራ አምስቱ ስልክ ደግሞ ከነአካቴው የማይሠራ ሲሆን፤ የአንዱ ብቻ ማለትም ‘የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሕብረት’ ስልክ ላይ የፓርቲውን አመራር ልናገኝ ችለናል። በተመሳሳይ ጊዜ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያደረግነው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪም ስልኩ ሊነሳ ባለመቻሉ ማብራሪያ ማግኝት አልቻልንም። እንግዲህ ‹የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ሰሞን ግርግር ከመፍጠር ያለፈ ምንም አይፈይዱም የሚለው ሐሳብ እንዲሁ ያለውን ሁኔታ ቀረብ ብሎ ካለማየት የሚመጣ ነው› የሚሉ ተችዎችም ሁሌም የሚፈተኑበት ጉዳይም ይሄው ተቃዋሚ ፓርቲ ተብለው የተመዘገቡት ፓርቲዎች በሚገባቸው ቦታ አለመዋላቸው ነው። ፓርቲዎቹ የስልክ እንኳን አድራሻ የሌላቸው/ቢኖራቸው እንኳን የማይሠሩ ስልኮችን ይዘው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የለውጥ መሠረት ይሆናሉ ብሎ ማሰቡንም ያከብደዋል። ይህ ደግሞ ተቃዋሚዎች የራሳቸው ሥራ ሳይሠሩ ገዥውን ፓርቲ ማውገዛቸው ተገቢ አይደለም የሚለው ሐሳብ ተምሳሌት ነው።
የጠዋቱ ጤዛ
‹የፓርቲ ፖለቲካ ማለት በሕግ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን አደራጅተው ለምርጫ የሚያደርጉት ትግል ነው› የሚለው ጠቅለል ያለ ትርጉም በኢትዮጵያ ፖለቲካ አኳያ ይሠራል ማለት ከባድ ነው። ከተመዘገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች በማይተናነስ መልኩ የራሳቸው ፍላጎት እና ዓላማ ያላቸው ብዙ ቡድኖች ራሳቸውን የፖለቲካ ፓርቲ ብለው ሰይመው የሚንቀሳቀሱ ከመሆናቸው አንፃር የፓርቲ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ዐውድ አንፃር ለምርጫ የሚደረግ ሠላማዊ ትግል ነው ከሚለው ትርጉም ፈቅ ያለ መሆኑንም ነው እነዚህ ፓርቲዎች የሚያስረዱን።
በቡድን ተደራጅቶ የፖለቲካ ፓርቲ የሚባል ድርጅት ፈጥሮ መንቀሳቀስ የተጀመረው ኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ ሞዴል (Party Political Model) የፖለቲካ ሒደት ከመጀመሯ ብዙ ቀደም ብሎ እንደሆነ የተለያዩ ጸሐፊዎች ያመላክታሉ። ከጣሊያን የአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በተለይም ውጭ አገር ቆይተው የተመለሱ ኢትዮጵያዊያን በአውሮፓና በአሜሪካ ካዩት አሠራር በመነሳት የፓርቲ አደረጃጀት ኑሮ ፖለቲካው በዛው መሥመር እንዲቃኝ መፈለጋቸው አልቀረም። ዘውዴ ረታ ‹የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት› ባሉት መጽሐፋቸው በመጋቢት 1939 ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው ስለ አገራችን ጠቅላላ ሁኔታና ስለ እኛ አመራር ሐሳባችሁን አቅርቡልኝ ባሉት መሠረት በወቅቱ የጽሕፈትና የሀገር ግዛት ሚኒስትርነትን ደርበው ይዘው የነበሩት ጸሐፊ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ከሦስቱ የማሻሻያ ሐሳብ አቅራቢዎች መካከል አንዱ ነበሩ። በወቅቱ ወልደጊዮርጊስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት እየተንቀሳቀሱ ነው የሚል ሐሜት ይሰማባቸው ስለነበር ይሄን ሐሜት “እኔና አቶ መኰንን [ሀብተወልድ] እየተግባባንና እየተረዳዳን በመሥራታችን የፖለቲካ ፓርቲዎች በመሆናቸው ነው እየተባለ የሚነገርብን ደህና አድርገን እናውቀዋለን። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚያውቁት፤ የፖለቲካ ፓርቲ በአገራችን የለም።” በማለት ካስተባበሉ በኋላ ስለፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት ሲያስረዱ “እኔ በዚያ በመከራው የስደት ዘመን እንዳየሁት፤ ዛሬ በአለንበት ሰዓት ለኢትዮጵያ አስተዳደር እንደ እንግሊዝ አገር፤ ንጉሥ የታሪክና የባሕል የበላይ ጠበቂ ሆኖ ይነግሳል፤ መንግሥት ደግሞ በፓርላማ ሕዝብ ቀጥታ ከመረጠባቸው እንደራሴዎች መካከል በፖለቲካ ፓርቲ አሸናፊ የሆነው ይመረጣል፤ የሚለውን ሐሳብ ወስዶ መጠቀም ይቻላል ብዬ አላምንም። እንደ እንግሊዝ አገር መሆን እንችላለን ብሎ ማሰብ፤ አቅምን ካለማወቅ የተነሳ በሸንበቆ ላይ እንደሚገነባ ምኞት የሚቆጠር ይሆናል” በማለት ነበር። ይህ ሐሳብ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ሃያ ሰባት ዓመታት ንጉሠ ነገሥቱ የፖለቲካ ፓርቲ የሚባለውን አደረጃጀት በጥርጣሬ እንደተመለከቱት ከመንበራቸው ሳይወዱ በግድ ተወገዱ። በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋምም ሆነ የፓርቲ ፖለቲካን ለማካሄድ የሚያስችል ምንም ዓይነት የሕግ ማዕቀፍም ሆነ ቀናነት ያልነበረ ቢሆንም የፓርቲ ቅርፅ ያላቸው አደረጃጀቶች በተለይም በመጨረሻዎቹ የንጉሡ አምስት የሥልጣን ዘመናት አቆጥቆጠዋል። አንትሮፖሎጅስቱ ዶ/ር ወንድወሰን ተሸመ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲ የዛሬ ሃምሳ ዓመት በ1958 የተመሰረተው ‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ካውንስል› ነው የሚሉ ሲሆን፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እዚህም እዚያም ማቆጥቆጥ የጀመሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሲወጡና ሲወርዱ ቆይተዋል።
ከንጉሠ ነገሥቱ ስርዓት ማብቃት ጋር ተያይዘው ብቅ ብቅ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በግራ የፖለቲካ አስተሳሰብ የተቃኙና በፍጥነት ወደመጠፋፋት በመዝለቃቸው ተስፋ የተደረገበትን የፓርቲ ፖለቲካ አካሔድ እዛው ካለበት ላይንቀሳቀስ ተተክሎ ቆይቶ ከኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ወደ ሥልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ አዲስ ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ማደሩ አልቀረም። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ከሚወደስባቸው ጉዳዮች አንዱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን (multi-party system) በሕግ ተቀብሎ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጋዊ ዕውቅና የሚሰጥ ስርዓት መዘርጋቱ ነው።
የሃምሳ ዓመታት የሙከራ ታሪክ፤ የሃያ አምስት ዓመታት ሕጋዊ ዕውቅና ያለው የፓርቲ ፖለቲካ ከዕድሜው አንጻር ምን ትርፍ አመጣ? ለምንስ ፈተናና እክል በየቀኑ እያጋጠመው ይወድቃል የሚሉት ጥያቄዎች መሠረታዊና የወደፊቱን ለመረዳት የሚረዱ ናቸው። በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ እንዳያብብ እና እንዲቀጭጭ ምን እክል አጋጠመው? ለሚለው ጥያቄ አንድ ዓይነት ምላሽ መስጠት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም እንደ መላሾቹ የተለያ መልሶችን እናገኛለን።
ዴሞክራሲ የማያበቅል መሬት?
