ባለፈው ቅዳሜ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ በደረሰው ቃጠሎ የ23 ሰዎች ህይወት ማለፉን መንግስት ገለፀ
(ኤፍ.ቢ.ሲ) ቅዳሜ ነሃሴ 28 ቀን 2008 በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ አደጋ የ23 ሰዎች ህይወት ማለፉን የመንግስት ኮሙዩኒኬኘን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ገለፀ።
ፅህፈት ቤቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል በአደጋው ወቅት በመረጋገጥ፣ በጭስ በመታፈን እና በቃጠሎ የሞቱት ሰዎች 21 ሲሆን፥ ሁለት ታራሚዎች ደግሞ ለማምለጥ ባደረጉት ሙከራ ህይወታቸው አልፏል።
በቃጠሎው የማረሚያ ቤቱ ሁለት ህንፃዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን መግለጫው አመልክቷል።
የታራሚዎች መገልገያ የሆኑ ፍራሾች እና ብርድልብሶች እንዲሁም የታራሚዎች የጋራ መገልገያ የሆኑት እንደ መዝናኛ ማዕከላት እና ሌሎች የጋራ መገልገያዎች ተቃጥለዋል።
በአሁኑ ጊዜ ፖሊስ የሟቾችን አስከሬን ተረክቦ አስፈላጊውን ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝና በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ዘጠኝ ታራሚዎች እና የፖሊስ አባላት የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ መደረጉን መግለጫው ጠቅሷል።
በእሳት አደጋው ወቅት ታራሚዎችን ከቃጠሎው እና ከጭስ መታፈን ለማውጣት ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም መንግስት አስታውቋል።
እሳቱን ለማጥፋት የፖሊስ አባላት፣ የአዲስ አበባ የድንገተኛና የእሳት አደጋ መከላከያ አባሎች፣ ታራሚዎች እና የአከባቢው ነዋሪ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ቃጠሎው ወደሌሎች አከባቢዎች እንዳይስፋፋ እና ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ ርብርብ ማድረጋቸውንም ነው ያነሳው።
አብዛኛው የታራሚዎች መኖሪያ ቤት በቃጠሎው በመውደሙ ምክንያት ታራሚዎች ለጊዜው ወደተለያዩ የፌደራል ማረሚያ ቤት ቅርንጫፎች እንዲሄዱ መደረጉም ተገልጿል።
በአሁኑ ጊዜ የአደጋው መንስኤ በፌደራል ፖሊስ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ እና በፌደራል ማረሚያ ቤቶች የጋራ ምርመራ ቡድን እንዲሁም ሰፊውን ታራሚ በማሳተፍ እየተጣራ ይገኛል ብሏል መግለጫው።
ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን የተመኘው መንግስት፥ የቀጠሮ ማረሚያ ቤቱ ቶሎ ተጠግኖ የተለመደ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ በመሆኑ ተገልጋዮች እና ቤተሰቦች በትእግስት እንዲጠባበቁ ጠይቋል።
No comments:
Post a Comment