Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, May 20, 2016

የ ሰዉ facebook አካዉንት ዘረፋ መፍትሔ/ facebook hacking solutions



በጣም የብዙ ሰዉ አካዉንት ያለአግባብ ሲዘረፍ እያየን ነዉ፡፡ ያለአግባብ ያልኩበት ምክንያት መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ እየተዘረፉ ነዉ ለማለት ፈልጌ እንጂ አግባብ የሆነ ዘረፋ ኖሮ አይደለም፡፡ ወደ መፍትሔዉ እንለፍ፡-

1. በሜሴጅ የሚላክ የትኛዉንም ሊንክ አትክፈቱ፡፡ ምናልባት በምታምኑት ሰዉ በኩል ቢላክና ብትከፍቱት ራሱ User-name እና Password የሚጠይቃችሁ ከሆነ ወደ ኋላ ተመለሱ እንጂ አትክፈቱት፡፡ የምናዉቀዉ ሰዉ ነዉ ብላችሁም መሸወድ አያስፈልግም ምክንያቱም መጀመሪያ የዛ ሰዉ አካዉንት ሀክ ተደርጎ በእርሱ አካዉንት በኩል መጥተዉ ሊሆን ስለሚችል ነዉ፡፡ እንደዚህ አይነት ሊንኮች በሜሴጅ ብቻ ሳይሆን በየትኛዉም አጋጣሚ ሊላኩ ይችላሉ፡፡

(እንዴት እንደሚሰራ፡- ሊንኩን ስትጫኑ ከፌስቡክ ዉጪ ወደ ሆነ ሌላ ዌብሳይት ይወስዳችኋል፡፡ ያ ዌብሳይት ደግሞ ፌስቡክ የሚጠቀምበትን source code ኮፒ በማድረግ ልክ የፌስቡክ የሚመስል መግቢያ ገፅ ያሳያችሁና ተሸዳችሁ ፓስዎርዳችሁን ትሞላላችሁ፡፡ ከዛም ዌብሳይቱ ፓስዎርዳችሁን ለሌባዉ በኢሜል ይልክለታል፡፡)

2. ፌስቡክ የከፈታችሁበት በኢሜል ከሆነ የኢሜል አድራሻችሁን ለሰዎች አትናገሩ፡፡ ምክንያቱም እርሱን አዉቀዉ የኢሜል አድራሻችሁ ተሰበረ ማለት ፌስቡክን መስረቅ ቀላል ነዉ፡፡ የእናንተ ፌስቡክ ላይ ሄደዉ ፓስወርድ ጠፋብኝ በማለት ፌስቡክ በኢሜላችሁ በኩል አዲስ ፓስወርድ መቀየር ስለሚያስችል በዛ በኩል ትዘረፋላችሁ፡፡ ለሰዎች ኢሜል አድራሻ መስጠት ከፈለጋችሁ ከፌስቡክ ጋር የማይነካካ ሌላ አዉጡ እና ስጡ፡፡
(ምናልባት ፌስቡክ ኢሜላችሁንና ስልክ ቁጥራችሁን የሚያሳይ ከሆነ የፕሮፋይል Setting ውስጥ ገብታችሁ ማስተካከል ትችላላችሁ። በሞባይል ላይ እና በኮምፒውተር ይለያያል። ሀሳቡን ለማስያዝ ያህል ግን፦ መጀመሪያ Profile ላይ ሂዱ፣ ከዛ About፣ ከዛ ኢሜል እና ስልካችሁ ያለበት ጋር በመሄድ edit በሉትና Only Me የሚለውን በመምረጥ አድራሻውን መደበቅ ይቻላል)

3. እናንተ በሌላችሁበት ማንም ስልካችሁን አይንካ፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ፌስቡክን ያወጣችሁት በስልካችሁ ከሆነ ወደ እናንተ ፌስቡክ አካዉንት በመሄድ ፓስወርድ ጠፋብኝ ይላሉ፣ ከዛም በስልካቸችሁ ላይ ፌስቡክ ኮድ ይልካል፡፡ ስልካችሁ እጃቸዉ ላይ ስላለ ያንን ኮድ በማግኘት እና ፌስቡክ ላይ በማስገባት ፓስዎርዱን ቀይረዉ አካዉንታችሁን መዝረፍ ይችላሉ፡፡ ምናልባት ስልካችሁን እጃቸዉ ላይ ባያገኙ እንኳን ደዉለዉላችሁ ኮድ እናንተ ጋር በስህተት ተልኳል ንገሩን ሊሉ ይችላሉ፡፡ እናንተ ስልክ ላይ የተላከን ነገር ለሌላ ሰዉ አትንገሩ፡፡

4. በሌላ ሰዉ ኮምፒዉተር ወይም ስልክ ላይ ፌስቡካችሁን አትክፈቱ፡፡ ምክንያቱም የምታስገቡትን ዳታ እና የምትነኳቸዉን ቁልፎች የሚቀዳ የስለላ ሶፍትዌር መጫን ስለሚቻል ነዉ፡፡ የወዳጅ ኮምፒዉተር እና ስልክ ቢሆንም ይሄን አታድርጉ፡፡ ማንንም አትመኑ፡፡ ቢሮ ዉስጥ የምትሰሩ ሰራተኞች የቢሮዋችሁን ኮምፒዉተር ሲበላሽም ለባለሙያ ካልሆነ በቀር ማንም አይንካዉ፡፡ ፌስቡክን ብቻ ሳይሆን ብዙ ሚስጥር በነዚህ ሶፍትዌሮች መዝረፍ ስለሚቻል፡፡



ከላይ ያሉት ዋና ዋና የሚባሉ የዘረፋ መንገዶችን ነዉ የዘረዘርኩላችሁ፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጡ ዌብሳይቶችንም ሆነ የስለላ ሶፍትዌሮችን እንዲሁም የቴክኒኮቹን የእንግሊዝኛ ስሞች አልዘረዘርኩም፡፡ ይሄም ነገሩን ከዚህ በፊት የማያዉቀዉ ሰዉ እንዳይጠቀምበትና ዘረፋዉን እንዳያባብሰዉ ስለፈራሁ ነዉ፡፡

* ያም ሆነ ይህ ብዙ ወገኖቻችን ሰለባ እየሆኑ ነዉና እባካችሁን ይሄን ፅሁፍ አንብበን ስንጨርስ Share እናድርገዉ

No comments:

Post a Comment

wanted officials