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሒደት በቅርበት የሚከታተሉ ምሁራን ለፓርቲ ፖለቲካ ስኬት ማጣትና ብሎም ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይደረጅ መሠረታዊውን አስተዋፅኦ ያደረገው የመጠላለፍና አምባገነኖችን የሚያበቅል የፖለቲካ ባሕል መኖሩ ነው ይላሉ። በኢትዮጵያ ላይ ብዙ ጥናት ያደረጉት ጆን ያንግ በዐሥር ዓመታት ልዩነት በኢትዮጵያ የፓርቲ የፖለቲካ ሒደት ላይ በጻፏቸው ሁለት ጽሑፎቻቸው ላይ ለኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካና ዴሞክራሲ ዋነኛ እክል አድርገው የሚያቀርቡት በኢትዮጵያ ያለውን ከመንግሥታዊ መዋቅሩ ውጭ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ተቋም እንዲፈጠር ያለመፍቀድ አባዜንና በእርሳቸው ቋንቋ በሃገሪቱ ውስጥ ከ11ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን የቀጠለው ፈላጭ ቆራጭ የፖለቲካ ባሕልን (Authoritarian Political Tradition) ነው። እንደ ጆን ያንግ ሁሉ ዶ/ር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዩች ላይ አብዝተው የተመራመሩት ጆን አቢኒክና ማሪና ኦታዌ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የትናንት የባሕል ሸክም እንዳጎበጠው እየገለጹ መፍትሔውን ይሄን ባሕል መቀየር ላይ ያደርጋሉ። እንዲሁም ሳራ ቮጋን እና ኬቲል ትሮንቮል የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አወቃቀር፣ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ድረስ በተዋረድ (hierarchy) የተሞላ መሆኑ ለዚህ የፖለቲካ ባሕል አለመዳበር እንደመንስኤ ይወስዱታል። “አብዛኞቹ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ዜጎች ተከራክረው፣ ሕይወታቸውን በተሻለ መንገድ ለመዘወር የሚያስችላቸውን አማራጭ ስለመለየት አያስቡም። ሌሎችም ይህንን ያደርጋሉ ብለው አይጠብቁም፤ የበላይ ወይም የበታች ከሚሏቸው ጋር ይህንን ማድረግ ደግሞ ጨርሶ የማይታሰብ ነው” ይላሉ።
ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግን ጨምሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሙሉ በጋራ የሚስማሙበት የሚመስለው ጉዳይ ‹የኢትዮጵ የፖለቲካ ባሕል አለማደግን› ነው። የፖለቲካ ባሕል ሊገለጽ የሚችልባቸው ብዙ መንገዶች ቢኖሩም፣ ‹ጠርዘኝነት› ግን ዋነኛውና ብዙዎቹ የፖለቲካ አመራሮች እንደፈታኝ የሚወስዱት ችግር ነው። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት “የፖለቲካ ባሕላችን ቀኖናዊ ነው” ወይም በሌላ አነጋገር “perfectionist (ፍፁማዊ)… ወይ አርዮስ ወይ ቅዱስ ብሎ የመፈረጅ አባዜ አለበት” የሚሉ ሲሆን፤ አያይዘውም “በእኛ ባሕል የፖለቲካ ሐሳብ ልዩነት ሲኖርህ መጠፋፋት ነው” ይላሉ። ይህ የኢንጅነር ይልቃል ምልከታ ከላይ የጠቀስናቸው ሳራ ቮጋን እና ኬቲል ትሮንቮል ‹The Culture of Power in Contemporary Ethiopian Political Life› በሚል ጥናታቸውን ከደረሱበት ድምዳሜ ጋር የሚስማማ ነው። ምሁራኑ በጥናታቸው ‹መንግሥት እና ተቃዋሚዎች በነገሮች እና ርዕዮተ-ዓለም ጉዳዮች ላይ አይወያዩም። የራሳቸውን ብቻ የፖለቲካ አመለካከት ይዘው እርስ በርስ በመነጋገር ፈንታ፣ አንዱ ሌላውን ይወቅሳል።› አጥኚዎቹ አክለውም፣ ሌላው ቀርቶ በፌዴራል መንግሥቱ ቋንቋ አማርኛ ውስጥ እንደሁለት የተነጣጠሉ አካላት የሚታዩት ‘state’ እና ‘government’ ተነጣጥለው የማይታዩ እና ‹መንግሥት› በሚለው ቃል ብቻ የሚተረጎሙ መሆኑ አንዱ የፖለቲካ ባሕሉ አለማደግ ምልክት አድርገው ይወስዱታል።
የኢ.ዴ.ፓ. የቀድሞው ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው ከፖለቲካ ባሕል አለማደግ ጋር አያይዘው ‹የእኛ የፖለቲካ ባሕል በጦርነትና በመገዳደል ሥልጣን መያዝ ነው፤ የእኛ ፖለቲካ ሲታይ አንዱ ባለኃይል ሌላኛውን ባለኃይል ሥልጣን የሚቀማበት ነው› የሚሉ ሲሆን አያይዘውም “ሕዝብ እንደሚሳሳት ማወቅና እና ሲሳትም ተሳስተሃል ሊባል እንደሚገባው መስማማት ይኖርብናል።” በማለት ባሕሉን እየተቸን ካላሳደግነው የፖለቲካ ሒደቱ የትም አይደርስም የሚል መደምደሚያ ይሰጣሉ።
ነገር ግን ይህ የፖለቲካ ባሕል አለማደግ ነው፣ የፖለቲካችን መሠረታዊ ችግር በሚለው ሐሳብ ሁሉም ምሁራን አይስማሙም። በዚህ ከማይስማሙት ምሁራን አንዱ ቶቢያስ ሐግማን ናቸው። “የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከባሕል አንፃር ብቻ መተርጎም ስህተት ነው” ይላሉ ሐግማን ጆን አቢኒክ ከምርጫ 97 በኋላ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ለጻፉት ጽሑፍ ምላሽ በሰጡበት ጽሑፋቸው። “ከዚህ እይታ ባለፈ ገዥው ፓርቲ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ከውስጡ ምን ያህል የተማከለ እና ፈላጭ ቆራጭ እንደሆነ መረዳቱ ነው ወሳኙ የፖለቲካው ውድቀት መነሻ” የሚሉት ሐግማን “ከዚህ ባለፈ ግን ችግሩን ወደ ባሕል መውሰዱ ገዥውን ቡድን ነጻ ማውጣት ነው የሚሆነው” ብለው የችግሩ መነሻና መድረሻ ገዥው ቡድን እንደሆነ አጽንኦት ይሰጣሉ። ነገር ግን ምሁራኑም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ባሕልን እንደ አንድ የችግሩ ምንጭ እንጅ የችግሩ ብቸኛው መነሻ አድርገው ላለመውሰዳቸው ጽሑፎቻቸውና አስተያየቶቻቸው ይገልጻሉ።
የታጠረው ምኅዳር
የፖለቲካ እሳቤዎች መዝገበ ቃላት እንደሚያስነብቡት የመድብለ ፓርቲ ስርዓት (multi-party system) ማለት በቁጥር የበዙ እና አሸንፈው መንግሥት በተናጥል ወይም በጥምረት የመመሥረት ዕድል ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለብሔራዊ ምርጫ የሚሳተፉበት ስርዓት ነው። ሌላው ቀርቶ በእነዚህ ብያኔዎች መሠረት የዴሞክራሲያውያኑ ምዕራብ አገሮች፣ ለምሳሌ የአሜሪካ የፖለቲካ ስርዓት የሁለት-ፓርቲ ስርዓት ነው። በአሜሪካ ከስልሳ በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም ከሪፐብሊካን እና ዴሞክራቶች በቀር አሸንፈው መንግሥት ለመመሥረት የሚችሉበት ዕድል ስለሌላቸው (ወይም ዕድላቸው እጅግ ጠባብ ስለሆነ) የአሜሪካ ስርዓት የሁለት-ፓርቲ ስርዓት እንጂ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ሊባል አይችልም።
