Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, September 22, 2016

አዲስ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአምስት ምሁራን የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ።


ዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ ታኅሳስ 12 ቀን 2009 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ህግ በሚያዘው መሠረት የምርምር፣ የማስተማርና የማኀበረሰብ ሥራዎቻቸው በየትምህርት ክፍሎቻቸው ጉባዔዎች፣ በኮሌጆቹ የአካዳሚክ ኮሚሽኖች፣ በተለያዩ የውጭና የአገር ውስጥ ምሁራንና በሴኔት ተገምግመው የቀረቡለትን አምስት ምሁራን የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አጽድቋል።
በዚሁ መሠረት ኘሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ፣ ፕሮፌሰር መሐመድ ሀሰን፣ ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ፣ ፕሮፌሰር ጀማል ሃይደርና ፕሮፌሰር አስፋው አጥናፉ ዩኒቨርሲቲው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷል።
ኘሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ በእንሰትና በሥራሥር ተክሎች ላይ በርከት ያሉ ምርምሮችን በማከናወንና የድህረ-ምረቃ ተማሪዎችን በማማከር በታወቁ ጆርናሎች ላይ ከ31 በላይ ጽሁፎችን አሳትመዋል።
ብዙ የምርምር መረጃዎች በሌሉበት በእንሰት ተክል ላይ ስለ እንሰት አስተዳደግ፣ ሥነ-ምህዳር ምርታማነት፣ ሥነ-ምግብ፣ የብዝኀ-ሕይወት ልዩነትና ሥርጭት በርካታ ምርምሮችን አከናውነዋል።
በጥናታቸው የእንሰት ምርታማነት ከጊዜና ከሚይዘው ቦታ አንፃር ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሲወዳደር ምርታማነቱ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን፣ ከእንሰት ተክል የሚሠሩ ምግቦች የምግብ ንጥረነገሮች ይዘት ከሌሎች የሥራሥር ተክሎች የማያንስ መሆኑን በጥናታቸው አረጋግጠዋል።
በተለይም የእንሰት ምግቦች የብረትና ዚንክ መጠን ከሌሎች ሥራሥር ተክሎች የበለጠ መሆኑንና በሀገሪቱ የእንሰት አብቃይ አካባቢዎች በአካባቢው ቋንቋ የተለያዩ ስሞች የሚሰጧቸው የእንሰት ዓይነቶች በአብዛኛው በዘረ-መል የተለያዩ በመሆናቸው ያሏቸው የምግብ ንጥረ-ነገሮች ኘሮቲንና የመሳሰሉት መጠኖች እንዳላቸው ምርምር አድርገዋል።
ፕሮፌሰር አድማሱ በድንች ተክል ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ገበያ ድረስ ያለውን የምርትና የግብይት ሥርዓት በማጥናት የተክሉን ምርታማነት ለማሳደግ የሚረዱ መንገዶችን አሳይተዋል።
ኘሮፌሰር አድማሱ ከምርምርና ከማስተማር ሥራቸው ጐን ለጐን በቀድሞው የሐዋሳ ግብርና ኮሌጅ የአስተዳደር ዲን፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ኘሬዚዳንት፣ የአካዳሚክና ምርምር ምክትል ኘሬዚዳንትና ኘሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል።
ኋላም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመዛወር ላለፉት አምስት ዓመታት በኘሬዚዳንትነት እያገለገሉ ሲሆን፥ በአገር አቀፍ ደረጃ በተቋቋሙ የተለያዩ ቦርዶች በሰብሳቢነት፣ በምክትል ሰብሳቢነትና በአባልነት በማገልገል ለአገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚገኙ ምሁር ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ለፕሮፌሰር መሐመድ ሀሰን በክሮፕ ኢኮሎጂና ሪሶርስ ኮንሰርቬሽን የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷል።
ፕሮፌሰር መሐመድ በማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ በጂኦግራፊና የአካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሲሆኑ፥ በአፈርና አካባቢ ሳይንስ፣ በኃይድሮሎጂ፣ በመሬት አጠቃቀምና ተፋሰስ ልማት ላይ 40 ያህል የጥናትና ምርምር ውጤቶች በታወቁ ሙያዊ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል።
