Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, October 14, 2015

የወያኔ ስራ በቤተክርስትያናት ላይ!! Government interference on Ethiopian church


የወያኔ ስራ በቤተክርስትያናት ላይ!! በዘመናችን ያለ የቤተክርስቲያን ትልቁ ፈተና – ጉዞ ወደ እናት ቤተክርስቲያን (እንቀላቀል) ለምን ትልቅ ፈተና ሆነ ስንል?



ከጌታቸው ካሳሁን

የእስከዛሬዎቹ ጥቃቶች የሚፈፀሙት ከቤተክርስቲያን ውጪ በሆኑ ሰዎችና ተመሳስለው በገቡ ማንነታችውን በደበቁ ሰዎች ሲሆን ይህኛው ግን ለየት የሚያደርገው የሃይማኖት ሽፋን ያለው እንዲሁም እውቅና በሰጠናችውና በፈቀድንላቸው ጥፋታቸውን እራሳቸውን ሳይደብቁ በግልፅ እያሳዩን እንኳን ዝም ብለን የተቀበልናቸው የቤተክርስቲያን አማሳኞች አባቶችና ምዕመናን የሚከናወን በመሆኑ ነው።እንግዲህ ወደ ጉዳዩ ስንገባ በመጀመሪያ ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ርትዕት ናት በዶግማ ምንም ችግር የለባትም ነገር ግን በአስተዳደር ችግር ምክንያት ለሶስት ቦታ ተከፍላለች ። ልብ በሉ በዶግማ አላልኩም በአስተዳደር ምክንያት ነው ያልኩት።

በአስተዳደር ለ3 ( ሶስት) ቦታ የተከፈሉትን እንደዚህ እናያቸዋለን
በኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ ስር የሚተዳደሩ
በአሜሪካን ሀገር ባለው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር የሚተዳደሩ ሲሆኑ፡
ገለልተኛ ቤተክርስቲያን፡-የሚባሉት ደግሞ በአሁን ግዜ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስትያን ሁለት ፓትርያርክ ስለሆነ ያላት ለየትኛውም ፓትርያርክ አንወግንም የሚሉና ገለልተኝነታቸው ከሁለቱ አባቶች እንጂ ከቤተክርስትያኒቱ ያልሆነ እንዲሁም እርቀ ሰላም ወርዶ አንድ ሲኖዶስ በቦታው እስኪመለስ ድረስ ለየትኛውም አንወግንም የሚሉ ናቸው።

ነገር ግን በሶስቱም አስተዳደር ስር ያሉት ቤተክርስቲያኖች መተዳደሪያ ደንባቸው በቅዱስ ሲኖዶስ የተዘጋጀው ቃለ ዓዋዲ ሳይሆን ከቤተክርስትያኑ አባላት በተውጣጡ ጥቂት ሰዎች በሚቀርጹት መተዳደሪያ ደንብ ነው። ቤተክርስቲያንነታቸው የአንዲት (እናት) ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲሆን፤ አንዱ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ሌላው ደግሞ እንጀራ ልጅ ሊባሉም አይችሉም። እንዲሁም ምእመኖቻቸው የአንዲት እናት የኢ/ ኦ/ተ ቤተክርስቲያን ልጆች ናቸው። ጊዜ ያመጣው ፖለቲካ አስተዳደሩን ለሶስት ከፈለው እንጂ ሁሉም አሃዱ አብ ቅዱስ ብለው የሚቀድሱ እና የሚያመሰግኑ ልዩነት የሌላቸው በአንድ አምላክ የሚያምኑ ናቸው።

በዚህ ጊዜ በአንድነት ስም ቤተክርስቲያንን መክፈል ያስፈለገበት ምክንያት

ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው መንግስት ከጫካ ጀምሮ አንግቦ በመጣው የኢ/ኦ/ተ ቤተክርስቲያንን የማፍረስ ዓላማ በተለያዩ ጊዜያት ቤተክርስቲያንን ሲያቃጥል፣ ሲያስፈርስ፣ ሲያርስ፣ ታሪኳን በጠራራ ፀሀይ ሲያጠፋ የሀይማኖት ቦታዋን እየነጠቀ ለሌላ ሲሰጥ ስለ ቤተክርስቲያን ብሎ አንድም የተናገረላት አባትም ሆነ የበላይ አካል ዝም ብሎ ከማየት ወጭ ያደርጉት አስተዋፆ የለም። በትንሹ ቢሆን በየአካባቢው ያሉ ምእመናን አትንኩ ቤተክርስቲያኔን ሲሉ በአፀፋው እስር፣ እንግልት፣ መገደል ደርሶባቸዋል። በእኛ ዝምታ መንግስት ተግባራዊ አድርጎታል ነገር ግን በተቻለው ፍጥነት የማፍረስ ሂደቱ እንዳይከናወን ሁለት ነገሮችን ይፈራል።
ማህበረ ቅዱሳንን፡- ማህበሩን ለምን ይፈራዋል ስንል የቤተክርስቲያን የጀርባ አጥንት ነው በሎ ስለሚያስብ ስለዚህ ማህበሩን ለማፍረስ በተለያየ ጊዜ ብዙ ሙከራ ቢያደርግም አልሳካ በማለቱና ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ የሚደረገውን እሩጫ ማህበሩ ባያቆመውም ወደ ኋላ ስለጎተተበት እንዲሁም ውጤቱ እንዲያዘግም ስላደረገና መዋቅሩም በጣም ጥልቅና እስከ ታች ድረስ ዘልቆ ስለገባ ማፍረስ ባለመቻሉ በዚህ ጉዞ ወደ እናት ቤተክርስቲያን በሚል ከተቻለ ለማፍረስ አለበልዚያም ለማዳከም ነው።

ይህ አቅጣጫ እንዴት ማህበሩን ያፈርሳል ?



ጉዞ ወደ እናት ቤተክርስቲያን በሚል እውነትነት ያለው በሚመስል የሃይማኖት ሽፋን ነገር ግን ህዝብን ከህዝብ፤ ባልን ከሚስት፤ በአጠቃላይ የምእመናንን ልብ ለሁለት ከፍሎ እስከመለያየት የሚያደርሰውን አጀንዳ የማህበረ ቅዱሳን አጀንዳ አድርጎ በምእመን ዘንድ ሰርጾ እንዲገባ በማድረግ ማህበሩ በምእመናን እንዲጠላ ማድረግና ከተቻለ በዚህ አጋጣሚ ማህበሩን አፍራሽ አድርጎ በይፋ በማውጣት ማፍረስ ወይም ከምእመናን ልብ ውስጥ ማውጣትና ማዳከም ነው። እዚህ ጋር ግን የሚያሳዝነው የማህበሩ አባል በሆኑ ነገር ግን የማህበሩ ዓላማ ባልሆነው ነገር እነርሱን ከፊት በማሳየት መጠቀምና ተአማኒነትን ለማግኘት በመሞከር የማህበሩን ተልእኮ እያስፈፀሙ አስመስሎ በማሳየት በእነርሱ መጠቀም ነው።
ብዙ ህዝብ የተሰበሰበበት በዘር በጎሳ ያልትከፋፈለና ስርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቀ አገልግሎት የሚሰጥበትን ቤተክርስቲያንን ፦ እነዚህን ለምን ይፈራል ስንል አንድነትን አጥብቆ ስለሚፈራ ለስልጣኔ ያሰጋኛል ስለሚል። እንደዚህ ዓይነት ቤተክርስቲያኖች የሚገኙት ደግሞ በገለልተኛ ቤተክርስቲያን ስር ያሉት ጋር ነው። እነዚህ ቤተክርስቲያኖች አንድነታቸውን ጠብቀው ፍፁም ኢትዮጵያዊነት ስለሚታይባቸውና በቂ ባይሆንም ቤተክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን አደጋ በመግለጫም ቢሆን በጥቂቱ ይቃወማሉ። እንዲሁም በሰው ኃይል፣ በፋይናንስ እና ከእዳ ነፃ የሆነ ቤተክርስቲያን ባለቤትና በአገልግሎትም ጠንካራ ስለሆኑ መንግስት በስጋት ያያቸዋል። ይህን ቤተክርስቲያንን የመክፈል (የማዳከም) ስራ ማን ይስራው

እንግዲህ በአሁን ግዜ በቤተክርስትያኒቱ ውስጥ ሁለት አይነት ሰዎች ዲያቆናት፣ካህናትና እንዲሁም ጳጳሳት ከታች እስከ ላይ በተዋረድ ከስር አጥቢያ ቤተክርስትያን አንስቶ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ አሉ። እነርሱም፦

1. የመጀመሪያዎቹ ፡- በመንግስት ተመልምለው ለዚህ ለቤተክርስቲያን የማፍረስና የማዳካም ስራ ስልጠና ወስደው ከድቁና እስከ ጵጵስና ደረጃ ተምረው ወይም የነበሩትን በዘር፣ በስልጣን፣ በጥቅማ ጥቅም ተደልለው ቤተ ክርስቲያኒቱን ከአጥቢያ ቤተክርስትያን እስከ ቤተክህነት እንዲሁም ጵጵስና ደረጃ የያዙት ሲሆኑ

2.ሁለተኞቹ፡- ደግሞ በታማኝነት፣ በፍፁም ፍቅር ፣በፍጹም እምነት በቤተክርስቲያኒቱ ያደጉና ለቤተክርስቲያኒቱ ዘብ የሚቆሙ ህመሟ ህመማቸው የሆነ ችግሯ ችግራቸው የሆኑ ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን እስከ ጵጵስና ያሉ ሲሆኑ እነዚህኞቹ ግን በአጥፊዎቹ ተውጠው በፍፁም እንዳይንቀስቀሱና ድምፃቸው ወደ ውጭ እንዳይወጣ ታፍነው የተያዙ ናቸው። እንግዲህ ይህን ያህል ካልን ይህን የማፍረስ ስራ በበላይነት እንዲመሩ የተመረጡት ደግሞ ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ናቸው።

ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ፦ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን እንደዚህ ሳትከፋፈል በአንድ አስተዳደር ስር በነበችበት ግዜ ማለትም ሲኖዶስ አንድ መንጋውም እረኛውም አንድ በነበረበት ወቅት አቡነ ማትያስና አቡነ ጳውሎስ በገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን ሆነው አሁን ለአለው መንግስት ገንዘብ እየሰበስቡ ይረዱ የነበሩ፤ እንዲሁም በአሁን ጊዜ በስርዓት ቤተክርስቲያን ያልተሾሙና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የፕትርክና አሿሿም ስርዓትና ደንብ ያልተሾሙ በመንግስት ፊት አውራሪነት ስራዬን ይሰሩልኛል ብሎ በመንግስት ፈቃደኝነት የተሾሙ ፓትሪያርክ ሲሆኑ ይህን ደግሞ የቤተክርስትያኒቱ ፍትሃነገስት እንደሚቃወም ኤጲስቆጶሳት አንቀጽ 5 ቁጥር 175 ረስጠብ 21<< በዚህ አለም መኳንንት ቢረዳ ከእነርሱም ዘንድ ለቤተክርስትያን ቢሾም ይሻር እርሱና ግብረአበሮቹ ሁሉ ይለዩ ብሎ ይነግረናል>> ቤተክርስቲያንን የማፍረሻ (የመክፈያ) ዋና አጀንዳቸው ደግሞ ስርዓት ቤተ ክርስቲያን ፈርሷል የሚል ነው

ስለ ስርዓት ከመነሳቱ በፊት የቤተክርስቲያንን ስርዓቶችና እና አገልግሎቶች በጥቂቱ እንመልከት
ሠዓታት መቆም
ማህሌት መቆም
ቅዳሴ መቀደስ
ስብከት ወንጌል ካሉት ግልጋሎቶች በጥቂቱ እነዚህን ስናይ

እንግዲህ እነዚህ አማሳኞች የሚጠቀሙት አንዱን ቅዳሴን በማጉላት (በማዉጣት) ሌላው አገልግሎት ላይ ሥርዓት እንደሌለ በማድረግ ያውም የፓትርያርክ ስም አለመጥራትን እንድ ትልቅ ክህደት (ዶግማ) የተጣሰ ያህል በማራገብ ቤተክርስቲያን መክፈልን ተያይዘውታል። እነርሱን የሚያስጨንቃቸው የፓትርያርክ ስም መጠራት አለመጠራቱን እንጂ የቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎቶች ሰዓታቱ፣ ማህሌቱ፣ ስብከተ ወንጌሉ ፣ ቀኖናው፤ዶግማው ስርዓት የጠበቁ አገልግሎቶች መሆናቸው ላይ ግድ የላቸውም። ይህ ማለት በቅዳሴ ጊዜ ስም አለመጥራት ችግር አይደለም ሥርዓት አልፈረሰም ማለት አይደለም። ነገር ግን በቅዳሴ ጊዜ ስም መጥራት የቤተክርስትያኒቱን ስርአት ሙሉ ያደርገዋል ማለት አይደለም የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም የማይጠራበት ምክንያት እልባት ቢያገኝ የቤተክርስትያኒቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮችና የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓትና አገልግሎቶች ሙሉና አንድ ወጥ ይሆናሉ። የቤተክርስቲያኒቱ ሰላም አንድነት እንዲሁም አስተዳደር አንድ ይሆናል። አባቶች በቅዳሴ ጊዜ የፓትርያርክ ስም እንዲጠራ ሲደነግጉ በስርዓተ ቤተ ክርስቲያን የተሾመ ስርአቷንና ዶግማዋን ቀኖናዋን ጠብቀው የተሾሙ የፓትርያርክ ስም እንዲጠራ እንጂ ከቤተክርስትያን የፓትርያርክ አሿሿም ስርዓት ውጭ ማለትም በመንግስት የተሾሙትን እንዲጠራ የሚል አይደለም ስርዓት ከተባለ ደግሞ አንድ ፓትርያርክ ፓትርያርክ ሊባል የሚችለው የቤተክርስቲያን ስርዓትዋንና ደንቧን የጠበቀ የእግዚአብሔርን ህዝብ በስርዓት የሚጠብቁ ኃይማኖቷን ቀኖናዋን ዶግማዋን ተከትሎ በእኩል የእግዚአብሔርን ህዝብ የሚመሩ አባትን እንጂ ከእግዚአብሔር ህዝብ ጡንቻ ያለውን መንግስት የሚያስቀድምን አባት አይደለም።ለዚህ ፍትሃ ነገስቱ ኤጲስቆጶስ አንቀጽ 5 ቁጥር 175 ረስጠብ 21 <<በዚህ አለም መኳንንት ቢረዳ ከነርሱም ዘንድ ለቤተክርስትያን ቢሾም ይሻር እርሱና ግብራበሮቹ ሁሉ ይለዩ >>ነው የሚለው።

ለአብነት ያህል የኤርትራውን ፓትርያርክ እንመልከት። የኤርትራው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ አንቶኒዮስ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከጥር 13/ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከመንበራቸው አንስቶ የቁም እስረኛ ያደረጋቸው የኤርትራው መንግስት ነው። ምክንያቱም ደግሞ መንግስት ገዝቱ ያላቸውን 3000 ምእመናን አልገዝትም በማለታቸውና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ በመጠየቃቸው ሲሆን እርሳቸውም ከመንግስት ጡንቻ የእግዚአብሔር ይበልጣል በማለት አስካሁን በቁም እስር ላይ ይገኛሉ። መንግስትም አሳቸውን አስሮ በምትካቸው የመንደፈራውን አቡነ ዲዩስቆሮስን መሾሙ ይታወቃል።ይህን መረጃ በድሬቲዩብ January 22 2015 ላይ ተገልጾ እናገኛለን ልብ በሉ እውነት አሁን አባቶች ሥርዓቱን ሲሰሩ በቅዳሴ ሰዓት በመንግስት የተሾሙትን የአቡነ ዲዮስቆሮስ ስም እንዲጠራ ነውን? አይደለም። ትክክለኛው ስርዓት በእስር ላይ ያሉት የአቡነ አንቶኒዮስ ስም እንዲጠራ እንጂ በመንግስት የተሾሙትን አለመጥራት እንደውም ስርዓትን መጠበቅ ነው።በመንግስት እንደተሾሙ እየታወቀ መጥራት ስርአት ማፍረስ ነው። እንደ ኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስትያን ቀኖና መሰረት በአሁን ሰአት ቤተክርስትያን ፓትርያርክ የላትም ምክንያቱም ፓትርያርክ ይሰደዳል መንበር ግን አይሰደድም በስደት ላይ ያለው ሲኖዶስ ግን መንበር አቋቁሟል እንዲሁም የሃገር ውስጥ ሲኖዶስም በመንግስት በተሾመ ፓትርያርክ ተሰይሟል ቀኖና ቤተክርስትያን ደግሞ በመንግስት የተሾመ ይሻር ይላል እኔ ሳልሆን ቀኖናው ይሽራል ስለዚህ የትኛው ስም ይጠራ ?

እነዚህ አማሳኞች እውነት አንድነት ከሆነ ዓላማቸው ለምን ቃለ አዋዲውን አይቀበሉም? ለዚህ የሚመልሱት ደግሞ ከአሜሪካን ሀገር ጋር የማይስማማ ስላለው ነው ባይሎ የምንቀርፀው ይላሉ። ምክንያቱም የተነሱበት ዓላማ ያ ስላልሆነ ነው፤ እንጂ ከአሜሪካን ሃገር ጋር የማይስማማ ቢሆን እንኳን ጥያቄ ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርበው ቅዱስ ሲኖዶስ ከአሜሪካ ሃገር ህግ ጋር የሚስማማ ሊያወጣላቸው ይገባል እንጂ ማንም ሰው ተነስቶ ቃለ አዋዲውን ሊያሻሽል አይችልም። ምክንያቱም የማሻሻልም ሆነ የማስተካከል ስልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ስለሆነ ። እንዲሁም እነዚህ በኢትዮጵያ ስር ነን ብለው ቃለ አዋዲውን የማይቀበሉት አንድ ባይሎ(መተዳደሪያ) እንኳን የላቸውም። ለምሳሌ በአንድ እስቴት ውስጥ 10 ቤተክርስቲያን ቢኖር እንኳን 10 የተለያየ ባይሎ(መተዳደሪያ) ነው ያላቸው እንጂ ለአስሩ እንኳን አንድ ባይሎ(መተዳደሪያ) የላቸውም ምክንያቱም ዓላማው መለያየት ስለሆነ ባይሎው አንድ ከሆነ አንድነትን ስለሚያመጣ አያስፈልግም። ይህን ደግሞ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ፓትርያርኩን ጨምሮ በማፍረስ ስራ ላይ የተሰማሩት አንድም ምእመናንን በመከፋፈል በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት እድሜ ማራዘም ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የራሳቸውን የወደፊት መውደቂያ እያመቻቹ ነው። መንግስት ተቀይሮ ወይም በሆነ ምክንያት የቤተክርስቲያን አንድነት ቢመለስ እነዚህን ቤተክርስቲያኖች ገለልተኛ ለማድረግና ሸሽተው መጥተው በቁጥጥራቸው ስር አድርገው የቤተክርስቲያናችን ትንሳኤ እንደገና ወደ ኋላ ለመጎተት የታለመ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምእመን ሆይ ይህ ሁሉ ደባ በቤተክርስቲያን ላይ ሲሰራ ከዚህ ነገር ላይ ጥቂት ተጠቃሚዎች ካህናትና ግለሰቦች ስላሉ ጉዳዩን በደንብ አጢነን ዝም ብለን ከምንከተል ተው ልንላቸው ይገባል።

ይህ የአስተዳደር ችግር በምእመን የሚፈታ ችግር አይደለም የጀመሩትም አባቶች ናቸው የሚፈቱትም አባቶች ናቸው። ሁለቱ አባቶች ከፈለጉ አንድ ያደርጉታል ከፈለጉ እንደበተኗት ያስቀሯታል። ሁለቱ ከታረቁ ሁሉም መንጋውም ግን እረኛውም አንድ ይሆናል። ምእመን ቤተክርስትያንን አንድ እናድርግ ቢል ግን ሁከትና እረብሻ ነው የሚፈጠረው ምክንያቱም አባቶች አይፈልጉማ። አንድነት እንዳይመጣ እጃቸውን ያስገባሉ። ስለዚህ እኛ ምእመናን ግን ስደተኛ ገለልተኛ በኢትዮጵያ ሳንል አንድነታችንን ጠብቀን በያለንበት ቤ/ተክርስትያን እየተገለገልን በፍጹም ወንድማማችነት መፍትሔ እስኪመጣ ድረስ እግዚአብሔርን እየጠየቁ መኖር ያስፈልጋል።

እነዚህ አማሳኞች በተለያዩ ቦታዎች ከሰሯቸው የማፍረስ ስራዎች ውስጥ ለኣብነት ያህል በሚኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢ/ኦ/ተ/ ቤተክርስቲያን ያደረጉትን እንመልከት

በመጀመሪያ የሜኒሶታ ደ/ሰ/መ/ቤተክርስትያን ማን ናት?በሜንሶታ ካሉ አብያተክርስቲያናት አንዱ ላይ ያዉም ደብረሰላም መድኃንያለም የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስትያን ለምንተመረጠ?