ከገዢው ፓርቲ ውጪ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እና አንድ በግል የተመረጡ አባላት ብቻ ከተወከሉበት ምርጫ 2002 ወዲህ ገዢው ፓርቲ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ራሱን ‹አውራ ፓርቲ› በማለት መጥራት ጀምሯል። ይህንኑም ልማታዊ ዴሞክራሲ እያለ ከሚጠራው ከኢኮኖሚ ዕቅዱ ጋር አዋድዶ ለመቀጠል ትልሙ እንዳለው በተለያዩ መድረኮቹ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ‘የአውራ ፓርቲ’ (dominant party) ስርዓት እያራመደ ሳይሆን በኢፍትሐዊ መንገድ ያገኘውን የሕዝብ ተወካዮች ወንበር በሕዝባዊ ይሁንታ ያገኘው ለማስመሰል ከመጣሩም ባሻገር ምጣኔሀብታዊ ጠቀሜታ ያለው በማስመሰል ሕዝባዊ ቅቡልነት ለመግዣ እየተጠቀመበት ነው ከሚል ትችት አልዳነም። የአውራ ፓርቲ አካዳሚያዊ ብያኔ ‹አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ተከታታይ ምርጫዎችን በበላይነት ሲያሸንፍ፣ ወደፊትም የመሸነፍ ዕድሉ አነስተኛ ሆኖ ለመገመት የሚያስቸግርበት ስርዓት› እንደሆነ ይደነግጋል። ይህ ዓይነቱ ስርዓት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የታየው በተለይ በጃፓኑ ዴሞክራቲክ ሊበራል ፓርቲ እና ሌሎች ጥቂት አገራት ብቻ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የአውራ ፓርቲ ስርዓት የተከሰተባቸው አገራት ታሪክ የሚያሳየው አውራ ፓርቲው ‹አውቶክራት› (ለዴሞክራሲ ያልበቃ፣ በሌላ በኩል የወጣለት አምባገነንም ያልሆነ) ስርዓት ነው።
ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ራሱን አውራ ፓርቲ በማለት መጥራት የጀመረው ፓርቲው ‹ልማታዊ ዴሞክራሲያዊነት በተግባር ተፈትሾ ነጥሮ ወጥቷል› እንዲሁም ምርጫው ‹በኪራይ ሰብሳቢዎች ካምፕ ድንጋጤና ውዥንብር ፈጥሯል› ብሎ በገመገመው ምርጫ 2002 ማግስት ነበር። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ይሄን ‹አውራ ፓርቲ› የሚል ማዕረግ ለራሱ ሲሰጥ የአውራ ፓርቲ ስርዓት የዘረጉ ዴሞክራሲያዊ አገሮችን ሲዊዲንና ደቡብ ኮሪያ እያለ እያጣቀሰ የአንድ ፓርቲ ስርዓት ሳይሆን ወደ አውራ ፓርቲ ስርዓት እያመራን ነው፤ ይሄም ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ታላቅ እመርታ ነው በማለት ግምገማውን በወቅቱ አስቀምጧል። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ራሱን አውራ ፓርቲ ብሎ ከመሰየሙ ሦስት ዓመታት ቀደም ብሎ በ1999 የፓርቲዎች የሥነ ምግባር ደንብ ሙሉ ለሙሉ ተገልብጦ መጥቶበታል የተባለው ‹International Institute for Democracy and Electoral Assistance (IDEA)› የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ባቀረበው ሪፖርት ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ከምርጫ 97 ማግስት ወዲህ አውራ ፓርቲ እንደሆነ የሚያትት ነው። ‹IDEA› የአውራ ፓርቲ ስርዓት የሚባለው ስርዓት በአራት መልኩ የዴሞክራሲ ፀር እንደሆነ በሰነዱ ላይ የገለጸ ሲሆን እነዚህም አንደኛ፣ የፉክክር ፖለቲካን ያቀጭጫል፤ ሁለተኛ፣ የሕግ አውጭውን ሥልጣን ጠቅልለው በመያዝ በአንድ አገር ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ፍላጎቶች ይቆጣጠራል፤ በሶስተኝነት፣ ጠያቂ ስለማይኖርበት ተጠያቂነት የሌለበት ስርዓት ይፈጥራል እንዲሁም በመጨረሻም፣ የሥልጣን ትዕቢት በመፍጠር ለዜጎች ጥያቄ ደንታ ቢስ መንግሥት እንዲፈጠር ያደርጋል የሚሉ ናቸው። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የምርጫ ሥነ ምግባር ሕጉንና የአውራ ፓርቲ ፅንሰ ሐሳብን ከ‹IDEA› ወስዶ ይሄን የድርጅቱን የአውራ ፓርቲ የሰላ ትችት እንዳላየ ሁኖ በማለፍ በተለያዩ የፓርቲው ሰነዶች አሁንም አውራ ፓርቲ መሆኑን እየገለጸ ይገኛል።
የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ወዳጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ታላቁ ሊቅ ሳሙኤል ሀንቲንግተን ‹ዴሞክራሲ ሊጠናከር የሚችለው መንግሥት በምርጫ ሥልጣን ሊያጣ ሲችልና ሥልጣን ላይ የወጣው አዲስ ፓርቲም እንዲሁ ሥልጣኑን በምርጫ ሊያጣ ሲችል ብቻ ነው› በማለት የሥልጣን ሽግግር የዴሞክራሲ ምሰሶ መሆኑን ያስረዳሉ። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የወዳጆቹንም የጠላቶቹንም ምክር ወደ ጎን ብሎ የት እንደሚያደርሰው ባይታወቅም አሁንም የፖለቲካ ሥልጣኑን ሙሉ ለሙሉ ጠቅልሎ ይዞ ይገኛል።
አሁን አሁን ደግሞ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ራሱን የሚጠራበት ‹አውራ ፓርቲ› የሚለው ስያሜ የሚያንሰው እንደሆነ ተቺዎች መናገር ጀምረዋል። አንዳንዶች አሁን ፓርቲው ከመሠረቱ ሲያራምደው ከነበረው ሶሻሊስታዊ የብዝኃ አደረጃጀት (Mass Party) ቅርፅ ላይ የመንግሥታዊ ፓርቲነት (Cartel Party) ካባ ደርቦ ወፍሯል የሚለው ትችት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። መንግሥታዊ ፓርቲዎች የመንግሥትን ሀብት እንደፈለጉ የሚጠቀሙ ፓርቲዎች ሲሆኑ፤ አንዳንዴ የፓርቲና የመንግሥት መዋቅሮችን መለየት እስኪያስቸግር ድረስ አንድ ላይ የሚያዋህድ ቅርፅ ነው። ከዚህ መንግሥትና ፓርቲን ካልለየ አካሄድ ጋር ተያይዞ “ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ” የጣሊያናዊውን ማውሮ ሴሊዜን (Mauro Calise) ቋንቋ በመዋስ “ወደ ፓርቲክራሲ (Particracy) ቀይሮታል” ወደሚል መደምደሚያ ላይ እየደረሱ የሚገኙ ብዙዎች ናቸው።
በዚህ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የመጠቅለል አካሄድ ላይ ስጋት የገባቸው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢ.ዴ.ፓ.) የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው “ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በይዘት ከቻይና አስተሳሰብ ብዙም አይለይም” ይላሉ። የቻይና አስተሳሰብ የሚሉት፣ ‹አሁን ባለንበት ሁኔታ ዴሞክራሲ አያስፈልገንም፣ የሚያስፈልገን የኢኮኖሚ ሪፎርም ነው› የሚለውን ነው። የቻይና መንግሥት ይህንን የሚያደርገው በይፋ የአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲን ደንግጎ ነው። በቻይና ሕጋዊ ዕውቅና ያለው አንድ ‹የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ› ብቻ ነው። የቻይና የፖለቲካ ስርዓት አሀዳዊ እንጂ አውራ ፓርቲ ስርዓት አይባልም። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ግን ይህንን ማድረግ ያልቻለው፣ ደርግን ጥሎ አዲስ አበባ እግሩ በረገጠበት ሰዓት የቀዝቃዛው ጦርነት እየከሰመ ዓለም በሁለት ‹ብሎክ› የሚጠራበት ስርዓት እያበቃ በአንድ ዓለምዐቀፍ አስተሳሰብ እየተጠራ ስለነበር “የቻይና አካሔድ የሚበጅ ሆኖ ባለማግኘቱ” እንደሆነ አቶ ልደቱ ይናገራሉ። ስለሆነም “በወረቀት የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ደንግጎ፣ በተግባር ግን የቻይናን መንገድ ይከተላል”።
