Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, September 14, 2016

የቱርክ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ባለንብረቶች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ ብድርና የታክስ ክፍያ ሳይከፍሉ ከሃገር መኮብለላቸው ተሰማ

የቱርክ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ባለንብረቶች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ ብድርና የታክስ ክፍያ ሳይከፍሉ ከሃገር መኮብለላቸው ተሰማ
ኢሳት (ታህሳስ 18 ፥ 2009)
ሁለት የቱርክ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ባለንብረቶች ከመንግስት የወሰዱትን ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የባንክ ብድርና የታክስ ክፍያ ሳይከፍሉ ከሃገር መኮብለላቸው ተሰማ።
ለሁለት የቱርክ ባለሃብቶች ብድር ሰጥቶ የነበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ግለሰቦቹ ከኢትዮጵያ እንዳይወጡ ጥያቄውን ለኢሚግሬሽን ቢሮ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ጥያቄው በቶሎ ተግባራዊ ባለመደረጉ ምክንያት ባለሃብቶች ወደ ሃገራቸው ቱርክ መሄዳቸው ታውቋል።
ሳይፈቲን እና ኢማም አልቲንባ የተሰኙት ሁለት የቱርክ የጨርቃጨርቅ ባለሃብቶች ከመንግስት በወሰዱት ብድር ያቋቋሙት ኤልስ አዲስ ኢንዱስትሪያል ዴቬሎፕመንት ሃላፊነቱ የግል ኩባንያ ከአምስት አመት በፊት ወደ ምርት ስራ መግባቱን በሃገር ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጦች ዘግበዋል።
ይኸው በናዝሬት አዳማ ከተማ የሚገኘው የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ባለፈው አመት ወደ 4 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ባለመክፈሉ የሃይል አቅርቦቱ ተቋጦበት እንደነበር ተመልክቷል።
የጨርቃጨርቅ ፋብሪካው ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከመንግስት የወሰደውን ብድር በአግባቡ መክፈል እንዳልጀመረ የሚገልጽ ማሳሰቢያ ሲሰጠው እንደነበረም የባንኩ ሃላፊዎች አስረድተዋል።
ፋብሪካው የማምረት አቅሙ 95 በመቶ አካባቢ ደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ ምርቱን ወደ ውጭ እንዳልላከ በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ባንቲሁን ገሰሰ አዲስ ፎርቹን ለተሰኘው ጋዜጣ ተናግረዋል።
የፋብሪካው ባለንብረቶች በአጠቃላይ ከመንግስት 900 ሚሊዮን ብር አካባቢ ብድርና ያልተከፈለ የታክስ ዕዳ እያለባቸው ከሃገር የኮበለሉ ሲሆን፣ የባለሃብቶቹ መሰወር ተከትሎ ለፋብሪካው የጥጥ ምርት በማቅረብ ላይ የነበሩ 10 ድርጅቶችም ያልተከፈላቸው 20 ሚሊዮን ብር አካባቢ መኖሩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አስታውቀዋል።
እነዚሁ ጥጥ አቅራቢዎች የፋብሪካው ባለቤቶች በባንኮች ተቀባይነት የሌለው ቼክ ሲሰጧቸው እንደነበርም ለመንግስት ባቀረበቱት አቤቱታ ገልጸዋል።
የጨርቃጨርቅ ፋብሪካው ከመቋቋሙ ጊዜ ጀምሮ በአምስት ዙሮች ለእቃ ግዢዎችና ለስራ ማስኬጃዎች በማለት ብድሩን ሲወስድ የቆየ ሲሆን፣ የአንድ አመት ያልተከፈለ የግብር ዕዳው ብቻ 30 ሚሊዮን ብር አካባቢ መሆኑም ታውቋል።
ባለንብረቶቹ ከሃገር ከመውጣታቸው በፊት የፋብሪካው ማሽነሪዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ አበላሽተው የነበረ ቢሆንም፣ መንግስት የውጭ ባለሙያዎችን በማስመጣት ብልሽቱ መፍትሄ እንዲያገኝ ማድረጉንም ለመረዳት ተችሏል።
ለፋብሪካው ብድርን የሰጠው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፋብሪካውን በ729 ሚሊዮን ብር ለመሸጥ ጨረታን አውጥቶ የሚገኝ ሲሆን፣ ፋብሪካው ወደ 1ሺ የሚጠጉ ሰራተኞች እንዳሉት ታውቋል።
በጋምቤላ ክልል ተመሳሳይ ሁኔታ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ የተሰማሩ የህንድ ባለሃብቶች ከመንግስት የወሰዱትን ከፍተኛ ብድር ሳይመልሱ ከሃገር መኮብለላቸውን ስንዘግብ መቆየታችን የሚታወስ ሲሆን፣ የመንግስት ባለስልጣናት በህንድ ባለሃብቶች ያልተመለሰውን የብድር መጠን ከመግለፅ ተቆጥበዋል።
በክልሉ በጫት ቤቶች ሳይቀር የመሬት ይዞታ ካርታ ሲሰጥ መቆየቱን የገለጹት ባለስልጣናት ይህንኑ ህገወጥ ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉ አምስት አመራሮችና ስምንት ባለሙያዎች ለእስር መዳረጋቸውን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጋትሎዋክ ቱት ለመንግስት መገኛኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ በቅርቡ በጋምቤላ ክልል ከመሬት አሰጣጥ ጋር ተፈጽሟል ከተባለው የሙስና ድርጊት ጋር በተያያዘ 13 የክልሉ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል። ወደ 4.9 ቢሊዮን ብር ብድር በወሰዱት የትግራይ ባለሃብቶች በልማት ባንኩ ሃላፊዎች ላይ ግን የተወሰደ ርምጃ የለም።
በርካታ ባለሃብቶች በተመሳሳይ መሬት ላይ ብድርን በመውሰድ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ላይ በቢልዮን የሚቆጠር ኪሳራ ማድረሳቸውና በክልሉ በኢንቨስትመንት ስም የተካሄደው መሬት የመስጠት ዘመቻ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ መብለጡን 15 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ጥናቱን ማቅረቡ ይታወሳል። የትግራይ ባለሃብቶች ቡድኑ የወሬኞችና የአሳባቂዎች ደጋፊ ሲሉ መዝለፋቸው ይታወሳል

No comments:

Post a Comment

wanted officials