ደብረሰላም መድኃኒዓለም የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስትያን ከተመሰረች ከ1993 እ. ኤ. አ.በገለልተኝነት የምትታወቅ ሲሆን በተለያዩ ጳጳሳት የተባረከችና በአሁን ጊዜም የተለያዩ ጳጳሳትና የቤተክርስትያን ታላላቅ አባቶች ከኢትዮጵያ ድረስ በመምጣት ምክር ትምህርትና ቡራኬ ያልተለያት እንዲሁም በአሜሪካን ሀገር አሉ ከሚባሉት ታላላቅ አድባራት በአሁን ሰዓት ግንባር ቀደም ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም በአሁን ግዜ አገልግሎቷን በማስፋት በአመት 365 ቀናት ማለትም አመቱን በሙሉ ለተገልጋዮች ክፍት በመሆን የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ብቸኛዋ ቤተክርሰትያን ናት ቢባል ማጋነን አይደለም።

በደብረሰላም መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን የሚሰጡ አገልግሎቶች
(1)ዘወትር ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ከጠዋቱ 6am – 10am ለጸሎት ክፍት ሆኖ የእጣን ጸሎት እና የኪዳን ጸሎት ይደረጋል።
(2)ዘወትር እሁድ የሰንበት ቅዳሴ ከነግህ ጸሎት ጋር ከንጋቱ 5am ጀምሮ ይሰጣል።
(3)ዘወትር የአዘቦት ቅዳሴ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ባሉት ቀናት ወር በገባ የሚካኤል ፣ ፣ የኪዳነምህረት፣ የገብርኤል

የማርያም እና የመድኃኒዓለም ቀን ይቀደሳል።
(4) በአመት 8 ግዜ አመታዊ በአለ ንግስ ይደረጋል።በሁሉም በዓላት የዋዜማ አገልግሎት ከ3pm ጀምሮ ይሰጣል።

እንዲሁም በበዓሉ ቀን በማህሌት ከ2am ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ በድምቀት ይከበራል። እንዲሁም ከዓመታዊ

በዓላት በተጨማሪ የጽጌ ፤ የደብረታቦር ፤የስብከት፤የኖላዊ፤የልደት፤ የጥምቀት፤የሆሳእና፤የትንሳኤ፤ የዳግማ ትንሳኤ እና የጰራቅሊጦስ ማህሌት ይቆማል።
(5)በዓብይ ጾም 5 ቀን ሙሉ ስርአተ ሰሙነህማማት ከጠዋቱ 6am ጀምሮ ይከናወናል።
(6)14 ቀን የፍስለታ ሱባኤ በለሊት ሰዓታት፤በውዳሴ ማርያም ትርጓሜ እና በቅዳሴ አገልግሎት ይሰጣል።
(7)የመስቀል በዓል በየዓመቱ ኢትዮጵያዊ በሆነ መልኩ በድምቀት ይከበርል።
(8)ዘወትር ሐሙሰ ከምሽቱ 5pm ጀምሮ የስብከተ ወንጌል ትምህርት ይሰጣል ።
(9)ዘወትር እሁድ ከቅዳሴ በሁዋላ ማህበረ ካህናቱ እና የሰንበት ት/ቤት መዘምራን በህበረት የየእለቱን እና የየባእላን ያሬዳዊ ዜማ (ወረብ) ይዘመራል።እንዲሁም ከአገልግሎት በሁዋላ የባእላቱ ቀለም ይጠናል።
(10)ዘወትር እሁድ ከቁርባን በሁዋላ ለህጻናትና ወጣቶች መንፈሳዊ እና የቋንቋ ትምህርት ይሰጣል።
(11)ለቤተክርስትያን ዓባላት መረዳጃ እድር ይሰጣል።
(12) በኢትዮጵያ ለሚገኙ የተለያዩ አድባራትና ገዳማት በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ ያደርጋል።

በተጨማሪም ቤተክርስትያኒቱ ከእዳ ነጻ ፤የዘር፤የጎሳ፤ልዩነት ሳይኖራት ከሁሉም አይነት የብሄር ተዋጽኦ በእኩል ፍጹም ኢትዮጵያዊነትን በተሞላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ህጉዋን፣ ስርአቷን፣ ቀኖናዋንና ዶግማዋን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት እስከ አሁን ድረስ በመድኃኒዓለም ሃይል ያለች እና ወደፊትም የምትኖር በተጓዳኝም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የህንጻ ዲዛይን አሰራር መሰረት በእዚህ በሜንሶታ ለቤተክርስቲያኒቱና ለሃገራችን እንዲሁም ለተተኪ ትውልድ አሻራ ጥሎ ለማለፍ ባለ 3 ጉልላት ያለው የተለያዩ የአገልግሎት ዘርፍ መስጠት የሚችል ካቴድራል ለመገንባት እንዲሁም ቤተክርስትያኒቱን በውጭው ዓለም ከፍ አድርጎ ሊያሳይ የሚችል እና ዶግማዋና ቀኖናዋ ተጠበቆ ሳይበረዝ ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረገው ርብርብ ለቤተክርስትያኒቱ እጅግ ጠቃሚና ለመንግስት ደግሞ እራስ ምታት ስለሆነበት የመንግስት አይን አረፈበት ።

እስቲ ልብ በሉ ይህን ሁሉ አገልግሎት እና ስርአት ጠብቃ የያዘች ቤተክርስትያን ልትደገፍና ልትበረታታ ይገባታል እንጂ ይህንን ሁሉ ስርአተ ቤተክርስትያንን እና አገልገሎትን ወደጎን ትቶ የአቡነ ማትያስን ስም አልተጠራም ተብሎ በአንድ ቀን ቤተክርስትያንን አፍርሶ መሔድ ባልተገባ ነበር። ይሁን ስህተት እንኳ ተገኝቶም ከሆነ በምክር በትምህርት መስተካከል ሲችል በክፉ መተያየትን እና መለያየትን ባላመጣን ነበር። እዚህ ጋ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የተናገሩትን ጠቅሼ ልለፍ [በዘልማድ ሆኖ ገለልተኞች ብለው ፈረጇቸው እንጂ በሀገረ ስብከትም እንተዳደራለን የሚሉ የራሳቸውን ባይሎ ቀርጸው የሚተዳደሩ እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቃለ አዋዲን አንድም የሚተገብር ቤተክርስቲያን በመላው አሜሪካ አለ ብዬ አልጠብቅም………እንዲሁ ገለልተኛ ብሎ ማራቅ ለቤተ ክርስቲያን ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ያልተወገዙና ያልተለዩ አካላት መሆናቸው እየታወቀገለልተኛ ብሎ ማራቅ አይገባም። ልዩነት ሊኖር ይችላል ይህን አምነን መቀበል አለብን። የአስተዳደር እንጂ የሀይማኖት ልዩነት የለንም ሁሉም በስርዓት የሚቀድሱ ማህሌት የሚቆሙ ክርስትና እየተነሳባቸው ሰው እየተዳረባቸው ፍታት እየተፈታባቸው አስፈላጊው መንፍሳዊ ነገር ሁሉ ሚስጥራተ ቤተክርስቲያን እየተፈጸመባቸው እየታወቀ ገለልተኛ ብሎ መጥራት ምን ማለት ነው? ሊታረም የሚገባው ነው……..ወግድ ብሎ ማራቁ ክርስቲያናዊ ተግባር አይደለም ። በቅዳሴ ላይ የፓትርያርክ ስም አለመጠራቱ ችግር አይደለም አልልም ችግር ነው። ነገር ግን በዚህ ምክንያት ሊለያየን አይገባም ብዬ አምናለሁ] እኚህ አባት ይህንን ያሉት ጁን 12,2012 ላይ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ ነው።

በተጨማሪም በፋይናነስ በአካውንት ውስጥ ሚሊየን ዶላር አለ የሚባል ነገር ሲመጣማ በጣም ትኩረት ተሰጠው ስለዚህ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድበት ከመንግስት ትእዛዝ ተላለፈበት ።

መንግስትም ይሰሩልኛል ብሎ ባስቀመጣቸው አባት መሪነትና በተላላኪዎቻቸው አንድ ተብሎ ተጀመረ ይህንንም የማፍርስ ስራም እንዲሰሩ ሰዎች ተመለመሉ።