እንደ አቶ ልደቱ ገለጻ “ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ያስፈልገዋል ብሎ አያምንም። ለዚህ ሕዝብ አሁን ዴሞክራሲ አያስፈልገውም… የዳቦ ጥያቄው ከተመለሰ በኋላ ይደርስበታል ብሎ ነው የሚያምነው።”
የኦሮሞ ፌዴራል ኮንግረስ (ኦ.ፌ.ኮ.) ሊቀመንበር እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር መረራ ጉዲናም ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የመድብለ ፓርቲን የሚያስተናግድ አስተሳሰብ እንደሌለው ይናገራሉ። “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ይላሉ ዶ/ር መረራ “የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለማስተናገድ የተፈጠረ አይደለም”። በኢትዮጵያ መድብለ ስርዓትን የሚፈቅድ “የይስሙላ ጨዋታ” የተፈቀደው ዕርዳታ ለጋሽ አገራትን ለማስደሰት ብቻ ነው” በሚል ነው ዶ/ር መረራ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አለ ሊባል የሚችለው ብለው የሚያስቡት።
የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን የመጀምሪያ የሥልጣን ዘመናት በገመገሙበት ጽሑፋቸው ይሄን አካሄድ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የአግላይነት ፖለቲካ (politics of exclusion) ያሉት ሲሆን፤ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ያልተመቸውን ሰውም ሆነ ድርጅት ወደ ጎን እየገፋ ዙሪያውን በራሱ ሰዎች መክበብን እንደ ዋነኛ የሥልጣን ላይ መቆያ ዘዴ እንዳደረገው አያይዘውም ይገልጻሉ። ዶ/ር ካሳሁን ይህን ካሉ ከ15 ዓመታት በኋላ ይህ አካሄድ መባስ እንጅ መሻሻልን እያወቀ አይደለም።
የተበላሸ ዘርና ተጣሞ ‘ያደገ’ ተክል
የፓርቲ ፖለቲካ ላይ የሚቀርበው ሌላው መሠረታዊ ትችት የፖለቲካው ተዋንያንንና ከተዋንያኑ አደረጃጀት ጋር ተያይዞ የሚቀርብ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቋቁሟቸው ግለሰቦች በራሳቸው ብዙ የራሳቸው የግል ፍላጎት ያሏቸውና ተደራጅተው ከሌሎች ጋር መሥራት የሚቸግራቸው ናቸው ከሚለው ሐሳብ ነው ትችቱ የሚጀምረው። ዶ/ር ወንድወሰን ተሾመ በአሁኑ ወቅት ያሉ የኢትዮጵያ ፓርቲ ፖለቲካ ተዋንያንን በሰባት መደቦች ያስቀምጧቸዋል። በዐፄ ኃይለሥላሴ ስርዓት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ (ex-minsters of the ancien régime)፣ የግራ ፖለቲከኞች (leftists)፣ የቀድሞ የግራ ፖለቲከኞች (ex-leftists)፣ ፋኖ ያሉ ፓርቲዎች (rebels)፣ ታማኝ ተቃዋሚዎች (loyal oppositions)፣ አስመሳይ ተቃዋሚዎች (phony oppositions) እና በፊት ኢሕአዴግ ውስጥ የነበሩ (ex-EPRDF members) በማለት። እንግዲህ እነዚህ በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች ላይ ያሉ ተዋናዮች (አንዳንድ ከሁለት በላይ ባሉ መደቦች ውስጥ እየገቡ) የራሳቸውን ፍላጎት ለማራመድ ሲሉ ሌሎችን እየጠለፉ ሁሉም የፖለቲካው ከፍታ ላይ መድረስ እንዳይችሉ ሁኗል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ የውስጥ ፓርቲ የዴሞክራሲያዊነት (intra-party democracy) ችግር እንዲሁም ተቋማዊ ቁመና (Institutionalization ) የመያዝ ችግር አለባቸው የሚለው ትችትም ሁሌም የሚሰማ ነው። ሮበርት ሚሸልስ የተባሉ ምሁር የውስጥ ፓርቲ ዴሞክራሲን ይዞ የተደራጀ መዋቅር ያለውና ተቋማዊ ቁመና ያለው ፓርቲ ማቋቋም አብረው ሊሄዱ የማይችሉ (inconsistent) ጉዳዩች ናቸው ይላሉ። ፓርቲን ተቋማዊ ቅርፅ አስይዞ በተመሰሳይ ወቅት ዴሞክራሲያዊ ላድርግ ማለት የኋላ ኋላ ሁለቱንም ያሳጣል የሚል ነው የሐሳቡ አንኳር። ኢንጅነር ይልቃል በዚህ ሐሳብ የሚስማሙ ይመስላሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ‹የፓርቲ አባላትን ዲስፕሊንድ አድርጌ የውስጥ ፓርቲን ዴሞክራሲ አሰፍናለሁ ማለት በዚህ ዘመን ከባድ ነው› ይላሉ። አያይዘውም የውስጥ ዴሞክራሲን በፓርቲ ውስጥ አስፍኖ የፓርቲ ዲሲፕሊን የሚባለውን ጉዳይ ወደ ጎን ብሎ የንቅናቄ ቅርፅ ያለው ፓርቲ ይዞ መቀጠልን እንደሚመርጡ ይገልጻሉ።
የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ አሉባቸው ከተባሉት የአባላት ችግር እና የውስጠ ፓርቲ ቁመና ችግር ባለፈ ያለምንም ዓላማ አዳዲስ ፓርቲዎች እየተቋቋሙ እርስ በርሳቸው ይጠላለፋሉ የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ድረ-ገጽ ላይ (ሚያዝያ 28/2008 እንዳየነው) የተዘረዘሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች 75 ናቸው። ከ2007 ምርጫ በፊት ‹ለቀጣዩ ምርጫ በንቃት የሚሳተፉ ፓርቲዎች ዝርዝር› በሚለው ስር የተዘረዘሩት ፓርቲዎች ቁጥር ግን ጠቅላላ ከተባለው የፓርቲዎች ዝርዝር ይበልጣል። እሱም በእንግሊዝኛው እና በአማርኛው ላይ የተለያየ ሁኖ እናገኘዋለን። በእንግሊዝኛው 79 ሲሆኑ፣ በአማርኛው 76 ናቸው። ከዚህ የቁጥር ዝብርቅርቅ በተቃራኒው፣ ብዙዎች የሚተቹት ብዛታቸው እና የርዕዮተ-ዓለም ልዩነታቸው የማይጣጣም መሆኑን ነው። ምንም እንኳን ብዙዎቹ ፓርቲዎች በዘውግ ከመደራጀታቸው በቀር ልዩነት ባይኖራቸውም መንግሥት ለመመሥረት በሚያስችላቸው ቁመና ለመቆም ጥምረት ወይም ግንባር ሲፈጥሩ አይታዩም። ኅብረ-ብሔራዊ መሠረት ይዘው የተደራጁትም፣ ግልጽ የሆነ የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ባይኖራቸውም ተደራጅተው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን ለመገዳደር በሚያስችላቸው መዋቅር ለመቅረብ አልሞከሩም፣ ቢሞክሩም አልተሳካለቸውም።
