Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, October 20, 2015

የአርበኞች ግንቦት 7 ሪከርድ የሰበረ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በሚኒሶታ * ነአምን ዘለቀ አርበኞች ግንቦት 7 መንፈስ ነው አሉ


የአርበኞች ግንቦት 7 ሪከርድ የሰበረ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በሚኒሶታ * ነአምን ዘለቀ አርበኞች ግንቦት 7 መንፈስ ነው አሉ (ሪፖርታዥ)


“የኤርትራ መንግስት ከራሷ ጋር የታረቀች ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ይፈልጋል”
“ሁሉንም ፖለቲካ ሃይሎች ያካተተ የሽግግር ሂደት ይኖራል”
“የወደብ ጥያቄን በተመለከተም ወደፊት በድርድር/በሰጥቶ መቀበል የሚፈታ ይሆናል እንጂ አሁን የትግሉ አጀንዳ መሆን የለበትም”
“የመረጃ ትንሽ የለውም… መረጃ አይናቅም”



(ዘ-ሐበሻ) በሚኒሶታ ትናንት ማምሻውን ለአርበኞች ግንቦት 7 ገቢ ማሰባሰቢያ የተደረገው ዝግጅት በታሪካዊነቱ እንደሚቀመጥ የሚኒሶታ ነዋሪዎች አስታወቁ:: በሚኒሶታ ታሪክ ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት በአንድ ቀን 78 ሺህ ዶላር በላይ ሲሰበሰብ የትናንቱ የመጀመሪያው ነበር::



ከ200 በላይ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በተሰባሰቡበት በዚሁ ታሪካዊ የአርበኞች ግንቦት 7 የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ ነአምን ዘለቀ እና ወጣት ሚካኤል ከላስቬጋስ ነበሩ:: ይህ የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት የተከፈተው የንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ከአስመራ በቭዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ነበር::



ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመልዕክታቸው እየተደረገ ያለው ትግል አንድን አምባገነን ጥሎ ሌላ አምባገንን ለመተካት ሳይሆን የተሻለች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት እንደሆነ አስምረውበታል:: ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋርም በኢትዮጵያ አንድነት በመተማመን በመነጋገር ላይ መሆናቸውን እና ጥሩ ነገር እንደሚሰማም የገለጹት ፕሮፌሰሩ በቶሎ ትግሉ እንደሚጀመር አስታውቀዋል::

በዕለቱ በአዳራሹ በክብር እንግድነት የተገኙት የንቅናቄው የውጭ ጉዳይ ሃላፊ አቶ ነአምን ዘለቀ ባሰሙት ንግግር “አርበኞች ግንቦት 7 መንፈስ ነው” ብለዋል:: ይህን ሲያብራሩም “የአርበኞች ግንቦት 7 ተዋናዩም ተመልካቹም ሕዝቡ ነው:: ንቅናቄው ዘረኝነትን በተንገሸገሸ – እኩልነት; ፍትህ እና ሰላም በተጠማው የኢትዮጵያ ተማሪ… ወጣት… ገበሬ.. ሴት… ወንድ ውስጥ ያለ ሕዝባዊ ትግል ነው:: ይህም ማለት በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ንቅናቄው አለ ማለት ነው:: ይህ መንፈስ ሥር እየሰደደ ሄዷል:: አሁን ባለው ዘረኛው ስርዓት ብዙዎች ተገድለዋል… በግፍ ታስረዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተንገላተዋል:: እነዚህ ሁሉ ሚሊዮኖች በውስጣቸው የአርበኞች ግንቦት 7 መንፈስ አላቸው::”

አቶ ነአምን ንግግራቸውን ቀጥለው “የወያኔ ፋሽስታዊ አገዛዝ በግፍ ብዙዎችን ከመሬታቸው ፎቅ ካልሰራችሁ እየተባሉ እንዲገፉ አድርጓል:: ቦታቸው ተቸብችቧል:: እነዚህ ዜጎች መሥእረታዊ የዜግነት መብታቸውን ተነጥቀዋል:: በጋምቤላ በደቡብ እየተደረገ ያለው ይኸው ነው:: የዘር ማጥፋት እየደረሰባቸው ነው:: እነዚህ የወያኔ ሰለባ የሆኑ ወገኖቻቸን ዴሞክራሲን የሚናፍቁ ናቸው:: ብዙ ኢትዮጵያውያን ካለፍርድ በ እስር ይማቅቃሉ:: ፍርደ ገምድሉ ሥር ዓት በፍትህ ላይ ቀልደዋል:: በነዚህ ሚሊዮኖች ውስጥ ሁሉ የአርበኞች ግንቦት 7 መንፈስ አለ” ብለዋል::