የተመለመሉት እነማን ናቸው?
ብጹዕ አቡነ ዘካርያስ የኒወርክና አካባቢው ሀገረስብከት ጳጳስ፦ የጎጃም ሃገረስበከት ጳጳስ የነበሩና የፓትርያርክ የበላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ሆኖ ሳለ ነገርግን አቡነ ጳውሎስ ከቅዱስ ሲኖዶስ በላይ በመሆን ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝና ፍቃድ በአቡነ ጳውሎስ ትእዛዝ ለኒዎርክና አካባቢው ሃገረ ሰብከት የተዘዋወሩና በፍትሃነገስት ላይ ኤጲስቆጶሳት አንቀጽ 5 ቁጥር 158 ኒቅያ 77<<ኤጲስቆጶስ በአገሩ መስፋትና መጥበብ በህዝቡ ማነስና መብዛት ምክንያት ኤጲስቆጶስነት ከተሾመበት አገር ወጥቶ ወደ ሌላ አገር አይሂድ ስለዚህም ከእርሷ የሚሻለውን ሊፈልግ አይገባውም ይህ ለእርሱ አይገባውምና።ለሰው ሁሉ ድርሻው ከእግዚአብሄር ተሰጥቶታል እንጂ ይህ ከህዝባውያን ወገን ሚስት ያገቡ ሰዎችን ይመስላል ያለዝሙት ምክንያት ሰው ከሚስቱ ቢሰነካከል ከእርሷ በምትበልጥ ሊለውጣት ቢፈልግ እርሱ በጣም በደለኛ ነው።ከአገራቸው የተሻለ አገርን የሚፈልጉ ኤጲስቆጶሳትም ካህናትም እንደዚሁ ናቸው ስለዚህም አውግዘን ለየናቸው ።ይህ ልማድ መጥፎ ነውና ።>>የሚለውን በመተላለፍ የተሾሙበትን ሃገረ ስብከት ትተው የመጡ ፤ ኤጲስቆጶሳት አንቀጽ 5 ቁጥር 167 ድስቅ 30<<ከነውር ወገን አንዲቱ ነውር በኤጲስቆጶስ ላይ ብትታወቅ ከመዓርጉ የሚዋረድበትን ከሹመቱ የሚሻርበትን ምክንያት ይናገራል።>>ይህንን በመተላለፍ እምነት ያጎደሉ እንዲሁም በኤጲስቆጶስ አንቀጽ 5 ቁጥር 172<<አንድ ሊቀጳጳስ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ አልመጣም አይበል የታወቀ ምክንያት ካላገኘው በቀር ወደኋላ አይበል የቀረበትንም ምክንያት ይጻፍ ፈቃድም ይቀበል>> የሚለውን በመተላለፍ እዚህ ሀገር ከገቡ ጀምሮ ከ10 ግዜ በላይ አንድም ስብሰባ ያልተካፈሉ እንዲሁም እንደ ቤተክርስትያን ቀኖና ህግና ስርአት ቅዱስ ሲኖዶሱ የማያውቃቸውና ጵጵስናቸው የተሻረ አባት ናቸው።እንዲሁም በፓትርያርክ ቀብርም ሆነ ሹመት ላይ ያልተገኙ አባት ናቸው።ለዚህ ስራ ሲመረጡ ስልጣናቸውን ተገን በማድረግና በመጠቀም በማውገዝና በማስፈራራት ከቀኖና ውጭ በሆነ መንገድ እንዲያስፈጽሙ ማድረግ ነው።
በእዚህ በሚንሶታ እስቴት ውስጥ የሚገኙ በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ስር ነን የሚሉ ነገር ግን ያይደሉ ከመንግስት ጋር በቅርበት የሚሰሩ ካህናትና ግለሰቦች ናቸው።
በዛው በደብረሰላም መድሃንያለም ለብዙ ግዜ አገልጋይ የነበሩ እንዲሁም ተገልጋይ የነበሩ ካህናትና ዲያቆናት ቤተክርስትያኒቱ የነበረባቸውን ስጋዊ ችግር በገንዘብም ሆነ በተለያየ ነገር የቀረፈችላቸው በችግራቸው ግዜ የቀረቧት ዛሬ ደግሞ ሲሞላላቸውና ጊዜ ፊቷን ዞር ስታደርግላቸው የተነሱባት የእናት ጡት ነካሾችና እንዲሁም ለዚህ ስራ የተመረጡ ጥቂት የቤተክርስትያን ተቆርቁዋሪ መስለው ቤተክርስትያን የማፍረስን ስራ የሚሰሩ ግለሰቦችና እግዚአብሄርን የማያውቁ ነገር ግን የእግዚአብሄር አገልጋዮች የነበሩ የሰንበት ት/ቤት አገልጋዮች ናቸው።

እነዚህ ከላይያየናቸው አማሳኞች ለስራቸው መጀመሪያ የተቀበሉዋቸው ሁለት መመሪያዎች
አንደኛው በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ ቤተክርስትያኒቱን ከነሙሉ ንብረቷ በመንግስት ቁጥጥር ስር ማዋል ይሄኛው በጣም አዋጭ ሲሆን ብዙ ጊዜ ፤ገንዘብና ጉልበት ቆጣቢ እንዲሁም በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ያችን ትልቅ የኢ/ ኦ/ተ/ቤተክርስትያንን ዶግማዋንና ቀኖናዋን እንዲሁም ስርዓተ ቤተክርስትያን ጠብቃ የምትሄደውን ለሁለት ከፍሎ ከተቻለ ማጥፋት ካልሆነም ማዳከም የሚል ነው ይህ ደግሞ ግዜ ይወስዳል። እንግዲህ እነዚህ አማሳኞች በመመሪያቸው መሰረት ኔትወርካቸውን ዘርግተው ከኢትዮጵያ ድረስ መመሪያ ሲያስፈልግ በይፋ በቡራኬ መልክ አይዟችሁ በርቱ ከጎናችሁ ነን በማለት እንደየ አስፈላጊነቱ ደግሞ ከሃገረስብከቱና ከቅዱስ ፓትርያርኩ በሚመጡ ፍጹም መንፈሳዊነት በሌላቸው ቤተክርስትያንን የሚከፍሉና የሚበትኑ መልእክቶችን በመጻጻፍ የክርስቲያኑንና የቤተክርስትያኑን ክብር ያላገናዘበና የኢትዮጵያን ኦ/ተ/ቤ አማኙን አንገት ያስደፋ እንዲሁም የሚያሸማቅቅ ደብዳቤዎችን በመላላክና ግልጽ በሆነና በድብቅ የስልክ ግንኙነቶች በማድረግ ቤተክርስቲያኒቱ ላይ ጥቃታቸውን ቀጠሉ።



የአጀንዳቸው መሠረት ስርአተ ቤተክርስቲያን ፈርሷል

እንግዲህ እነዚህ ለማፍረስ በተመለመሉ ኅይሎች አማካኝነት ከ20 ዓመት በላይ ቤተክርስትያኒቱ ሰላሙዋንና አንድነቷን ጠብቃ የኖረችበትን አቋሟን ወደጎን በመተው የቤተክርስትያን አገልግሎት ቅዳሴ ብቻ በማስመሰል ስርአተ ቤተክርስትያን ተጥሷል በማለት በቅዳሴ ግዜ የፓትርያርክ ስም አልተጠራም መጠራት አለበት በሚል በሰፊው ማራገብ ጀመሩ ።ጥያቄአቸውንም አቀረቡ ጥያቄአቸውም አግባብ፤ተገቢና መብታቸውም ስለሆነ መልስ መሰጠት አለበት በሚል በቤተክርስትያኒቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ተደረገ በአብዛኛው አባላት ከጠቅላላ አባላቱ ከ50+1 በላይ የሆነው አባል አንድነቷ ተጠብቆ በአለችበት አቋሟ እንድትቀጥል የሚል ውሳኔ ተሰጠ። እነርሱ ግን አላማቸው ሌላ ነበርና ተስማምተው ድምጽ የሰጡበትን በማጠፍ ጠቅላላ ጉባኤ አልተሟላም አሉ እሺ ካልተስማማች እንደገና ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራ ሲባሉ በፍጹም እኛ በመረጥነው መንገድ ብቻ ነው መሆን ያለበት አሉ።

እነዚህ አማሳኞች በመጀመሪያ ደረጃ ያስቀመጡት አልሳካ ሲላቸው ሁለተኛ አማራጫቸውን በመጠምዘዝ በሁከትና በረብሻ ቤተክርስትያኒቱን ማወክ ተያያዙት ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራና አባላቱ ይወስንበት ሲባሉ በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ እንደማይሆንላቸው ስላወቁት በፍጹም ጠቅላላ ጉባኤ ሳይጠራ እኛ የፈለግነውን ነገር ብቻ ካልተደረገ አሉ ። ይህን ግዜ ነበር ህግ ያለበት ሀገር ስለሆነ በህግ እንዲዳኝ ወደ ፍርድ ቤት ጉዳዩ ያመራው ። ጉዳዩም በፍርድ ቤት እያለ በዘረጉት ኔትዎርክ በመታገዝ እንዲያስታርቁ ሳይሆን ከተቻለ አስፈራርተውም ሆነ አውግዘው ወደ እራሳቸው አላማ ማለትም መንግስት ወደ ሚቆጣጠራት ቤተክርስትያን የማስገባት ስራ እንዲሰሩላቸው ካልሆነም የተፈለገውን የመክፈል ሰራ እንዲሰሩላቸው ሁለት ጳጳሳትን አመጡ
አቡነ ማርቆስን ከኢትዮጵያ
አቡነ ዘካርያስን ከአሜሪካን

በማስመጣት በአዳራሽ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ያውም በአርምሞ ሱባኤ በሚያዝበት በታላቁ አብይ ጾም ህዝብን ከሚመራ ጳጳስ የማይጠበቅ የስድብ አፍ በቤተክርስትያኒቱ፤በንዋያተ ቅዱሳቱ፤አላማቸውን በማይደግፉት ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም ምእመናን ላይ ሲሳደቡ፤ሲሳለቁና ሲስቁ ውለው እና አድረው እንዲሁም በማግስቱ የመጋቢት መድኃኒዓለም በዓለ ንግስ ላይ በአቡነ ማትያስ እየተመሩ የመጡት ልዑካን ከነግብራበሮቻቸው በጣም ከአቅም በላይ የሆነ ትእግስት እና እልህ አስጨራሽ ትእይንት በቤተክርስትያኑ ዓውደ ምህርት ላይ በማሳየታቸው ምእመኑ ከአቅሙ በላይ ስለሆነበት አግባብ ያልሆነ ስድብ በጳጳሳቶቹ ላይ እንዲሳደብ አድርገውታል የእነርሱም አላማ በአውደምህረቱ ላይ ያልተገባ ትእይንት በማድረግ ምእመኑን ንዴት ውስጥ በመክተት ያልሆነ ቃል እንዲናገር ማድረገ ነበረና እነዚህ አፍራሽ ሃይሎች ይህችን አጋጣሚ በመጠቀም ጳጳሳቶች ተሰደቡ እያሉ ምእመኑ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር ሞክረዋል ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ማንነታቸው ተጋለጠ። እዚህ ጋር አንድ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር አለ ጳጳስ ይሰደባል ግን አይሳደብም ፣ይመታል ግን አይማታም፣ይገደላል ግን አይገድልም፣ያስታርቃል ግን አያጣላም፣ ምእመንን ይሰበስባል ግን አይበትንም ፣ፍቅርን ይዘራል ግን ጥላቻን አያበቅልም እንዲሁም አንድ ጳጳስ ገና ሲመነኩስ እንደሞተ (የሞተ)ስለሆነ በቁሙ ተስካሩን ያወጣል የጵጵስናውን አስኬማ ሲደፋ ደግሞ ለሃይማኖቱ፣ለህዝቡ፣ለተበደለ፣ለተገፋ፣ፍትህ ላጣ ፣ለተጨቆነ ፣ለቤተክርስትያን ለመሳሰሉት ሊሰደብ፣ሊገረፍ፣ሊታረዝ፣ሊታሰር፣ ብሎም ሞትም ከአስፈለገ ሊሞት ነው እንጂ ሹመቱ እንደ አለማዊ ሹመት አይደለም። እነዚህ ጳጳሳት ግን እንደነርሱ ፍላጎት ከፍለውት ነው የሄዱት ሆኖም ግን በመድኃኒዓለም ቸርነት ምእመኑ ለቤተክርስትያኑ ጠንክሮ እንዲቆም ነው ያደረጉት ቆሞም ተገኘ ።ከዛም ጳጳሳቶቹ ለአፍራሽ ካህኖቻቸው መመሪያ ሰጥተው የአቡነ ማትያስን ስም ሳትጠሩ ከእንግዲህ እንዳትቀድሱ ብለዋቸው ለሰሩት ሁከትና ብጥብጥ ተመራርቀው እና ተመሰጋግነው ጳጳሳቶቹም ወደ መጡበት ተመለሱ።