ዶ/ር መረራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ችግር ነው ብለው አያምኑም። “እስራኤል 5 ሚሊዮን ሕዝብ ብቻ ነው ያላት፤ ነገር ግን ከ30 በላይ በአገሪቱ ሕልውና የማይደራደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሏት። ስለዚህ ለ100 ሚሊዮን ሕዝብ ብዙ ፓርቲዎቹ ቢኖርም ያን ያክል ችግር አይደለም። ችግሩ፣ እነዚህ ፓርቲዎች ለሕዝብ ጥቅም የቆሙ ናቸው ወይስ አይደሉም፤ ለራሳቸውም ሥልጣን ለማግኘት ቢሆን ችግር የለውም፤ እንዲሁ የገዢው ፓርቲ ቀለብ የሚሰፍርላቸው ናቸው የሚለው ነው የሚያሳስበው” ይላሉ። የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ስንመለከትም ዶ/ር መረራ ከሚሉት እውነታ ብዙም የራቀ ድምዳሜ ላይ አንደርስም። ኬኒያ በአንድ ወቅት እስከ 160 የሚደርሱ የተመዘገቡ ፓርቲዎች ነበሯት፤ ናይጄሪያም 60 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሏት። ደቡብ አፍሪካንም የወሰድን እንደሆን ከ80 በላይ ፓርቲዎች ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱባት ሀገር ነች። ከዚህም አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲዎች መብዛት መሠረታዊ ችግር ነው የሚለው ሐሳብ ትክክል ነው ማለት አይቻልም። መሠረታዊው ችግር ያለው ‹እነዚህ ፓርቲዎች እንቅስቃሴያቸው ምን ይመስላል? የፓርላማ ውክልናቸውስ?› የሚለው ነው የሚሆነው። ኬኒያ ካሏት ፓርቲዎች መካከል 23 የሚሆኑት የፓርላማ ውክልና አላቸው፤ በናይጀሪያም 6 ፓርቲዎች በፓርላማ መቀመጫ ያለቸው ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ 13 በፓርላማ ወንበር ያላቸው የፓርላማ ፓርቲዎች (Parliamentary Parties) አሏት። እንግዲህ የኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ አሳዛኝና አሳሳቢ የሚሆነውም ከዚህ አንጻር ስንመለከተው ነው። በአሁኑ ወቅት ገዥው ፓርቲ ብቻ በፓርላማ ተወክሎ የፈለገውን የሚወስንበት ጊዜ ሲሆን፤ ይሄም የፓርቲ ፖለቲካ የሚባለውን ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ እንዳይቀብረው የብዙዎች ስጋት ነው።
ዶ/ር መረራ በኢትዮጵያ ‹የፈሉትን› የፖለቲካ ፓርቲዎች “አንዳንዶቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከራሳቸው [ከሊቀመንበሮቹ] የግል ዝና ያለፈ ቁመና ያላቸው አይመስለኝም…” ሲሉ አቶ ግርማ ሰይፉ ደግሞ “በአንድ ሰው የሚዘወሩ ሱቆች ወይም ከሱቅ በላይ ማዕረግ የሌላቸው ናቸው” ይሏቸዋል። አቶ ግርማ የሚያስገርማቸው “አንደኛ፣ እንደዚህ ዓይነት ፓርቲዎች እንዲቋቋሙ የሚፈቅድ መንግሥት መኖሩ እና ፓርቲዎቹ ውስጥ ለመሰባሰብ የሚፈቅዱ አባላት መኖራቸው” ነው። አቶ ግርማ፣ ሲቪክ ማኅበራት ሲዋቀሩ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያስቀምጥ መንግሥት፣ አገር እንመራለን ብለው የሚደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ‹በነጻ የመደራጀት መብትን ለማክበር› በሚል ሰበብ ብቻ እንዲሁ መተው ተገቢ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና በሕዳር ወር 2007 በሰጡት ይፋ ቃለ ምልልስ “75 [የፖለቲካ ፓርቲዎች] አሉ። ነገር ግን የሕግ ጉዳይ ያላሟሉና ሥልጣንን ሞኖፖላይዝ ያደረጉ እንዲሁም ራሳቸው ባወጡት ደንብ መሠረት ለ18 ዓመታት ጠቅላላ ጉባኤ ያልጠሩ አንዳንድ ፓርቲዎች ይገኙበታል። ለዴሞክራሲው ስንል በሆደ ሰፊነት ነው የምንይዛቸው” ብለው ነበር። አመራር የነበሩበት አንድነት ፓርቲ በእርሳቸው አገላለጽ ‹ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ› በምርጫ ቦርድ ጣልቃ ገብነት የተሰነጠቀባቸው እና ለሌሎች ተላልፎ የተሰጠባቸው አቶ ግርማ ሰይፉ ግን ይህ አባባል አይዋጥላቸውም። “ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. እንዲህ ዓይነቶቹን ‹ሱቅ› የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝም የሚላቸው ለሥልጣኑ ስለማያሰጉት እና ስለሚፈልጋቸው ነው።” በማለት ነው ሐሳባቸው የሚገልጹት።
አቶ ልደቱ አያሌው “ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ የተመዘገበ፣ ሰርቲፊኬት ያለው ተቃዋሚ ፓርቲ እንጂ በተግባር ግን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴ የሚመጥን ተቃዋሚ ፓርቲ እስካሁን አልተፈጠረም። በምርጫ ቦርድ መስፈርቱን አዘጋጅተን ተመዝግበናል። ሕጋዊ ፈቃድ አለን፣ ቢሮ አለን፣ እንንቀሳቀሳለን። ምርጫ እንወዳደራለን። አሁን ካለው የኢትዮጵያ ሁኔታ አንፃር ግን፣ በተለይ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን ዓይነት ግዙፍ ድርጅት ተቋቁሞ ለሥልጣን መብቃት የሚችል የፖለቲካ ፓርቲ እስካሁንም አልተፈጠረም፤ አሁንም የለም።” በማለት አቶ ግርማ ‹ሱቅ› እያሉ የሚጠሯቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቹም ፓርቲዎች ሕዝቡን በሚመጥን ቁመና ላይ እንደሌሉ ይሟገታሉ። አቶ ልደቱ ለዚህ ችግር መንስኤ ናቸው የሚሏቸውን አምስት ነጥቦች ዘርዝረዋል። “አንደኛ፣ ፖለቲካችን የሐሳብ ፖለቲካ አልሆነም፤ ሁለተኛ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና መጫወት የሚችለው የኅብረተሰብ ክፍል በተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ ተሳትፎ አያደርግም፤ ሦስተኛ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣዊ ዴሞክራሲ የላቸውም፤ አራተኛ፣ አካባቢያዊ ስሜት በፓርቲዎች ውስጥ ነግሷል፤ አምስተኛ፣ ፓርቲዎቹ የውጪ ፖለቲከኞች ላይ ጥገኛ ናቸው” በማለት ያስቀምጧቸዋል።
የኢትዮጵያ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥራቸው ቢበዛም በአሁኑ ወቅት አንድም የፓርላማ ወንበር መያዝ አልቻሉም። ከላይ ካነሳናቸው የውጭና የውስጥ ችግሮች በተጨማሪ ከውሕደትና ጥምረት ጋር ተያይዘው የሚቀርቡባቸው ትችቶችም አሉ። ትችቱ ተዋሃዱ የሚል ብቻ ሳይሆን ለመዋሃድ ሲባል ፓርቲዎች መሠረታቸውን እየናዱ ይፈርሳሉ፤ መዋሃድን እንደ ግብ መውሰዳቸው ስህተት ነው የሚልም ነው። በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ከሁሉም ፈታኝ የሆነ ችግር እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙበት መተባበር አለመቻልን ነው። መተባበሩ ቀርቶ አንድ ፓርቲ ሳይሰነጠቅ እየጎለበተ መሄድ የሚችልበት ሁኔታም በተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሚናፈቅ ነገር ሆኗል የሚሉም አልታጡም። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ አቶ አስናቀ ከፋሌ ‹The (un)making of opposition coalitions and the challenge of democratization in Ethiopia, 1991–2011› በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታቸው ላይ ምርጫ 97 ላይ የመተባበር (coalition) ፖለቲካ እመርታ ታይቶ እንደነበር ይገልጻሉ። በዚህም ተቃዋሚዎች ‹ለምርጫ ሕጎች መሻሻል እና በአካባቢያዊ እና ብሔራዊ ደረጃ ጉልህ ውክልናን ለማሸነፍ በሚያስችል ሁኔታ መደራደር ቢችሉም፣ ያንን ማስቀጠል አልቻሉም። ያኔ እና ከዚያ በኋላ ትብብሮች ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም› ብለዋል።