ዩኒቨርሲቲው በፍልስፍና የትምህርት ክፍል ለመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷል።
ፕሮፌሰር በቀለ ከሰላሳ ዓመታት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል በማስተማር፣ በምርምርና የማኅበራዊ ሳይንስ ዲንነትን ጨምሮ በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች አገልግለዋል።
የፕሮፌሰር በቀለ በፖለቲካዊ ፍልስፍና እንዲሁም በእንተርካልቸራል ፍልስፍና በማስተማርና በአፍሪካ ፍልስፍናና ማኅበራዊ መስኮች ከሃያ በላይ የምርምር ጽሑፎችን በታወቁ ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል።
ዩኒቨርሲቲው በጤና መስክም ለፕሮፌሰር ጀማል ሃይደር የፕሮፌሰርነት ማዕረግን የሰጠ ሲሆን፥ እኚህ ምሁር የተለያዩ የኑትሪሽን መረጃዎችን፣ የህፃናት አመጋገብ ማኑዋሎችና መፃፎችን ጽፈዋል።
ለፕሮፌሰር ጀማል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀጥረው በሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት በመምህርነት፤ በትምህርት ክፍልና በትምህርት ቤት ኃላፊነት በተለያዩ ጊዜያት ሲያገለግሉ ከ80 በላይ የምርምር ጽሁፎችን በተለያዩ የአለም አቀፍና በሀገር ውስጥ በሚገኙ ጆርናሎች አሳትመዋል።
በዚህም ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጤና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የቦዲ ኢሜጂንግ ሰብ ስፔሻሊስት ለሆኑትና በሙያቸው ከሃያ አምስት ዓመት በላይ ላገለገሉ ለዶክተር አስፋው አጥናፉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷል።
ፕሮፌሰር አስፋው በህክምና ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ትምህርት ቤት የራዲዮሎጂ ትምህርት ክፍሉን ከመሰረቱት አንጋፋ ራዲዮሎጂስቶች አንዱ ሲሆኑ እስከ አሁንም በማስተማር ሂደት ላይ ይገኛሉ።
ከዚህም በላይ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በማድረግ በአገር ውስጥና ውጪ ባሉ የምርምር ጆርናሎች ከሃያ ሰባት በላይ የምርምር ውጤቶችን ለህትመት አብቅተዋል።
ፕሮፌሰር አስፋው በተለያዩ የበሽታ ዓይነቶች ማለትም በቲቢ፣ ሊንፎማና የመሳሰሉ የሬዲዮሎጂ መገለጫዎችን በሚመለከት ለሕመምተኞችና የተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች በሬዲዮሎጂ አጠቃቀም ሊከተሉት የሚገባውን አካሄድ በማስመልከት በሰፊው ጽፈዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የሬድዮሎጂ ሙያ ደረጃና ለወደፊት ሙያውን ለማሻሻል ሊደረጉ የሚገባቸውን አቅጣጫዎችና ብሎም ከአገር ውጪ ካሉ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የአገልግሎቱንና የማስተማር ሂደት በምን መልክ መስፋፋት እና ማደግ እንደሚገባው በጥናታቸው አሳይተዋል።
ፕሮፌሰር አስፋው ባላቸው ተጨማሪና ተጓዳኝነት ባለው ICT ጋር በተያያዘ ሙያቸው ሬዲዮሎጂንና በአጠቃላይ የቴሌሜድስን አገልግሎት በኢትዮጵያ እና በመሳሰሉ ታዳጊ አገሮች የባለሙያዎችን እጥረት በማካካስ የህክምና ጥራትን ለማሻሻል እንደሚረዳና የአገሪቱን ሪፈራል መርሃ ግብር በምን መልክ መደገፍ እንደሚችል በምርምር ጽሁፋቸው አሳይተዋል፡፡
ፕሮፌሰር አስፋው የሞባይል ስልክ ቴክኖሎጂ በጤና አገልግሎት ላይ በአገራችን ሊኖረው የሚችለውን ከፍተኛ ሚና በተለይም የእናቶችና የህፃናት ሞትን ለመቀነስ በሚያስችልበት መልኩ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ሙከራ ለማድረግ የቴክኒዎሎጂውን ጠቀሜታ በማሳየት ስድስት የተለያዩ ጽሁፎችን አሳትመዋል፡፡
በአጠቃላይ ፕሮፌሰር አስፋው ባለፉት ሃያ አምስት አመታት ለአገሪቱ የሕክምና አገልግሎት፣ መማር ማስተማርና ምርምር ላይ በተለይም በሬዲዮሎጂ ሙያ መስፋፋት እና ጥራት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በዚህ መሠረት ዩኒቨርሲቲው በሬዲዮሎጂ የኘሮፌሰርነት ማዕረግ አሰጥቷቸዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ

No comments:

Post a Comment

wanted officials