“ተከሳሽ በሚጠቀምበት ማሀበራዊ ድህረ ገጽ በተለይም ፌስ ቡክ አድራሻዉን ተጠቅሞ በዉጭ አገር ከሚገኝ የሽብር ቡድኑ ግንቦት ሰባት አመራር እና አባል የሆነው ግርማ ካሳ ተብሎ የሚጠራ ግንኙነት በመፍጠር በሽብር ቡድኑ የተሰጠዉን ተልእኮ በማስፈጸም በቀን 27/2/2007 ዓ/ም፣ በ28/2/2007 ዓ/ም፣ በ10/6/2007 ዓ/ም፣ በ11/06/2007 ዓ/ም፣ በ18/06/2007 ዓ/ም፣ በ01/07/2007 ዓ/ም እየተገናኙ ስለ ግንቦት ሰባት እና አሸባሪ ተብለው የተከሰሱትን ቤተሰቦቻቸው እንዴት ሊደገፉ እንደሚችሉ የሚገልጽ የተለያዩ ይዘት ያላቸው መረጃዎች የተለዋወጡ በመሆኑ በዝርዝር ያደረጉት ንግግር በክሳችን በተጠቀሰው ማስረጃ የቀረበ በመሆኑ”…
ጋዜጠኛ ጌታቸውን ከከሰሱበት ፍሬከርስኪ ክሶች መካከል የተወሰደ ነው። የአንድነት ፓርቲ እውቅናዉን ከተነፈገ በኋላ የአንድነት ደጋፊዎችና ለሎች አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፣ የእስረኞች ኮሚቴ አቋቁመን፣ መጠነኛም ቢሆን የሕሊና እስረኞች ቤተሰቦችን (ኢኮኖሚካሊ ችግር ላይ ያሉትን) ለመደገፍ ጥረት ስናደርግ ነበር። በቂ ነበር? በቂ አልነበረም። ካደረገነው የበለጠ ማድረግ እንችል ነበር ? በሚገባ። ግን ትንሽም ብትሆን ከምንም ይሻላል።
አሁንም ያ ጥረት እየቀጠለ ነው። የአንድነት እስረኞችን ብቻ ሳይሆን፣ የመድረክ፣ የሰማያዊ፣ የመኢአድ፣ ጋዜጠኞና በዉሸት ክስ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከሰው የተፈረደባቸውንም ሳይቀር። የትም ድርጅት ይሁኑ ሁሉም የታሰሩት ለአገርና ለሕዝብ ነውና የሕሊና እስረኞች ናቸው። ጀግኖቻችን ናቸው።
በዚህ ረገድ የምናደርገው እንቅስቃሴን ነው እንግዲህ “ሽብርተኝነት” ተደርጎ ለክስ እያቀረበ ያለው። በዉሸት ክስ መከሰሳቸው ሳያንሳቸው፣ እስረኞችን ኢሰብዓዊ ጭካኔ እየፈጸሙ መደብደባቸው ሳያንሳቸው፣ የነርሱን ልጆች ለመዝናናት በፓሪስና በዱባይ እየላኩ የሌሎች እስረኞችን ልጆች ያስራቡት ሳያንሳቸው ፣ አሁን ደግሞ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ለእስረኞች ቤተሰቦች ድጋፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ “ሽብርተኝነት ነው” ይላሉ። ከዚህ የበለጠ ጭካኔ፣ ከዚህ የበለጠ አሪዮስነት ምን አለ ?
በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ አይምሮ አለን የምትሉ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች እንድትጽፉና የምትደግፉት ድርጅት አመራሮች ላይ ግፊት እንድታደርጉ በአክብሮት እጠይቃለሁ። ይኸው 25 አመት ደፈናችሁ። ምንድን ነው እየሆናችሁ ያላችሁት። በጫካ ከነበረችሁበት ጊዜ ሁሉ የባሰ አዉሬዎች እየሆናችሁ ነው ? እንዴት ነው ሳንወድ በግዳችን፣ የምንቃወመዉን ደርጅት እንድነቀላቀል ነው እንዴ የምትፈልጉት? እኛ የግንቦት ሰባት አካሄድ አያዋጣም እያልን እየተከራከርን፣ መልሳችሁ እኛን ” የግንቦት ሰባት አመራር አባል” ብላችሁ ስትሰይሙን እንደው አታፍሩም?
ለማጠቃለል ትንሽ ስለ ጌቾ ልጻፍ። ጌታቸው ሽፈራው ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን ለተቸገሩ የሚራራ፣ በተለይም ለእስረኞችና ለቤተሰቦቻቸው ትልቅ ሸክም የነበረው ትልቅ ሰው መሆኑን ነው በቀረበበት ክስ ከሳሾቹ ለአለም ሁሉ የነገሩለት። እኛ በፊት እናውቀዋለን። አሁን ግን ማንን እንዳሰሩ ሁሉም አወቋል። ጌታቸው የእስረኞች ጉዳይ በጣም ይከነክንው የነበረ ነው። የእስረኞች ወዳጅ ነው።
አሁንም እኛ ከመቼዉም ጊዜ በላይ አጋርነታችንን ለጌታቸውና ለሌሎች አሁንም በወህኒ እየተሰቃዩ ላሉ የበለጠ ማሳየት ይጠበቅብናል። በተለይም የእስረኞች ልጆች ፣ አረጋዊያን እናቶቻቸውና አባቶቻቸው ዳቦ ማጣት የለባቸውም።
No comments:
Post a Comment