Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, October 5, 2015

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የልብ ህክምና ስፔሻሊስት አስራለች

12106927_10205145682302555_7926962653447447435_n 

የልብ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት የነበሩትን ፕሮፌሰር አስራት ወ/የስን ለእስር ዳርጎ በልብ ህመም ይሰቃዩ በነበሩ ዜጎች ህይወት የፈረደው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ከአስራት በኋላ በኢትዮጵያ የታዩትን የዘርፉ ባለሞያ ዶክተር ፍቅሩ ማሩን በሙስና ወንጀል ጠርጥሪያቸዋለሁ በማለት ካሰረ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ የገቢዎች ሚኒስትር ከነበሩት የብአዴኑ አቶ መላኩ ፈንታ ጋር ለእስር የተዳረጉት ፍቅሩ በልብ ህክምና ስፔሻላይዝድ ያደረጉት በስዊዲን አገር ቢሆንም አገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ በማለት አዲስ የልብ ህክምና ማዕከልን ከፍተው ነበር፡፡ዶክተሩ በራሳቸው ወጪ ዶክተሮችን ወደ ስዊዲን በመላክም በዘርፉ ስፔሻላይዝድ የሚያደርጉ ባለሞያዎች እንዲፈጠሩ ማድረጋቸውም ይነገርላቸዋል፡፡

ዶክተሩ ከአንድ የሞያ አጋራቸው (ዶክተር በቀለ ጋር በሽርክና )በከፈቱት ሆስፒታል የልብ ምታቸው የቀነሰ ታካሚዎች ምታቸው እንዲስተካከልና የተዘጉ የልብ የደም ስሮችን የሚያፍታታ ህክምና መስጠት ጀምረው የነበረ ቢሆንም ከታሰሩ በኋላ ህክምናውን የሚሰጥ ባለመገኘቱ እየተመላለሱ ይታከሙ የነበሩ ህሙማን ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡ አርቴፊሻል መሳሪያ ተገጥሞላቸው በየስድስት ወሩ እየተመላለሱ ህክምናቸውን ያደርጉ የነበሩ የልብ ህሙማን ፍቅሩን ማግኘት ባለመቻላቸው ለሞት የተዳረጉ መኖራቸውንም የሚናገሩ አልጠፉም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሜዲካል ስኩል ፍቅሩ ያለ ክፍያ እውቀታቸውን ማካፈልም ጀምረው ነበር፡፡በስዊዲን ዩኒቨርስቲዎች ዳጎስ ያለ ገቢ ይዝቁበት የነበረን የመምህርነት ሞያቸውን ለአገር ፍቅር የገበሩትን ፍቅሩን በሙስና ማሰር ቤት እንደማይመታ የቅርብ ሰዎቻቸው ይናገራሉ፡፡

 ዶክተሩ የህክምና አገልግሎት ሲሰጡባትና ሲያስተምሩባት ከነበረችው ስዊዲን ጋር ጠንካራ ግኑኝነት የነበራቸው በመሆኑም ስዊዲናዊያን የልብ ሐኪሞች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የልምድ ልውውጥ ሲያደርጉ ነበር፡፡ከዶክተሩ እስራት ጀምሮ ግን ስዊዲናዊያኑ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አያውቁም፡፡ የዶክተሩ መታሰር ብዙ ችግር እንደፈጠረ የተረዳው የኢትዮጵያ የግል ሐኪሞች ማህበር ለፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ለዳያስፖራ ዴስክ ደብዳቤ ደብዳቤ በመጻፍ ዶክተር ፍቅሩ እንዲፈቱ ተማጽኗል ፡፡

 እንደ ሪፖርተር ዘገባ ከሆነ ደብዳቤው በማኅበሩ የተጻፈው ጳጉሜን 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ቢሆንም፣ እስካሁን ከማናቸውም ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘቱ ታውቋል፡፡ዶክተር ፍቅሩ በስዊዲን ነዋሪ የሆነች አንዲት ሴት ልጅ አለቻቸው፡፡ የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌይማን ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ ትልልቆቹን አሳዎች የማናጠምደው ‹‹ልማቱ እንዳይደናቀፍ በማሰብ ነው››ማለታቸው አይዘነጋም፡፡በዶክተሩ መታሰር የስንቱ ህይወት እየተደናቀፈ መሆኑስ አልታያቸው ይሆን? መቼም ወንጀል የፈጸመ ሰው መታሰር የለበትም በማለት ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ሊከራከር ባይችልም እንደ ኢትዮጵያ ለፖለቲካ ገረድ የሆነ ፍርድ ቤት ባለበት አገርና ንጹሐን ለዓመታት እየታሰሩ ነጻ ናችሁ መባላቸውን እየተመለከትን የእስራታቸው መንስኤ ሙስና ነው ለማለት አንደፍርም፡፡ በሙስና ተብለው የታሰሩ የከተማችን ሐብታሞች እስር ቤቱን ማደሪያ ብቻ ሲያደርጉት እየተመለከትን በዶክተሩ ላይ በር ቆልፎ በቀጠሮ እየተመላለሱ ህክምና ያገኙ የነበሩ ህመምተኞችን (በሽታው ጊዜ እንደማይሰጥ እየታወቀ) በሞት መቅጣት ለዜጎቹ ዋጋ ከሚሰጥ አካል የሚጠበቅ አይደለም፡፡
by
 Dawit Solomon Yemesgen

No comments:

Post a Comment

wanted officials