በኦሮሚያ ምስራቅ አርሲ አራት የአጋዚ ክ/ጦር አባላት መገደላቸው ተገለጸ
ኢሳት ( መስከረም 13 ፥ 2009)
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ ዞን ዛሬ አርብ እለት አራት የአጋዚ ክ/ጦር አባላት መገደላቸው ታወቀ። አንደኛው ደግሞ መማረኩን የአይን ምስክሮች በምስል አስደግፈው ለኢሳት አድርሰዋል። የተማረከው የሰራዊት አባል ለማስለቀቅ በሚል ተጨማሪ ሃይል ወደ ስፍራው መድረሱና ተኩስ መቀጠሉን ለመረዳት ተችሏል።
በምስራቅ አርሲ አጄ አካባቢ ልዩ ስሙ ቀሲሳ ተራራ በተባለ አካባቢ በህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል በሚል በአጋዚ ክፍለ ጦር አባላት ላይ ጥቃት የፈጸሙት የአካባቢ ነዋሪዎች መሳሪያዎቹን ነጥቀው መሰወራቸው ታውቋል።
በስርዓቱ ይፈጸማል ያሉትን ግፍና በደል በመቃወም፣ በተለይም በህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመግታት በሚል ሰራዊቱ አባላት ላይ ዕርምጃ የወሰዱት ግለሰቦች ትጥቅ ይዘው ለትግል መነሳታቸውንም በቪዲዮ ባሰራጩት መግለጫ አስታውቀዋል።
በኦሮሞ ህዝብና በሙስሊሙ ላይ የሚደርሰው ጥቃት መቀጠሉ እንዳስቆጣቸውም ተደምጠዋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ አራት አጋዚ ክ/ጦር አባላት መገደል እንዲሁም የአንደኛው መማረክ የተረጋገጠ ሲሆን፣ በስፍራው ከተኩሱ ጋር ተያይዞ ስለደረሰው ጉዳት የታወቀ ነገር የለም። የተማረከው ወታደር እንዳልተለቀቀ ታውቋል።
No comments:
Post a Comment