“በኮንትሮባንድና በዘረፋ የተሰማሮ 90% የሕወሓት ጀነራሎች እና መኮንኖች ሃብታም በሆኑበት መከላከያ ሠራዊት ውስጥ… አርበኞች ግንቦት 7 አለ:: ሠራዊቱ በከንቱ የወያኔ ጣልቃ ገብነትና ወረራ ደማቸው ደመከልብ ለመሆን ችሏል:: ይህ ሠራዊት እኩልነትን የተጠማ ሠራዊት ነው::” በማለት አሁን ስላለው የሕወሓት/ኢሕ አዴግ ሠራዊት ስለሚደርስበት የዘር መድልዎ የጠቀሱት አቶ ነአምን የትግሉ መዳረሻ የት ነው? በሚለው ንግግራቸው አርበኞች ግንቦት 7 መዳረሻ ዴሞክራሲያዊ ሥር ዓት መገንባት እንደሆነ ገልጸዋል:: አሁን ያለው ሥርዓትም በኃይል የወጣ የመጨረሻው አምባገነን ሥርዓአት ይሆናል ብለዋል::

“ሁሉንም ፖለቲካ ሃይሎች ያካተተ የሽግግር ሂደት ይኖራል:: ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር ቁጭ ብለን የምንነጋገርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም” ያሉት አቶ ነአምን በ3ኛ ደረሻ ስለ ኤርትራ መንግስት አብራርተዋል::

“የኤርትራ መንግስት ከራሷ ጋር የታረቀች ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ይፈልጋል:: እንድትበታተን ይሰራል ብለን አናምንም:: ኢትዮጵያን የማዳከም ስልት ወይም ፖሊሲ ኤርትራ አላት ብለን አናምንም:: በጣም ጤናማ ስኬታማ ኢትዮጵያ እንድትኖር የኤርትራ መንግስት እንደሚፈልግ ነው የምናውቀው” በማለት የተናገሩት አቶ ነአምን አርበኞች ግንቦት 7 ከኤርትራ መንግስት ጋር ኢትዮጵያን በሚመለከት ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች; በወደብ ጥያቄ ለመደራደር ምንም ዓይነት ስልጣን እንደሌለው እንዲሰመርበት እፈልጋለሁ ብለዋል::



“የወደብ ጥያቄን በተመለከተም ወደፊት በድርድር/በሰጥቶ መቀበል የሚፈታ ይሆናል እንጂ አሁን የትግሉ አጀንዳ መሆን የለበትም” ያሉት አቶ ነአምን በ4ኛ ደረጃ በውጭ ከሚገኘው ኢትዮጵያዊ ይህ የነፃነት ትግል ምን እንደሚጠብቅ አብራርተዋል:: በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ይህን ትግል በዲፕሎማሲው; በቁሳቁስ እና በገንዘብ ሊደግፍ እንደሚገባ ያስታወቁት የንቅናቄው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ “በውጭ ያለው ኃይል በየከተማው ያሉትን ሴናተሮችን እና ኮንገረሶችን ስለኢትዮጵያ መንግስት ጥፋቶች ሊነግሩ ይገባል:: በየከተማው ባሉ ሚዲያዎች እየወጡ በመጻፍና በመናገር የዲፖሎማሲው አካል በመሆን ትግሉን ማገዝ ይገባቸዋል:: የህክምና ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዎችም እንዲሁ በመድሃኒት አቅርቦት ላይ ብዙ ይጠበቅባቸዋል” ያሉት አቶ ነአምን አርበኞች ግንቦት 7 ጠላትን በተመለከተ ትልቅ የመረጃ ማሰባሰቢያ ኔትወርክ እንዳለው ጠቁመው ሁሉም ኢትዮጵያዊ መረጃዎችን ለድርጅቱ በተዘራጋው መዋቅር በኩል እንዲያስተላለፍ ጠይቀዋል:: “የመረጃ ትንሽ የለውም… መረጃ አይናቅም” ያሉት አቶ ነአምን በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ በስር ዓቱ ላይ እስካሁን እያሳየ ያለውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት እንዲቀጥል አበክረው ጠይቀዋል::