እለተ ሆሳዕና፦

እነዚህ አማሳኞች የሆሳዕና በዓል ከመደረሱ ከቀናት በፊት አንድ ቤተክርስትያኒቱን በእጃቸው የሚያስገቡበት የመሰላቸውን ተንኮል(ዘዴ) ቀይሰው ያች ቀን እስክትደርስ መጠባበቅ ጀመሩ። ድንጋዮች ያመሰገኑበት ሻጮችና ለዋጮች በጅራፍ እየተገረፉ ከቤተመቅደስ የወጡበት ክርስቶስ ቤቱን ያጸዳበት ቀን እለተ ሆሳህና በታላቋ የምስጋና ቀን ሆሳህና በ2006 በሚንሶታ በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢ/ኦ/ተ/ ቤተክርስትያን አሳዛኝ ነገር ተከሰተ።

የሚገርመው ደግሞ እርስ በእርሳቸው ስለማይተማመኑ እንዳይካካዱ ተፈራርመው በሌሊት ወደ ተከበረችው የእግዚአብሄር ቅዱስ ስጋው እና ክቡር ደሙ ወደ ሚፈተትበት ቅድስት መቅደስ ገቡ። ህዝበ ክርስትያኑ ለአገልግሎት መጡ ነው ያለው እነርሱ ግን ለአሰቡት አላማ ነው የመጡት እቅዳቸውም ከቅዳሴ በፊት የሚከናወኑ ስርአቶች ከተከናወኑ በሁዋላ በቅዳሴ ጊዜ የአቡነ ማትያስ ስም ከተጠራ እንቀድሳለን ካልተጠራ አንቀድስም ብለው አቋማቸውን በፊርማቸው በይፋ አሳወቁ በዚህን ግዜ በሆሳዕና እለት ድንጋዮች በአመሰገኑበት ዕለት እኛ ካልቀደስን እንዲሁም የሰንበት ተማሪዎች ካልዘመሩ ቤተክርስትያኑ ይዘጋል ሳይወዱ በግዳቸው የእኛን ፍላጎት ያሟላሉ ብለው የእግዚአብሄር ቤት መሆኑን እረስተው የትዕቢት ስራን ሰሩ። በዚህን ጊዜ ነበር መድኃኒዓለም ጅራፉን ያነሳው መድኃኒዓለም ከተነሳ ያውም በሆሳዕና ዕለት እስከ መጨረሻው ካላጸዳ አይመለስም እናም የማጽዳቱን ስራም ጀመረ።

እነሆ ከወደ ቤተመቅደስ አንድ ድምጽ ተሰማ “ እባካችሁ በዚህ በታላቅ ቀን በሆሳዕና ድንጋዮች ባመሰገኑበት ቀን የጳጳስ ስም ካልተጠራ ብለን የእግዚአብሔርን ስም አንጠራም አይባልም እውነት ከእግዚአብሔር ምስጋና የሰው ምስጋና ይበልጣልን ? በረከት ያስወስድብናል በጅራፍም ያስገርፈናል ከቤቱም ያስባርረነናል አሁን ምእመኑን ከምንበትን ቤተክርስትያኑንም ከምንዘጋ እስከዛሬ ድረስ ለብዙ ዘመን የጳጳስ ስም ሳንጠራ የቀደስንበትን ቤተክርስትያን አንቀድስም ከምንል እንቀድስና ጥፋትም ሆኖ ቢገኝ እንኳን ይቅርታ እንጠይቅበት’’ የሚል ቃል መጣ እነርሱ ግን ከበላይ ነው የታዘዝነው ብንቀድስ ክህነታችን ይያዛል መቀደስ አንችልም ብለው አቋማቸውን ገለጹ በዚህን ግዜ ነበር መድኃኒዓለም ያዘጋጃቸው ካህናትና ዲያቆናት ቅዳሴ መቀደስ ሲጀምሩ የአማሳኞቹ ካህናትና ዲያቆናት ተከታይ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እንዲሁም ጥቂት የእነርሱ አጀንዳ የእውነት የቤተክርስትያን አንድነት የመሰላቸው ወደ 50 የሚጠጉ ንጹሃን የቤተክርስትያን ምእመን አንድ በአንድ በየተራ ቤተመቅደሱን ለቀው ወደ ፓርክ በማመራት የሆሳእና እለት እግዚአብሔር መድኃኒዓለም በእየሩሳሌም ለቤቱ አልታዘዝ ያሉትን ጠራርጎ እንዳስወጣ ሁሉ በዳግማዊቷ እየሩሳሌም በሚንሶታ ደብረ ሰላም መድኃኒዓለም የኢ/ኦ/ተ/ቤ ተደገመ። እግዚአብሔር በቤተመቅደሱ ተመሰገነ ከበረ ተወደሰ አቡነ ማትያስ በፓርክ ተመሰገኑ ከበሩ ተወደሱ ።

ከሁሉም በጣም ለየትና ግርም የሚለው ደግሞ እሁድ እሁድ ሁልጊዜ ከቅዳሴ በሁዋላ የዕለቱ ያሬዳዊ ዜማ (ወረብ) ይወረባል (ይዘመራል) ያን ግዜ ግን ሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች በሙሉ ወጥተው ፓርክ ሄደው ስለነበር ማን ሊዘምር ነው ሲባል ለካ እግዚአበሔር እኛ ስናምጽ ለራሱ የሆነ ሰው ለቤቱ ያዘጋጃል፤ ከምእመን እርሱ መረጠ አንድ አንድ እያሉ አውደ ምህረቱን ሞሉት እግዚአብሔር እንዲያመሰግኑት ከመረጣቸው መካከል አንዲት ልትወልድ የደረሰች እህት የመድኃኒዓለምን ድምጽ በሰማች ግዜ ከተቀመጠችበት ብድግ ብላ ልታገለግል ልትዘምርለት መጣች የአምላካችን ስራው ድንቅ ነው ።አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ትዝ አለኝ በሉቃስ ወንጌል ላይ ምዕ 1 ቁጥ 41 እንዲህ የሚል ቃል አለ “ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ግዜ ጽነሱ በማህጸኗ ውስጥ ዘለለ በኤልሳቤጥም መንፈስቅዱሰ ሞላባት ………… ኤልሳቤጥም እነሆ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ግዜ ጽንሱ በመሃጸኔ በደስታ ዘሏልና’’ ብላ እንዳመሰገነች አንዲት ልትወልድ የደረሰች ነብሰጡር የመድኃንያለምን ድምጽ በሰማች ግዜ ከተቀመጠችበት በድግ ብላ መቁዋሚያውንና ጽናጽሉን አነሳች በዚህን ግዜ በማህጸኗ የነበረው ጽንስ ዘለለ ፤ሰገደ፤አመሰገነ እግዚአብሄር በሆሳዕና እለት በድንጋዮችና በህጻናት ተመሰገነ ማለት ይህ አይደል።

እንግዲህ ምእመናን እሺ ብንል ለእግዚአብሔር ብንታዘዝ የምንከብረው የምንባረከው እኛው ነን እምቢ ብንል ደግሞ የምንጎዳው እኛው ነን እግዚአብሔር እንደው ምንም የሚጎልበት አንዳች ነገር የለውም ቢፈልግ በመሃጸን ያሉትን ያስነሳል ቢፈልግ ህጻናትን ያስነሳል ቢፈልግ ድንጋዮችን ያስነሳል ይህንንም ደግሞ በሚንሶታ ደብረሰላም መድኃኒዓለም ቤተክርስትያን አይተነዋል ።

የአውጋዡንና የተከታዮቹን ማንነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ውግዘት አውጋዡም ሆነ ተከታዮቹ በእውነት የኢ/ኦ/ተ ቤተክርስትያን አማኞች ናቸውን?