አቶ አስናቀ በዚሁ ጥናታቸው፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር አለመሳካት መንስኤ ሆነዋል የሚሏቸውን ሰባት ምክንያቶች በጽሑፋቸው ላይ ዘርዝረዋል። 1ኛ፣ ከልካዩ የፖለቲካ ምኅዳር እና የመንግሥት ተፅዕኖ፤ 2ኛ፣ በርዕዮተ-ዓለማዊ መግባባት ሳይሆን በሥመ-ተቃዋሚነት ብቻ ለመተባባር መስማማት፤ 3ኛ፣ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች በተለያዩ ቡድኖች የመቧደን ተፅዕኖ፤ 4ኛ፣ የጋራ መግባቢያ የመፍጠር ልምድ ማነስ እና የዴሞክራሲ ባሕል እጦት፤ 5ኛ፣ የድርጅት ነጻነት (independence) ከግምት ውስጥ ያላስገባ ‹ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ› በሚለው ግፊት ብቻ የማይዘልቅ ጥምረት መመሥረት፤ 6ኛ፣ በተጣማሪዎቹ ድርጅቶች መካከል ያለ የኃይል/ሥልጣን ሽሚያ፤ እና 7ኛ፣ በተጣማሪ ቡድኖች መካከል መተማመን አለመኖር ለብዙዎቹ ጥምረቶች ስኬት ማጣት እና መልሶ መፍረስ ሰበቦች መሆናቸውን አመላክተዋል።
ከዚህ ከአቶ አስናቀ ትችት በተመሳሳይ አቶ ልደቱ አያሌው ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች ‹አንዱ መተባበርን እንደግዴታ የሚወስድ ባሕል መኖሩ እንደሆነ ይናገራሉ። የተለያየ የፖለቲካ ግብ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን ለመገዳደር ብቻ ሲባል እንዲተባበሩ ግፊት ይደረግባቸዋል። የሚተባበሩት በርዕዮተ-ዓለም አንድ ሆነው ስላይደለ ኅብረታቸው አይሰምርም› ይላሉ። ማኅበር (ወይም የፖለቲካ ድርጅት) መመሥረት በራሱ መተባበር እንደሚጠይቅ የሚናገሩት ኢ/ር ይልቃል ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል “የመተባበር አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነገር አይደለም” ባይ ናቸው። ይልቁንም፣ ኢንጅነር ይልቃል እንደችግር የሚወስዱት ያላደገው የፖለቲካ ባሕላችን ችኩልነትን እና ፍፁማዊነትን መሻቱን ነው። ማኅበሮች በችኮላ እንዲመሠረቱ እና ፍፁማዊ ስኬት እንዲያስመዘግቡ ይጠበቃል። ይህ ደግሞ አይሳካም ይላሉ። “አለመተባበርም፣ ለውጤት የመጓጓትም ችግሮቹ አንድ ናቸው፤ ምንጩን ስናየው ውጤቱን በአንድ ሌሊት ለማየት መጓጓት ነው። ቅንጅትንም ያፈረሰው ይሄው ነው” ብለዋል።
በመጨረሻም ፓርቲዎች ውጤት ለማምጣት ላለመቻላቸው የሚጠቀሰው ምክንያት የአደረጃጀታቸው ጉዳይ ነው። ይሄም ሕብረ-ብሔራዊና የዘውግ (ethnicity) አደረጃጀት የሚለው ክፍፍል ኅብረ-ብሔራዊ የሚባሉት ፓርቲዎች ጎልተው እንዳይወጡ አድርጓቸዋል፤ የብሔር መሠረት ያላቸው ፓርቲዎች ደግሞ ከራሳቸው ማዕቀፍ ወጥተው ጠንካራ ተገዳዳሪ መሆን እንዳይችሉ አደረጃጀታቸው በራሱ ያግዳቸዋል የሚለው ነው።
በ1960ዎቹ በጋናዊው ኩዋሚ ኑኩሩማህ ጀማሪነት የተጀመረው የአፍሪካ ፓርቲዎችን በንዑስ መሠረት (particularistic) ላይ እንዳይመሠረቱ መከልከል እየተለመደ መጥቶ ከ1990ዎቹ ወዲህ እጅግ ሰፍቶ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ውጭ ፓርቲዎች ዘውግንም ሆነ ሃይማኖትን መሠረት አድርገው የተደራጁበት የሰሃራ በታች የሚገኝ የአፍሪካ ሀገር አለ ማለት አይቻልም። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ፓርቲዎች ዘውግን መሠረት አድርገው የሚደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕግ የተከለከሉ ናቸው። ለዚህም የሚሰጠው ዋነኛ ምክንያት እንደዚህ ያሉ አደረጃጀቶች ከፋፋይና (divisive) የሲቪል የፖለቲካ ሂደት እክል ናቸው የሚል ነው። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ከላይ ባየነው የአፍሪካ እውነታ በተቃራኒው በአሁኑ ወቅት ገዥውን ግንባር ጨምሮ አብዛኞቹ ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው ፓርቲዎች የአደረጃጀት መሠረታቸው ዘውግ ነው።
ከዚህ መሬት ላይ ያለ እውነታም በመነሳት ‹በአሁኑ ወቅት በተሻለ የጥንካሬ ቁመና ላይ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔር ወይም በዘውግ የተደራጁት ናቸው፤ ኅብረ-ብሔራውያኑ ተዳክመዋል። ኅብረ-ብሔራውያኑ ፓርቲዎች የመሰነጣጠቅ አደጋ የሚያንዣብብባቸው በውስጣቸው በዘውግ የመቧደን አባዜ ስለሚከሰት ነው› በማለት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሚከሰቱ ውስጣዊ መዳከሞች እና መከፋፈሎች ላይ መንስኤው በዘውግ መደራጀት መፈቀዱ ነው የሚሉ ፖለቲከኞች ጥቂት አይደሉም። በአፍሪካ ውስጥ (ኬንያ እና ጋናን ጨምሮ) በዴሞክራሲ እያበቡ ያሉ አገራት በዘውግ መደራጀትን በይፋ በማገዳቸው የመድብለ ፓርቲ ስርዓታቸው ፈተና ውስጥ እንዳልወደቀ የሚከራከሩ አሉ።
አቶ ልደቱ አያሌውም ፖለቲካችን በከፍተኛ ሁኔታ የብሔር ፖለቲካ ያጠላበት መሆኑን አምነው፤ እንደሌሎች የአፍሪካ አገራት በዘውግ መደራጀትን ማገድ ያስፈልግ ይሆን ወይ ለሚለው ጥያቄ “የብሔር ፖለቲካን በሕግ ማገድ ያስፈልጋል ባልልም፣ እንደማይጠቅም ግን አምናለሁ” ይላሉ።
በሌላ በኩል በዘውግ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹ኅብረ-ብሔራዊ የሚባል ፓርቲ የለም። ኅብረ-ብሔራዊ ነን ብለው የሚደራጁት የአንድ ብሔር ሰዎች እና የከተማ ሰዎች ብቻ ናቸው› ብለው በተቃራኒው ይከራከራሉ። ባለፈው የፓርላማ ዘመን በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ እና የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አመራር አባል የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ ይህንን አስመልክቶ “አንድነት ፓርቲ የሁሉም ቤት ይሁን ብለን ስንሠራ ትልቁ ተግዳሮት የሆነብን ብሔር ተኮር የሆነው አመለካከት የሚጎትታቸው ብዙ ሰዎች መኖራቸው ነው። ለምሳሌ አንዳንድ አባላት የብሔር ፖለቲካ ታማኝነታችን መድረክ [አሁን የብሔር ድርጅቶች ብቻ ስብስብ] ውስጥ በመቆየት የሚገለጽ የሚመስላቸው አሉ። አንድነት ፓርቲ ውስጥ አባል ሆነው የሚቆዩት ፓርቲው የመድረክ አባል ሆኖ እስከ ቆየ ድረስ እንደሆነ ቅድመ ሁኔታ አድርገው የሚያስቀምጡ አሉ። ኅብረ-ብሔር ነኝ ብሎ ተደራጅቶ ውስጣዊ ፍልስፍናው ዘውጋዊ የሚሆንበትም ጊዜ አለ” ብለዋል።
