Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, October 12, 2015

የአዲስ አበባ የወተት ምርቶች ለጉበት ካንሠር እንደሚያጋልጡ ጥናቶች አመለከቱ



(የቀለም ቀንድ) አዲሱ የዐለም አቀፍ የእስሳት ሐብት ምርምር ኢንስቲትዩት (ILRI) ጥናት ውጤት በሰፊው የአዲስ አበባ ከተማ በሚሰራጩ የወተት ተዋጽኦ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የጉበት ካንሰር አጋላጭ ‹አፍላቶክሲን› የተባለ ኬሚካል እንዳለባቸው ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ ይፋ የሆነው ባለፈው ሐምሌ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ሲሆን የወተት ምርቶቹ ለተጠቃሚዎች ጤና ስጋት እንደሆኑ በሰፊው አትቷል፡፡


በጥናቱ መሠረት አፍላቶክሲን (Aflatoxin) የተባለው ለጉበት ካንሠር አጋላጭ ኬሚካል አራት ምድቦች ሲኖሩት ቢ1፣ ቢ2፣ ጂ1ና ጂ2 በመባል ይታወቃሉ፡፡ አፍላቶክሲን በየዓመቱ 90000 (ዘጠና ሽህ) ያክል ለሚሆኑ በጉበት ካንሠር በሽታ ለሚሞቱ ሰዎች ምክንያት እንደሆነ ጥናቱ አክሎ ገልጧል፤ በተለይ የህጻናትን የበሽታ መከላከል አቅም በማሳነስ የበለጠ ተጠቂ ያደርጋቸዋልም ብሏል፡፡


ከአፍላቶክሲን ጋር የተነካካ የእንስሳት መኖ በእንስሳት ምርት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ የወተት፣ የስጋና የእንቁላል ምርቶችን በሚጠቀሙ ሰዎች በተለይም ደግሞ ሕጻናትን ለማይድን ካንሠር ያጋልጣቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቀደም ብለው በተደረጉ ጥናቶች በጥራጥሬ ምግቦችና በተደቆሰ በርበሬ (ድልህ) አፍላቶክሲን እንዳለ ተረጋግጧል፡፡ አዲሱ በጆርናል ኦፍ ፉድ ኮንትሮል (Journal of Food Control) የታተመው ጥናት ግን በአዲስ አበባ በሰፊው በሚሰራጩ የወተት ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ አፍላቶክሲን መገኘቱን አሳውቋል፡፡

ከአለም አቀፉ የእስሳት ሐብት ምርምር ተቋም በተውጣጡ ሳይንቲስቶች ከመስከረም እስከ የካቲት 2007 ዓ.ም ድረስ የተካሄደው ጥናት የአፍላቶክሲንን መገኘቱንና መጠኑም ምን ያክል እንደሆነ በዝርዝር አትቷል፡፡ ተመራማሪዎቹ አዲስ አበባን የመረጡበትን ምክንያት ሲያስረዱ በርካታ በአፍላቶክሲን ጋር ተያያዥነት ያላቸው የጤና እክሎች መገኘታቸው ነው ብለዋል፡፡

በጥናቱ 110 የወተት ናሙና (100 ከወተት ከብት አርቢዎችና 10 ከነጋዴዎች) እንዲሁም 156 የእንስሳት መኖ ናሙና (114 ከገበሬዎችና 42 የእንስሳት መኖ አምራች ተቋማት) ተወስዷል፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው የወተት ምርት የአፍላቶክሲን ኬሚካል የተገኘበት ከመሆኑም በላይ የአውሮፓ ሕብረት ካስቀመጠው ስታንዳርድ በ0.05 ማይክሮ ግራም በእያንዳንዱ ሊትር ላይ ጭማሪ አለ፡፡ በእንስሳት መኖው ላይ የተደረገው ጥናት ደግሞ ሙሉ በሙሉ አፍላቶክሲን ሲገኝበት በኪሎ ግራም ከ7 እስከ 419 ማይክሮ ግራም ከመጠን የዘለለ ነው ተብሏል፡፡

ይኸው ጥናት ፋጉሎ የሚመገቡ ከብቶች አፍላቶክሲንን የመያዝ እድላቸው የሠፋ እንደሆነ አትቷል፡፡ በአንድ ኪሎ ግራም ፋጉሎ ውስጥ ከ290 እስከ 397 ማይክሮ ግራም መጠን ያለው አፍላቶክሲን ይገኛል፡፡ ተመራማሪዎቹ የጉበት ካንሠር አምጭ የሆነውን አፍላቶክሲን ለመቀነስ በእንስሳት ምርት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ከብቶቻቸውን ከፋጉሎ ውጭ የሆነ መኖ እንዲያቀርቡላቸው አስተያየት አቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም አፍላቶክሲንን መከላከል የተመለከተ የግንዛቤ ሥራ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ አጥኝዎቹ ፖሊሲ አውጭዎችና በልማት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ለጤና ስጋት የሆኑ ነገሮችን መረጃ መስጠት ላይ እንዲያተኩሩ በመጠቆም ምርምራቸውን ደምድመዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ የስነ ምግብ ምርምር ተቋምና የጤና ጥበቃ ሚንስቴር በጉዳዩ ላይ ያሉት የለም፡፡ የጉበት ካንሠር የተጠቃ ሰው በህይወት የመቆዬት እድሉ ከ6 እስከ 18 ወራት ብቻ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

Source:c(የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ቅጽ 3፡ ቁጥር 11)

No comments:

Post a Comment

wanted officials