እዚህ ጋር ተከታዮቹ ብዬ የገለጽኩት ይህንን ተግባር ተቀብለው የሚያስፈጽሙትን እንጂ ምዕመኑን አይወክልም ምክንያቱም ምዕመኑ በንጹህ ልቡ የእውነት አንድነት መስሎት ስለሚከተል በበመጀመሪያ በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤተክርስትያን ቀኖና መሰረት ስልጣኑ የተሻረ አባት ሊያወግዝም ሆነ ሊለይ አይችልም የተወገዘ እንዴት ያወግዛል ሲቀጥል በሰሞነ ሕማማት ማለትም ከሆሳእና እስከ ትንሳኤ ባሉት ቀናት ውስጥ እንኳን ማውገዝ ፤ማሰርና መለየት ቀርቶ መፍታት እንኳን በማይቻልበት ቀን አቡነ ዘካርያስ የደብረሰላም መድኃንያለም የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስትያን ካህናት ፤ዲያቆናት እንዲሁም ምእመንን በፍትሐነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 600 <<በሰሞነ ሕማማት ክርስትና ማንሳት፤ ክህነት መስጠት፤ለሞቱ ሰዎች መጸለይ አይገባም በእነዚህም ቀኖች ውስጥ ፈጽሞ ማገልገል ይገባል እንጂ በሰሞነ ሕማማት ስለሚሞቱት ሰዎች የሙታን ግንዘትና የሃዋርያት ስራ ወንጌላት የሙታን ፍታት በሆሳዕና በዓል ይነበብ እንጂ በጸሎተ ሐሙስ ጸሎተ ተአምኆ እግዚአ ሕያዋን የቡራኬ ጸሎት አይባልም(አይጸለይም)ቅዳሜ ግን እግዚአ ሕያዋን ይባላል ፍትሃት ይፈታል ከመሳለም በቀር ጸሎተ እጣንም ይጸለያል በእለተ እሁድ ግንዘት ማድረግ በፋሲካ ቀንም ማልቀስ አይገባም >> የሚለውን በመተላለፍ በሰሞነ ሕማማት ቀኖናውን ጥሰው አናገለግልም ብለው የወጡትን ምንም ሳይሉ ቀኖናውን ጠብቀው ምንም ሳያጉዋድሉ ያገለገሉትን በሙሉ በጸሎተ ኅሙስ ካህናቱና ዲያቆናቱ ቅዳሴ ቀድሰው ሲወጡ እነዚህ አማሳኞች ከአቡነ ዘካርያስ የመጣ የውግዘት ደብዳቤ ነው ተቀበሉ ብለው ፎቶና ቪዲዮ ደግነው ደብዳቤውን ለመስጠት ሞከሩ የተቀበለውም ተቀበለ ያልተቀበለም አልቀበልም ብሎ ወደ ቤቱ ሄደ።የተላለፈውንም ውግዘት እንደሚከተለው እናያለን፦
ቤተክርስትያኒቱ ፦ከተመሰረተች ከ20 ዓመት በላይ የሆናት በጳጳሳት ተባርካ ብዙ ክርስትያን የተጠመቀባት ፤የቆረበባት ፣የተዳረባት ፣ሰው ሲሞት ፍትሃት የተደረገባት፣ብዙ መንፈሳዊና ሚስጥራዊ ግልጋሎት የተሰጠባት ቤተክርስትያን እግዚአብሔር አምላክ የምእመኑን ጸሎት የተቀበለባትና የፈጸመባት ቤተክርስትያንን ከዛሬ ጀምሮ አሮጌ ህንጻና የአሳማ(የከብቶች) ማርቢያ ትሁን ብለው በህንጻ ቤተክርስትያኒቱ ላይ እንዲሁም በንዋያተ ቅድሳቱ ላይ የውግዘት ቃል ተላለፈ።
ካህናቱና ዲያቆናቱ ፦ከሆሳዕና ቀን ጀምሮ በደብረ ሰላም ቤተክርስትያን ብቻ የአቡነ ማትያሰን ስም ሳይጠሩ የቀደሱ ካህናትና ዲያቆናት ተወገዙ ልብ በሉ በሌላ ቤተክርስትያን ስም ሳይጠሩ መቀደስ ግን አያስወግዝም ቤተክርስትያን ሁሉንም በእኩል የሚዳኝ አንድ አይነት ህግ ያላት እንጂ አንዱን የሚኮንን አንዱን የሚያጸድቅ ህግ የላትም አለመጥራት የሚያስወግዝ ቢሆን እንኳን አይደለም እንጂ በዓለም ላይ ያሉት ገለልተኞች በሙሉ በተወገዙ ነበር ። ነገር ግን አላማው ጠንካራና ስርአተ ቤተክርስትያንን የጠበቁ ቤተክርስትያንን እየተከታተሉ የማጥፋት ዘመቻ ስለሆነ በደብረሰላም ብቻ ያሉት ተወገዙ ።
ምእመኑ(ህዝበ ክርስትያኑ)፦በዚህች ቤተክርስትያን ውስጥ ቅዳሴ ያስቀደሰ ፣የቆረበ ፣ክርስትና ያስነሳ፣የተዳረ፣ቤተክርስትያን ውስጥ አገልግሎት የሰጠውን ካህን መስቀል የተሳለመ እንዲሁም ማንኛውንም አገልግሎት የተገለገለ በሙሉ ተወገዘ ።

እንግዲህ በኢ/ኦ/ተ/ቤ ስርዓትና ደንብ ውግዘት እንዲሁ በቀላሉ የሚመጣ ነገር አይደለም በጣም ከባድ ነገር ነው እንደው በአሁን ግዜ ግን በጣም ያሳዝናል ። እንደ አንድ ኢ/ኦ/ተ/ቤ ምእመን ሆኜ ስመለከተው አንገቴን እንድደፋ አድርጎኛል። ስለውግዘት በፍትሃነገስት ላይ አንድ ካህን ስለ ሁለት ነገር ይወገዛል እርሱም ቢሆን ተመክሮ አልመለስ ሲል ነው።
በነውር ምክንያት 2. በምንፍቅና (በሃይማኖት ክህደት) ናቸው

እዚህ ግን የሆነው የሊቀጳጳሱን ፍላጎት ስላላሟሉ ለምን ቀደሳችሁ ተብለው ነው የተወገዙት መወገዝ ከነበረባቸውም አንቀድስም ብለው የሄዱት ነበር መወገዝ የነበረባቸው እንዲሁም በፍትሃነገስት ላይ ኤጲስቆጶስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 184 ረስጠብ 24<< አንድ ሊቀጳጳስ በቂም በበቀል ቢያወግዝ ከሹመቱ ይሻር በተጓዳኝ የተወገዘው ካህንም ይቋቋመው ነው የሚለው >>።ደግሞ ካህናቱ አጥፍተው ተወገዙ ቢባል እንኩዋን ቤተክርስትያኒቱንና መዕመኑ በምን ጥፋታቸው ነው የሚወገዙት ቤተ ክርስትያን በሄደ ፣ በቆረበ ፣ በአመሰገነ መቼም ይህንን ለቤተክርስትያኒቱ ትልቅ ውርደት ስለሆነ አንድ ሊባል ይገባዋል።



ስቅለት(ዕለተ አርብ)

እነዚህ አማሳኞች ቤተክርስትያኒቱ ተወግዛለች አንሄድም እንዳትሄዱ ብለው ለምእመኑ ቤት ለቤት በመሄድና በስልክ እየደወሉ ይናገሩ ጀመር እዚህ ጋር ልብ ልንለው የሚገባው ነገር በእለተ ሃሙስ ከቅዳሴ በሁዋላ ለካህናቱና ለዲያቆናቱ በደበዳቤ ነው ውግዘቱ የደረሳቸው ታድያ ምነው በዕለተ ዓርብ መጥተው አገለገሉ ። ዕለተ ዓርብ ውግዘቱ ተነስቶ ነበር ወይስ ለእነርሱ የማፍረስ ስራ ሲሆን እንዳይሰራ ቤተክርስትያንን የሚያንጽ ሲሆን ውግዘቱን እንዲሰራ ተደረጎ ነው የተወገዘው ነገሩ እንዲህ ነው ጸሎተ ሃሙስ ዕለት ወደ 300 የሚሆኑ የቤተክርስትያኒቱ አባላቶች እነዚህ አፍራሽ ካህናትና ዲያቆናት በራሳቸው ግዜ በዕለተ ሆሳዕና ስራቸውን እረግጠው ስለወጡ ከዛሬ ጀምሮ የቤተክርስትያናችን አገልጋዮች አይደሉም የሚል በፊረማ የተደገፈ ወረቀት ለዳኛው ስለተሰጠው የአሜሪካን ህግ ደግሞ ተፈጻሚ እንደሚሆን ስለሚያውቁት ሌላ ነገር መፈለግ ነበረባቸው እርሱም፦
ሌላ ቤተክርስትያን
ለቤተክርስትያኑ መገለገያ የሚሆን ነዋያተ ቅድሳት

ስለዚህ አዳራሽ ተከራይተው የትንሳኤን በዓል በአዳራሽ ብለው አወጁ በቤተክርስትያኒቱም ምንም አይነት አገልግሎት አይሰጥም ብለው ምእመኑን ለማወናበድ ሞከሩ እንዲሁም ለእኛ ወፈ ግዝት ለእነርሱ ደግሞ ግዝት የሆነውን ተላልፈው ቤተክርስትያን መጥተው ንዋያተ ቅድሳቱን ዘርፈው ከእንደገና ውግዘቱን አውጀው ላይመለሱ ወጥተው ሄዱ።ከዚህም ቀን ጀምሮ በድምጽም በሁከትም እንደማይሆንላቸው እንዲሁም በመድኃኒዓለም ቸርነትና በምእመኑ ያላሰለሰ ጥረትና ብርታት እንዳልተሳካላቸው ስላወቁት ቤተክርስትያን ለመክፈት አንድ ብለው ጀመሩ።

ሜይ 11 ወሳኙና አሳዛኙ ቀን

ለቤተክርስትያኒቱ በጣም አሳዛኝ ነበር ፤ የፍርድ ቤቱ ዳኛ በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ድምጽ ተሰጥቶ የቤተክርስትያኒቱ አቋም የተገለጸበት ቀን ነበር። እዚህ ጋ ሳልጠቅሰው የማላልፈው ነገር ትላንት አባቶች ጳጳሳት ተሰደቡ ብለው ሲናገሩ የነበሩ በዚህ ቀን ከ8 አመት በላይ የማይጠገበውን የቤተ ክርስቲያንን ያሬዳዊ ዜማ ያስተማሯቸውን፣ንስቸውን የተቀበሏቸውን ፣ በእጃቸው የተባረኩት እና የቆረቡትን አባት በአደባባይ መሳደብ የማይረሳና አሳዛኝ ትእይንት ነበር። ይህች ቀን ለአማሳኞቹ የደስታ ቀን ነበር ምክንያቱም ከሆነላቸው ቤተክርስትያኒቱን ከነ ሙሉ ንብረቷ መረከብ ካልሆነላቸው ደግሞ ለሁለት መክፈል ሁለቱም ውጤት ለእነርሱ የአሸናፊነት ነው ። ለቤተክርስትያኒቱ ምዕመን ግን የሃዘን ቀን ነበር ምክንያቱም ሁለቱም ውጤት የሃዘን ነበር ውጤቱ አፍራሾች ቢወስዱት በመንግስት ቁጥጥር ስር አውለው ቤተክርስትያኒቱን ባለቤት አልባ አድርገው የመንግስት ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሊያደርጉአት ስለሆነ ውጤቱ በ ተቃራኒውም ቢሆን ከእህት ከወንድሞቻቸው በመለየታቸው ምክንያት የሃዘን ቀን ነበር ያም ሆነ ይህ ውጤቱ የመድኃንያለምና የምዕመኑ ሆነ ቤተክርትያኒቱ በነበረችበት አቋሟ እንድትቀጥል ሆነ ።ቤተክርስቲያኔ ብለው ደፋ ቀና እንዳላሉባት በአፋቸው ሞልተው ለመጥራት እንኳን የሚሳሱላትን ቤተክርስቲያንን ከዚህች ቀን ጀምሮ እንደ ቤተክርስትያን ሳይሆን 4401 ሕንጻ እያሉ የእግዚአብሔርን ቤት ማዋረዳቸውን ቀጠሉ።