አቶ ልደቱ የአንድ ብሔር ሰዎች አንድ ድርጅት ውስጥ በዝተው ስለታዩ ፓርቲው ኅብረ-ብሔራዊ አይደለም አያሰኘውም። ይልቁንም “ፓርቲው የተደራጀበት አስተሳሰብ ነው ድርጅቱ ኅብረ-ብሔራዊ ነው አይደለም የሚለውን የሚወስነው” ይላሉ። ለምሳሌ ‹ኢዴፓ 46 በመቶ የሚሆኑት አባላቱ የደቡብ አካባቢ ሰዎች ናቸው› በማለት፣ ከአስተሳሰባቸው በተጨማሪ ኅብረ-ብሔራውያን ነን የሚሉት የአንድ አካባቢ ሰዎች ናቸው የሚባለው ሁሉ እውነት እንዳልሆነ ይከራከራሉ። አቶ ልደቱ “በተጨማሪም፣ አንዳንድ ጊዜ የመረጃ እጥረት ያለ ይመስለኛል” ይላሉ። “ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ጠንካራዎቹ እነማን ናቸው የሚለው ላይ እስካሁን ድረስ በተካሄዱት ምርጫዎች ላይ የተገኙትን ድምፆች መለስ ብለን ብናየው፣ ብዙ ድምፅ ያገኙት የብሔር ድርጅቶች ሳይሆኑ ኅብረ-ብሔር ድርጅቶች ናቸው” ይላሉ።
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ከዚህ የተለየ አመለካከት ነው ያላቸው። ኢ/ር ይልቃል “ኅብረ-ብሔራዊ” በሚለው አላምንም ይላሉ። እንደእርሳቸው ሰማያዊ ፓርቲ ራሱን “ኅብረ-ብሔራዊ” ብሎ አይጠራም። “ምናልባት አንዳርጋቸው ጽጌ በሚጠቀምበት አማርኛ ‹ዘውግ-ዘለል› ብንለው ይሻል እንደሆን አላውቅም፤ ፓርቲዎች ወይ የዘውግ ፓርቲዎች ናቸው አለበለዚያ ደግሞ የርዕዮት-ዓለም ፓርቲዎች ናቸው ማለት ነው። በሐሳብ ደረጃ በዜግነት ላይ የተመሠረቱ ፓርቲዎች አሉ፤ አለበለዚያ ‹ኅብረ-ብሔር› የሚለው ቃል ራሱ የመጣው የአንድ ብሔር አደለንም ለማለት ነው እንጂ ዘውግን መሠረት አላደረጉም ማለት አይደለም” ይላሉ። ይሁን እንጂ ኢ/ር ይልቃል የዘውግ አደረጃጀት በቅርብ የሚያስተሳስሩ የወል ሥነ-ልቦና ስለሚኖሩት በፍጥነት የተወሰነ ጊዜ መዝለቅ የሚችል ድርጅት ለመፍጠር እንደሚጠቅምም አበክረው ይናገራሉ። ‹ዘውግ-ዘለል› የሆነ ተቋም ለመመሥረት ግን ጊዜ ስለሚወስድ በመሐል ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ም በቀላሉ መስበር የሚችልበት ዕድል ይኖረዋል፤ ሌሎችም ሁኔታዎች ይፈታተኑታል በማለት በርዕዮት-ዓለም የሚደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዘውግ ከሚደራጁት ይልቅ ከፍተኛ ተግዳሮት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
አቶ ግርማ ሰይፉ በዘውግ መደራጀት “ግብ የለውም” ብለው ነው የሚያምኑት። “ሌላው ቀርቶ ብዙ ሕዝብ ያለው የኦሮሚያ ክልል ነው። ኦሮሚያ ክልልን መሠረት አድርገው የተደራጁት እንኳን አገር የማስተዳደር ግብ የላቸውም። ክልል ማስተዳደርን ግብ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ይህ ግን ሰንካላ ግብ ነው። አገር የማስተዳደር ግብ ሊኖራቸው አይችልም። አገር ለመምራት ከፈለጉ ሌላ አንድ ድርጅት መፈለግ አለባቸው። አንድ ፓርቲ ሲቋቋም በራሱ መንግሥት ለመመሥረት እንዲችል ሆኖ መሆን አለበት።” በማለት መንግሥት ለመመሥረት ከሚያስችል ባነሰ አደረጃጀት የሚቋቋሙ ድርጅቶች ግብ የላቸውም በማለት አምርረው ይተቻሉ። “በደቡብ ክልል አንዳንዶች አንድ የፌዴራል ምክር ቤት መቀመጫ የሚያስገኝ የዘውግ አደረጃጀት ይዋቀራሉ፤” የሚሉት አቶ ግርማ “እነዚህኞቹ ድርጅቶች በክልል ምክር ቤትም ይሁን በፌዴራል ደረጃ ምንም ፋይዳ የላቸውም። ግብ የላቸውም” ብለዋል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና በዚህ ዘውጋዊ አደረጃጀትን የማይቀበል አካሄድ አይስማሙም። “[በዘውግ መደራጀት በሌሎቹ አገራት] በሕግ ባይፈቀድም በተግባር ግን አለ፤ ኬንያን ለምሳሌ ብትወስድ ኪኩዩ ካልሆንክ ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረህ ማሸነፍ ያስቸግርሃል።… ለምሳሌ ኦዲንጋ እና ኡሁሩ ኬንያታ በምንም አይገናኙም። ኦዲንጋ በልምድም በዕውቀትም ይበልጠዋል። ኡሁሩ ያሸነፈው ኪኩዩ ስለሆነ ነው። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ዙማ ፕሬዚዳንት የሆነው ዙሉ ስለሆነ ነው እንጂ በመደበኛ ትምህርት እንኳን አልዘለቀም። እኔ የአፍሪካ ፖለቲካን እስካነበብኩ ድረስ ታንዛንያውያን ብቻ ነው ይሄ ነገር የሌለባቸው። እነሱም [የዘውግ] ቡድኖቻቸው ትንንሽ በመሆናቸው ነው። ይሄ ነገር የሚቀንሰው ካፒታሊስቶቹ ጋር ነው። እነሱ የሚደራጁት በጥቅም ፍልስፍና ነው። ነገር ግን በዘር መቧደን እዛም ይቀራል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ጥቁር አሜሪካውያን 80 በመቶ ኦባማን ሲመርጡ እንደነበር ይታወቃል” ይላሉ። አያይዘውም አንድ ፓርቲ ኅብረ-ብሔራዊ ነኝ ስላለ ብቻ የብሔር መሠረት የለውም ማለት አይደለም በማለት መከልከሉ ምንም ዓይነት ውጤት ያመጣል ብለው እንደማያስቡ ይገልጻሉ።
ነገሩ መነሳቱ በአደረጃጀት ደረጃ ያለውን ግንዛቤ ያጠራዋል በሚል ሐሳብ እንጅ ገዥው ፓርቲ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ራሱ በዘውግ የተደራጀ ፓርቲ ሆኖና ሕግ የማውጣቱን ሒደትና መሣሪያ ሙሉ ለሙሉ ተቆጣትሮት ባለበት ሁኔታ የራሱን አደረጃጃች ሕገ ወጥ የሚያደርግ መመሪያ ያወጣል ብለን ማሰብ ቅዥት ነው የሚሆነው።
ቻው ቻው የፓርቲ ፖለቲካ?
አሁን አሁን በኢትዮጵያ የሠላማዊ የፖለቲካ መድረክ ላይ ለብዙ ዓመታት ተዋናይ የነበሩ ግለሰቦችን ጨምሮ በብዙዎች ዘንድ የፓርቲ ፖለቲካን በአሁኗ ኢትዮጵያ ማካሄድ አይቻልም የሚል ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ ይታያል። ከእነዚህ የፓርቲ ፖለቲካ ተስፋ ከቆረጡ ግለሰቦች መካከል አቶ ግርማ ሰይፉ አንዱ ናቸው። አቶ ግርማ ‹ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን የሚያክል የሠላማዊ ትግል እክል ባለበት አገር ተቃዋሚዎችን ለመውቀስ የሞራል ብቃቱ የለኝም› ይላሉ። ለአቶ ግርማ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በኢትዮጵያ ተወልዶ የነበረውን የፖለቲካ ፓርቲ ትግል ወደ መቃብር ሸኝቶታል የሚል እምነት አላቸው። ከዚህ በኋላ በፓርቲ ቁመና ተደራጅቶ ልታገል ማለት ተደራጅቶ ለኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መመቸትና ለመጥፋት መንደርደርም ነው ብለው ያምናሉ። ከዚህም ተነስተው ከዚህ በኋላ አራማጅነትን (Activism) መሠረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች እንጅ የፓርቲ ፖለቲካ ለውጥ ያመጣል ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ። “አሁን ያለው የፓርቲ ፖለቲካና የእስካሁኑ ትግል እርሾ ሁኖ ይቀጥል በሚለው ሐሳብ አልስማም” የሚሉት አቶ ግርማ ነገሮችን በአዲስ አተያይና አዲስ አካሄድ ማስጀመር መልካም መሆኑን ይገልጻሉ።
“ተስፋ ብንቆርጥማ እዚህ ምን እንሠራለን?”