ከነመሪዎቹ አስመራ ለሚገኘው አርበኞች ግንቦት 7 መርጃ የተደረገው ጨረታ ላይ የግንባሩ ሴት ታጋዮች ምስል ቀርቦ 20 ዶላር ከተሸጠ በኋላ ወደ ጥያቄና መልስ ተገብቷል::

ፖስትሮድ የሚገኙ የኤርፖርት ታክሲ ሾፌሮች 10 ሺህ ዶላር አዋጥተው ሰጥተዋል::

በስፍራው “የፈራ ይመለስ” የሚል ቲሸርትና ህፃናትን ሳይቀር ያሳተፈ የገንዘብ ልገዛ ለግንባሩ ተደርጓል::

ከተሰብሳቢውም በአሁኑ ወቅት የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በሃይማኖቶች ውስጥ ጣልቃ በመግባት በተለይ ተሃድሶ የሚባል ነገር በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ በመፍጠር ሕዝቡን ለማለያየት አውቆ እየሠራ መሆኑን አርበኞች ግንቦት 7 እንዴት እንደሚመለከተው; ሞላ አስገዶም የትህዴን ሠራዊቱን ይዞ ወደ ወያኔ ሲገባ ከግንባሩ በቂ ምላሽ አልተሰጠም የሚል; አቶ ነአምን በቭኦኤ ላይ ቀርበው ስለአሜሪካዊ ዜግነት እንዳላቸው ሲጠየቁ ለምን መመለስ እንዳልፈለጉና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል::

አቶ ነአምን አሁንም የአሜሪካዊ ዜጋ ስለመሆናቸውና ስላለመሆናቸው መናገር እንደማይፈልጉ ገልጸዋል:: ይልቁንም በቅርብ ጊዜ የሕወሓት አስተዳደር “የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ስለሆኑ እንከሳቸዋለን” ማለቱን ጠቅሰው “ይምጣና ይሞክረን:: እንደውም ክስ ቢመሰርቱብን ጥሩ ነው:: በክሱ ሂደት ምን ዓይነት ወንጀሎችን እንደሰሩ እናሳያቸዋለን” ብለዋል:: አቶ ነአምን አክለውም የሰሞኑ የወያኔ ድንፋታ የአሜሪካንን ሕግ ካለማወቅ የመጣ መሆኑን አስምረውበታል::


“… የወያኔ መሪዎች በዘር ማጥፋት ወንጀል መዘፈቃቸውን የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በየጊዜው የሚያወጣውን ማስረጃ ማየት ነው። ይሄን ረስተው በአሜሪካ ፍርድ ቤት የአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪዎችን እንከሳለን የሚሉት ፍርድ ቤቱን እነሱ እንደሚቆጣጠሩት አለመሆኑን ካለማወቅ ነው ።ሌላው ቀርቶ ፕሬዝዳንቱ ፍርድ ቤት የማዘዝ ስልጣን እንደሌለው አያውቁም…እኛ እነሱ በሐውዜን ያደረጉትን ድራማ አንሰራም”

በሞላ አስገዶም ዙሪያ ለሕወሓት መንግስት በቂ የሆነ ምላሽ አልተሰጠበትም ለሚለው ጥያቄም “በቂ ምላሽ ስለሰጠንበት እኮ ነው ዛሬ ይህን ሁሉ አዳራሽ ሙሉ ሰው ያያችሁት” ሲሉ መልሰዋል::

የአርበኞች ግንቦት 7 የገቢ ማሰባሰብ በተለይም የአቶ ነአምን ዘለቀ ንግግርን ማንኛውም ጋዜጠኛ እንዳይቀርጽ መከልከሉ ተሰብሳቢውን አሳዝኗል:: በተለይ አርበኞች ግንቦት 7 ለመናገር ነፃነት እታገላለሁ የሚል ድርጅት በመሆኑ እንዲህ ያለው የጋዜጠኛ ክልከላ ገና ከጅምሩ እንዲህ ከሆነ የወደፊቱ ያሳስበናል የሚሉ አስተያየቶችም ተደምጠዋል:: በአጠቃላይ ግን አርበኞች ግንቦት 7 በሚኒሶታ የተሳካ ገቢ ማሰባሰብ ማድረጉን በሙሉ አፍ መመስከር ይቻላል::

source : zehabesha

No comments:

Post a Comment

wanted officials