ደብረሰላም መድኃኒዓለም ቤተክርስትያን ለሁለት ተከፈለች ፦ አብዛኛው ምእመን ደብረሰላም መድኃኒዓለም የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስትያንን ይዘው እንደበፊታቸው ሲቀጥሉ በሌላው ወገን ያሉት ደግሞ ጽርሃርያም ቅድስት ስላሴ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስትያን ብለው ሌላ ቤተክርስትያን መክፈታቸውን በይፋ አወጁ ሁለቱም በየአሉበት አገልግሎታቸውን ማከናወን ጀመሩ።

ከተከፈሉ በሁዋላ ደብረሰላምን የማዳከሙ ሂደት

ደብረሰላም መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ከተከፈለችበት ጊዜ ጀምሮ የመድኃኒዓለም ጥበቃ ያልተለያት ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ እግዚአብሔር ለራሴ የሚለውን እራሱ በፍቃዱ እያመጣ አገልግሎቱ ከዱሮ በበለጠ እየሰፋ በመሄዱ መንግስት በፖለቲካው ይጠቀምበት የነበረውን አሰራር ማለትም ለመንግስቴ ያሰጉኛል የሚላቸውን ጠንካራ ተቃዋሚዎችን የሚያዳክምበትን አሰራር በቤተክርስትያን ውስጥ በእነዚህ አፍራሽ ሃይሎች አማካኝነት እየተጠቀመበት እንዳለ እናያለን። እስቲ የሚንሶታ ደብረሰላም መድኃኒዓለምን ለሁለት ከተከፈለ በኋላ ለማዳከም የተጠቀሙበትንና እየተጠቀሙበት ያለውን ነገር በዝርዝር እንመልከት
የሚንሶታው ደብረሰላም መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ቤተክርስትያኒቱ ከተመሰረተች ጀምሮ ላለፉት 19 ዓመት የነበረውና ያለው የሰንበት ትምህርት ቤት መጠሪያ ስም ቤዛ ኩሉ ሰንበት ት/ቤት ነው። አሁን ደግሞ ጽርአርያም ቅድስት ስላሴ ስደተኛው ቤዛ ኩሉ ሰንበት ት/ቤት በማለት ሰይመውታል በጣም የሚገርመው ጽርአርያም ስላሴ ከተመሰረተ ገና አንደኛ አመቱ ሆኖ ሳለ እነርሱ ግን ጽርአርያም ስላሴ ስደተኛው ቤዛ ኩሉ ሰንበት ት/ቤት አስራ ዘጠነኛ አመት ብለው ለሰሚው ግራ የሆነ ዓመታዊ በዓል አክብረዋል እዚህ ጋር ስሙ ላይ ችግር የለበኝም እውነት ለሃይማኖት ከሆነ ቤዛ ኩሉ ሰንበት ት/ቤት አንደኛ አመት ነበር መባል የነበረበት። ለዚህ ደግሞ የሚሰጡት ምክንያት አብላጫዎቹ ዘማሪዎች ከቤተክርስትያን ስለወጣን ነው ይላሉ ልብ በሉ አብላጫዎቹ ምእመናን አይደለም ያሉት ምእመንም ቢባል እንኳን ስህተት ነው ሰንበት ት/ቤት ከመቼ ወዲህ ነው የግለሰቦች ሆና የምታውቀው ቤተክርስትያን ከ2000 ዘመን በላይ በኖረችበት በታሪኳ የዚህ አይነት ውርደት የቤተክርስትያን ልጆች ነን በሚሉት ልጆቿ ሰንበት ት/ቤት የኛ የተወሰንን ሰዎች ነው የሚል የተነሳባት የመጀመሪያዎቹ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም ። የሰንበት ት/ቤቱ ባለቤቶች ነን የሚሉት ደግሞ ሰንበት ት/ቤቱ በደብረሰላም መድኃንያለም ቤተክርስትያን ሲመሰረት እንኩዋን ያልንበሩ ናቸው።ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም ይባል የለ አባቶች ካላችሁ ስደተኛ ሰንበት ት/ቤት በሚንሶታ የተጀመረው በሌላውም እንዳይስፋፋ አንድ ልትሉ ይገባል ጅብ በቀደደው እንዳይሆን ስል የእኔን ሃሳብ እናገራለሁ።የሲኖዶስ መቀመጫ ኢትዮጵያ እንደሆነ ሁሉ የሰንበት ት/ቤቶችም መቀመጫቸው የተመሰረቱበት ቤተክርስትያን ነው የቤዛ ኩሉ ሰንበት ት/ቤትም መቀመጫ በተመሰረተበት ደብረሰላም ቤተክርስትያን ነው እንጂ በሌላ ሊሆን አይችልም።ሰው ይመጣል ይሄዳል እንጂ ሰንበት ት/ቤት ሰው ተከትሎ አይሄድም እንዲሁም ታሪክ ታሪክ የሚባለው ጊዜን እና ቦታን ሲገልጽ እንጂ የሰውን የሙቀት መጠን እየተለካ አይደለም የሚመለከተው አካል ካለ ኅይማኖታዊ ማስተካከያ ሊሰጠው ይገባል።
ደብረሰላም ቤተክርስትያን ውስጥ ያሉት ታቦታት (ሀ)የመድኃኒዓለም (ለ)የኪዳነምህረት (ሓ)የሚካኤል (መ)የገብርኤል ሲሆኑ እነዚህ አማሳኞች የመድኃኒዓለምን ታቦት በማስመጣት ሁለቱ ቤተክርስትያኖች ተለያይተው እንዲቀሩ ምዕመን ከምዕመን እንዳይገናኝ የማድረግ ስራ ሰርተዋል ለቤተክርስትያኒቱና ለህዝበ ክርስትያኑ ቢያስቡ ኖሮ በአንድ ከተማ ውስጥ ያለን ታቦት ባላስመጡ ነበር ። የሌለውን ነበር ማምጣት የነበረባቸው እግዚአብሔርም በአንድነትና በፍቅር እንዲከብር በተደረገ ነበር ። እነዚህ ሰዎች ለስርዓት የሚጨነቁ በማስመሰል በሃይማኖት ሽፋን ነበር ቤተክርስቲያኗን ለሁለት የከፈሏት እነርሱ ግን ዶግማውን እስከማፍረስ ሲደርሱ ተው ያላቸውም የለም ምክንያቱም ደግሞ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስትያን አስተምሮ ስላሴ ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው መድኃኒዓለም ማለት ወልድ ነው። ሁለቱም አንድ ናቸው ብላ ነው የምታስተምረው እንደ ቤተክርስትያን አስተምህሮ በስላሴ ታቦት ላይ የመድኃኒዓለም ታቦት አይገባም ምክንያቱም ሁለቱም አንድ ናቸውና በስላሴ ላይ እመቤታችን ፤ጻድቃን፤ ቅዱሳንሰ ናቸው የሚገቡት እንጂ በየትኛውም አስተምሮ መድኃኒዓለም አይገባም እነዚህ አማሳኞች አላማቸው ስለስርአት ጥሰት ሳይሆን የመንግስትን አላማ ማስፈጸም ስለሆነ አስገብተውታል።አራት መለኮት ሊባል ይሆን እግዚአብሔር ይሰውረን አንድ ሊቀ ጳጳስ እንደተናገሩት “እንደዚህ አይነት ድርጊት አራት አምላክ አለ ብለን እንደ ማመን ነው የሚቆጠረው ይህ አይነት ድርጊት በቅዱስ ሲኖዶስ ላይ ቢቀርብ እና ቢታይ ጵጵስናን እስከ ማሻር እንደሚደርስ” ገልጸዋል ። በመቀጠልም ለምእመኑ ለገብርኤል ንግስ መድኃኒዓለም ሄደው እንዳያነግሱ ከዚህ በፊት ዞር ብለው አይተውት የማያውቁትን የኤርትራ ገብርኤል ቤተክርስትያን ሄዳችሁ አንግሱ ብለው ለህዝቡ አስታወቁ ሔደውም አንግሰው ጥሩ ቀን እንዳሳለፉ ገለጹ እውነት ንግሱን ፈልገው ቢሆን ችግር አልነበረውም ነገር ግን ደብረሰላም መድኃኒዓለምን ለማዳከም የተደረገ ነው። እንጂ የሚደረገው ስራ አሁንም አላቆመም የቤተክርስቲያኗ አባት ከኢትዮጵያ የሚካኤልንም ታቦት ይዘው መጥተዋል። የሚቀራቸው የገብረኤል እና የኪዳነምህረትን ታቦት ነው ወደፊት ምን እንደሚሆን እናያለን፤ ስለዚህ ምእመናን ሆይ ይህ አስተምሮ የኢ/ኦ/ተ/ቤ አስተምሮ እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባል ዝም ብለን ተከታዮች ከምነሆን ቆም ብለን ልናስብ ይገባናል በተለይ ደግሞ ጉዞ ወደ እናት ቤተ ክርስትያን(እንቀላቀል) የሚለው ስሙ እና ከእላዩ ሲታይ መልካም የሚመስለልና የሃይማኖት ሽፋን ያለው ውስጡ ግን ዶግማውን የሚንድ የዘመናችን የቤተክርስትያን ፈተና አስተምሮው የቤተክርስትያን ያልሆነ የመንግስትና የእነርሱን ተልኮ ለማስፈጸም የሚሮሯሯጡ ሰዎች ያስገቡብን ስለሆነ በእውነተኞቹ የቤተክርስትያን አባቶች እርምት ሊወሰድበት ይገባል። ምዕመናንም ማንም ተነስቶ ቤተክርስትያንን አንድ ላደርግ ነው ተከተሉኝ ቢል ልንከተለው አይገባም የበላይ አካል የሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጠውን መመሪያ ብቻ ነው መከተል ያለበን። የቤተክርስቲያንም ክብር ሊጠበቅ ይገባል።