በታኅሣሥ 2001 የብዙ ግለሰቦችን ጥያቄ ይፈታል የተባለለት በኦሮሞ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እና የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ ፓርቲዎች ሁለት መሆናቸውን ትተው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦ.ፌ.ኮ.) በሚል አዲስ ስያሜ ተዋህደው አንድ ወደ እንቅስቃሴ መግባታቸው ለብዙዎች ተስፋ የሰጠ እርምጃ ነበር። ኦ.ፌ.ኮ. ከዛን ጊዜ ወዲህ ከሌሎች አራት ፓርቲዎች ጋር በመሆን ‹መድረክ› የተባለ ግንባር በመፍጠር እየተንቀሳቀሰም ይገኛል።
ኦ.ፌ.ኮ. በሐገሪቱ ውስጥ ካሉት ዘጠኝ የፌደራል ክልሎች መካከል በሕዝብ ብዛትና በቆዳ ስፋት ደረጃ ትልቁ በሆነው የኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ብቸኛው ፓርቲ ነው ለማለት በሚያስችል መልኩ የሚገኝ ሲሆን፤ ፓርቲው የብዙዎችን ትኩረት የሚስበውም ከዚህ አቅሙ አንፃር ነው። ነገር ግን ባለፉት አምስት ወራት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከተካሔዱት ሕዝባዊ ተቃውሞች ጋር በተያያዘ የድርጅቱ ዋነኛ አመራሮች የታሰሩበት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ በቡሌ ሆራ ከተማ የቀረች አንድ የፓርቲ ቢሮ ብቻ እንዳለችው የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በጥርጣሬ ይገልጻሉ። የድርጅቱ ሠላማዊ ታጋዮች ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በክልሉ እየወሰደው ባለው ርምጃ ተጠቂዎች እንደሆኑ የገለጹት ዶ/ር መረራ የፓርቲያቸው ድል አድርገው የሚቆጥሩት “ሕዝቡን በተለያዩ መንገዶች አንቅተነው አሁን እኛ ባንኖርም መብቱን የሚያውቅና ለማስከበርም ቆርጦ የተነሳ ሕዝብ መፈጠሩ ነው” ይላሉ። ከዚህም ተነስተው “በፓርቲ ፖለቲካማ ተስፋ እንዴት እንቆርጣለን? ተስፋ የምንቆርጥ ከሆነማ እዚህ ምን እንሠራለን?” በማለት ተስፋ አስቆራጭ ነው ስለሚባለው የፖለቲካ ምኅዳር ላቀረብንላቸው ጥያቄ ምላሻቸውን ይሰጣሉ። “ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ከመቼውም ጊዜ በላይ የተዳከመው አሁን ነው” የሚሉት ዶ/ር መረራ “ኢሕአዴግ በ101 ችግሮች ተብትቦ ቢይዘንም አሁንም የሚሻለው ያሉብንን የመተባበር ችግሮች ተሻግረን ወደፊት መሄድ ነው” ይላሉ። መሪ የሚሆን ፓርቲ በሌለበት ሁኔታ ለውጥ እንኳን ቢመጣ በለውጥ ማግስት የሚፈጠረው ክፍተት የመረራ ስጋት ነው።
ፍሬውን ለማየት
በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ እና የፖለቲካ ባሕል ውስጥ ተዘርዝረው የማያልቁ ችግሮች አሉ። ለችግሮቹ ተጠያቂ የሆኑ ዐብይ አካላት ቢኖሩም፣ ችግሮቹን ሁሉ ለአንድ ወገን ብቻ ጠቅልሎ መስጠት የትም እንደማያደርስ ከአጥኚዎች እስከ ፖለቲከኞች ድረስ ይስማማሉ።
አቶ ልደቱ አያሌው “ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛው ችግር ቢሆንም ብቸኛው አይደለም፤” ይላሉ። “ኢሕአዴግን የችግሩ አካል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመፍትሔ አካል አድርጎ ማየት ያስፈልጋል። እስከዛሬ ድረስ የሚጠቆሙት መፍትሔዎች በሙሉ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መቃብር ላይ ለማድረግ የሚታሰቡ መሆናቸው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በተፃራሪው እንዲሠራ አድርጎታል” ይላሉ። ስለዚህ ወደ መድብለ ፓርቲ የሚደረገው ጉዞ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን የችግሩ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔው አካል ማድረግ አለበት። በሁለተኝነት፣ አቶ ልደቱ በተመሳሳይ መንገድ “ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመፍትሔው አካል ነን፤ ነገር ግን የችግሮቹም አካል እንደሆንን ማመን አለብን። ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ውስጥ ያሉ ችግሮች በሙሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ውስጥም አሉ። ይህንን አምነን የተሻለ ሁነን ለመገኘት ራሳችንን የመገምገም እና ውስጣዊ ዴሞክራሲን ለመለማመድ መሥራት አለብን” ይላሉ።
ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፣ “ችግር ስላለ ነው እዚህ ያለነው” በማለት ነው ነገሩን የሚያብራሩት። “ፓርቲ መመሥረት አንችልም፤ ማኅበረሰባችን ለድርጅት ግንባታ ገና ነው፤ አምባገነንም ድርጅቶች አማራጭ ሆነው እንዲያድጉ አይፈልግም፤ ይሄ ወደትግል የመጣንበት ምክንያት ነው። ስለዚህ… ወደትግል የመጣንበት ምክንያት ውጤት ሆኖ ከትግል ሊያስወጣን አያስፈልግም።… ሁሉ ነገር የተደላደለ ከሆነማ ቀድሞውን መምጣት አያስፈልገንም ነበር።” በማለት ችግሩ ስላለ ነው የገባንበት፣ ከውድቀቶቻችን እየተማርን እንቀጥላለን እንጂ ልንቀርፈው በገባነው ችግር ተገፍተን አንወጣም በማለት የፖለቲካ ትግሉ እስኪያፈራ ድረስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ እንዲቀጥል ይመክራሉ።
አንጋው ተገኝ በሠላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ያለ ወጣት ነው። ፀጉሩን ያጎፍራል። ሲናገር በብዙ ነገሮች እየተደነቀ ነው። አንጋው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የሰሜን ጎንደር አብረሃ ጅራ ወረዳ ኃላፊ በመሆን እጅግ ፈታኝ ጊዜያትን አሳልፏል። የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የሀገሪቱ ክፍሎች መንቀሳቀስ የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ መሆኑን ደጋግሞ ይናገራል። የፓርቲው አመራር ሁኖ በሠራበት ወቅት ፓርቲ ስብሰባ እንኳን ማድረግ እጅግ ከባድ መሆኑን ያስታውሳል። ፖሊስና የደኅንነት ኃይሎች አመራሮቹን እየተከታተሉ ሲያስጨንቋቸው ‹የፓርቲው ሥራ ከሚቆም በሚል አንገረብ ወንዝ ወርደን እየዋኘን እንሰበሰብ ነበር› ይላል። እየዋኘን ሰው ወደኛ በመጣ ቁጥር እየተበታተንን፤ ሰው ራቅ ሲልልን ደግሞ እዛው ውኃው ውስጥ ሰብሰብ ብለን እየተንሳፈፍን ነበር ስብሰባ የምናደርገው የሚለው አንጋው በፓርቲ እንቅስቃሴ ምክንያት ስድስት ጊዜ ከሥራ ተባሮ ስድስት ጊዜ መመለሱን ሲገልጽ አንዳንዴ በሕይወት መቆየቴም ለኔ ግርም ይለኛል እያለ ነው። ይባስ ብሎ በሠላማዊ ትግል ቆርቦ በዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የነበረው አንጋው ተገኝ የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ሳይቀርብበት አሁን ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት አለህ በሚል ምክንያት በመጨረሻ ለእስር የተዳረገ ሲሆን፤ እስር ቤት ሁኖም የታገለለትና የደከመለት አንድነት ፓርቲ ሲፈርስና በእሱ አባባል ‹መፈንቅለ አመራር› ሲካሄድበት ተመልክቶ ያዝናል። ለዚህ ሁሉ መሆን አንጋው ተጠያቂ የሚያደርገው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን ነው። ‹ሕግ የማይገዛው መንግሥት› እያለ ሁሌም ይገረማል። ይህ የኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ችግር የገዥው ፓርቲ ቅጥ ማጣት ነው ከሚሉት ወገን የሚቀርበው ሐሳብ ትክክለኛ ተምሳሌት ነው።
ከዚህ አሳዛኝ ኹነት መለስ ብለን አርብ ሚያዚያ 28፣ 2008 ከጠዋቱ 4፡30 እስከ 5፡30 ድረስ በአንድ ሰዓት ውስጥ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጆች ለጽሑፉ ግብዓት የሚሆን መረጃ ለማግኘት በማሰብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ መሠረት እንዲሁ አለፍ አለፍ እያልን በአሁኑ ወቅት በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ከሚገኙ ሰባ አምስት ፓርቲዎች መካከል የሃያ አምስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች የስልክ አድራሻ ላይ ስልክ የደወልን ሲሆን፤ ከሃያ አምስቱ ሙከራዎች መካከል ሁለቱን ስልኮች ያነሱልን ሕፃናት ሲሆኑ፣ የሰባቱ ስልክ ቢጠራም አይነሳም፤ የዐሥራ አምስቱ ስልክ ደግሞ ከነአካቴው የማይሠራ ሲሆን፤ የአንዱ ብቻ ማለትም ‘የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሕብረት’ ስልክ ላይ የፓርቲውን አመራር ልናገኝ ችለናል። በተመሳሳይ ጊዜ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያደረግነው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪም ስልኩ ሊነሳ ባለመቻሉ ማብራሪያ ማግኝት አልቻልንም። እንግዲህ ‹የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ሰሞን ግርግር ከመፍጠር ያለፈ ምንም አይፈይዱም የሚለው ሐሳብ እንዲሁ ያለውን ሁኔታ ቀረብ ብሎ ካለማየት የሚመጣ ነው› የሚሉ ተችዎችም ሁሌም የሚፈተኑበት ጉዳይም ይሄው ተቃዋሚ ፓርቲ ተብለው የተመዘገቡት ፓርቲዎች በሚገባቸው ቦታ አለመዋላቸው ነው። ፓርቲዎቹ የስልክ እንኳን አድራሻ የሌላቸው/ቢኖራቸው እንኳን የማይሠሩ ስልኮችን ይዘው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የለውጥ መሠረት ይሆናሉ ብሎ ማሰቡንም ያከብደዋል። ይህ ደግሞ ተቃዋሚዎች የራሳቸው ሥራ ሳይሠሩ ገዥውን ፓርቲ ማውገዛቸው ተገቢ አይደለም የሚለው ሐሳብ ተምሳሌት ነው።
ይህ ጽሑፍ በሃገር ቤት ታትሞ በወጣው ውይይት መጽሄት ላይ የወጣ ነው:: በሃገር ቤት ያላችሁ መጽሄቱን ገዝታችሁ በማንበብ ጋዜጠኞቹን አበረታቷቸው::
No comments:
Post a Comment