3 ደብረሰላም መድኃኒዓለም ቤተክርስትያን ለምዕመኖቿ ወንጌልን ለማስፋፋት በምታደርገው መምህራንንና ዘማርያን ከተለያዩ ደብራት የምትጋብዛቸውን እየተከታተሉ ደብረሰላም መድኃኒዓለም ብትሄዱና ወንጌልን ብታስተምሩም ሆነ ብትዘምሩ ትወገዛላችሁ በማለት በማስፈራራት እንዲሁም አቡነ ዘካርያስ እዚያ ቤተክርስትያን አወግዝሃለሁ በሚል ማስፈራርያ ለመምጣት የአየር ትኬት ከተቆረጠላቸው በሁዋላ በዛቻው ምክንያት የሰረዙ መምህራን እንዳሉ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ ለዚህ ደግሞ ኤጲስቆጶስ አንቀጽ 5 ቁጥር 182 እንዲህ ይለናል <<ፈጽሞ ቂመኛ የሆነ ወይም በየጊዜው ሁሉን እስከማሰርና እስከ ማውገዝ ድረስ ፈጥኖ ለማውገዝ ቂሙን የማይረሳ ቢሆን ይሻር >> ይለናል እንዲሁም ምንም እንኳን ቤትክርስትያን የሰጠቻችሁ ሃላፊነት ቢሆንም ይህንን ሁሉ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ተቋቁማችሁ ሃይማኖታዊ ግዴታችሁን ለተወጣችሁ ሰባክያንና ዘማርያን በሃያሉ በመድኃኒዓለም ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ሽልማት

እንግዲህ እንደሚታወቀው ከዋልድባና ከመሳሰሉት ታላላቅ ገዳማትና አድባራት የመጡ አባቶች ተገፍተው፤ ተበድለው፤ፍትህ አጥተው፤ ቤተክርስትያን ሲቃጠልባቸው፣ ሲፈርስባቸው አቤት ለማለትና ለማሳወቅ በአሁን ግዜ ወደ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቢሮ ለመግባት በፍጹም ዝግ በሆነበትና በማይቻልበት ሁኔታ እንዲሁም ደግሞ በሌላ በኩል የመንግስት ጉዳይ አስፈጻሚዎች የቤተክርስትያን አፍራሽ ሃይሎች ለእነርሱ ደግሞ ክፍት ሆኖ እንደፈለጉ የሚወጡበትና የሚገቡበት በሆነበት በአሁን ጊዜ የሚንሶታው ደብረሰላም መድኃኒዓለም ቤተክርስትያን አፍራሽ ሃይሎች እንደ ፈለጉ ሲወጡና ሲገቡ እንዲሁም ላደረጉት(ላበረከቱት) ቤተክርስትያንን የመክፈል ስራ ሽልማታቸውን ከአቡነ ማትያስ ጋር ፎቶ በመነሳት አሳይተውናል።

ማጠቃለያ

እንግዲህ ይህ ሁሉ ሲፈጸም እነዚህ ቤተክርስትያንን በማፍረስ(በመክፈል) ላይ የሚገኙ አማሳኞች እራሳቸውን ንጹህ፣ ቅዱስ ፣ጻድቃን ፣ሃይማኖተኞች በማድረግ ሌላውን ለማዳከምና ለማፍረስ የሚፈልጉትን ቤተክርስትያንና ምእመናንን ፖለቲከኛ ፣ሃጥያተኛ ፣ በማድረግ በድፍረት የናገራሉ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የሚሰሩትን ጳጳሳት ትክክለኛ ናቸው ሲሉ የእነርሱን ሃሳብ የማይደግፉትን ፣የሚያስታርቁትን፤የሚመክሩትን ያውም የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑትን እውነተኛ አባቶችን ይሳደባሉ፤ያንቋሽሻሉ ትክክለኛ አባት እንዳልሆኑ ለደጋፊዎቻቸውና ለምእመን ይናገራሉ ደግሞ ልዩ መለያቸው ዓይን ያወጣ ውሸት ነው ።ይህን ደግሞ በሚንሶታ ደብረሰላም መድኃኒዓለም ቤተክርስትያን አይተነዋል።

እንግዲህ ውድ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስትያን ምዕመን ሆይ አንድ ልናጤነው የሚገባ በአሜሪካን አገር በሲኖዶስ ስር ነን የሚሉት በሙሉ በስም ብቻ በሲኖዶስ ስር ነን ይላሉ እንጂ አንድም ቅዱስ ሲኖዶስ የአዘጋጀውን መመሪያ ማለትም ቃለ ዓዋዲ ተግባራዊ የሚያደርግ የለም የሲኖዶሱን መመሪያ ተግባራዊ ሳያደርጉ (በሲኖዶስ ማዕቀፍ) ውስጥ ሳይገቡ ሌላውን መወንጀል ከፈረሱ ጋሪውን ማስቀደም ነው እንዲሁም ለግለሰቦች መጠቀሚያ መሆን እንጂ ለቤተክርስትያኒቱ የሚያስገኘው ነገር ስለሌለ እርምት ሊወሰድበት ይገባል። ደግሞም ቅዱስ ሲኖዶሱ ከስርአት ውጭ ነው ብሎ ምንም አይነት ተግሳጽም ሆነ ውግዘት ያላደረገበትን ቤተክርስትያን እንዲሁም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን የሚጠይቅ ጉዳይ አንድ ጳጳስ በግሉ ተነስቶ ሊለየው (ሊያወግዘው) አይችልም ተቀባይነትም አይኖረውም እንደውም ቅዱስ ሲኖዶሱ ስርአትን በመጠበቃቸው የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስትያንን ቀኖናና ዶግማ በመከተላቸው ህዝበ ክርስትያኑን በደንብ በስርአትና በኃይማኖት መምራት ይችላሉ ብሎ፦
አቡነ ዳንኤልን ከሚንሶታው ደብረሰላም መድኃኒዓለም ገለልተኛ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶሱ ለጵጵስና ሲሾማቸው እንዲሁም
አቡነ ፋኑኤልን ከዲሲ ሚካኤል ገለልተኛ ቤተክርስትያን ያን ቅዱስ ሲኖዶሱ ለጵጵስና ሲሾማቸው እነዚህ ስርአት አስከባሪዎቹ የት ነበሩ ?

ቅዱስ ሲኖዶስ ከገለልተኛ ቤተክርስትያን እየጠራ ሹመትን ሰጣቸው እንጂ አልለያቸውም ቅዱስ ሲኖዶስ ሲሾም ሌላው የቅዱስ ሲኖዶስ የበላይ ሆኖ ሊያወግዝም ሆነ ሊለይ እንደማይችል ለመግለጽ እወዳለሁኝ ስለዚህ በአሁን ግዜ እንደወረርሽኝ እየተስፋፋ የመጣውን ጉዞወደ እናት ቤተክርስትያን(እንቀላቀል)የሚለው የተሞከረባቸውን የተለያዩ አብያተ ክርስትያናትና ምእመናን ላይ ያስከተላቸውን ችገሮች ስንመለከት እንኩዋን አንድነትን ሊያመጣያ ቀርቶ በአንድነት የነበሩትን ምእመናን የበተነ፣ዘመዳማቾችን የለያየ ፣ባልና ሚስትን ያለያየ ፣በኢኮኖሚና በማህበራዊ ምዕመኑን ያቃወሰ እነዲሁም ስለቤተክርስትያን በጋራ ሆኖ ይሰራና ይነጋገር የነበረውን እንዳይሰራና እንዳይነጋገር ያደረገ ነው። ስለዚህ ማንኛውም የኢ/ኦ/ተ/ ቤተክርስትያን አማኝ ሊያደርገው የሚገባው ጥንቃቄ ማንም ተነስቶ እንቀላቀል ቢል ቤተክርስትያንን የሚያፈርሱና የሚያዳክሙ አማሳኞች መሆናቸውን ማወቅ አለብን ይህ ጉዳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የሚጠይቅ ስለሆነና ማንም ጳጳስም ሆነ ፓትርያርክ በግል የሚጽፉት ደብዳቤም ሆነ መልእክት የቤተክርስትያን ድምጽ አለመሆኑን በማወቅ ልንቃወመው ይገባል የቤተክርስትያን የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሆነ ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚመጡት መልእክቶች ብቻ የቤተክርስትያን ድምጽ መሆናቸውን መረዳት ይኖርብናል ።

በመጨረሻም በመንግስት የምትመኩ ፤በዘርና በጎሳ የተመካችሁ፤ በስልጣን ጥማት የሰከራችሁ፤በፍቅረ ነዋይ የታወራችሁ፤ክርስቶስን የማታውቁ ግን የክርስቶስ አገልጋዮች ነን የምትሉ በሙሉ ቤተክርስትያንን በማወክና ሰላሟን በማደፍረስ በመክፈል እንዲሁም በማዳከም ላይ የተሰማራችሁ ጳጳሳት ፤ካህናት፤ዲያቆናት ፤ግለሰቦች እስቲ ለአንድ ሰከንድ ቆም ብላችሁ የተሰቀለውን ክርስቶስን አስቡት ያን ግዜ እውነትን ታይዋታላችሁ እውነት ደግሞ የተሰቀለው ክርስቶስ እንጂ መንግስት አይደለም መንግስትም ይቀየራል፤ስልጣንም ይቀራል፤ገንዘብም ይጠፋል ሁሉም ያልፋል የማያልፈው እውነት ብቻ ስለሆነ ስለ እውነትን መስክራችሁ ሰማእት ለመሆን ሞክሩ።ከቻላችሁ እውነትን ተናገሩ ካልቻላችሁ ሃሰትን አትናገሩ ይህንንም ካልቻላችሁ ዝም በሉ።

ስለ እውነት ምንነት ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ከጻፉት ላይ በማቅረብ ጽሁፌን ልደምድም

እውነት ማለት የኔ ልጅ

እውነት ጽድቅ እንዳይመስልሽ ኩነኔ ነው እውነት ያማል

አይታከሙት ደዌ ያከሳል ያጎሳቁላል

ሁሌ አያስከብርሽም አንድ አንዴ ህይወት ያስከፍላል

ልጄ እውነት ከህይወት ይከብዳል

በመኖር ከህይወት ተገኝቶ መልሶ ህይወት ይበላል ።

__

<< እግዚአብሄር አምላክ ፍቅርን ይስጠን >>


No comments:

Post a Comment

wanted officials