ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የሃረር ውሃ ፕሮጀክት መክኖ መቅረቱን መረጃዎች ጠቆሙ
ሰኔ ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-
ከክልሉ ውሃ ልማት ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የሃረር ከተማን የውሃ ችግር ለመቅረፍ በሚል በተለያዩ ወቅቶች ከ747 ሚሊዮን 175 ሺ ብር በላይ ወጪ ቢደረግም አብዛኛው ፕሮጀክቶች በመክሰማቸው የከተማው ህዝብ ለአሳሳቢ የውሃ ችግር ተዳርጓል።
የከተማውን የውሃ ችግር ይቀርፋል ተብሎ ከፍተኛ ግምት የተጣለበት የሃሰሊሶ መስመር መጠናቀቁን ተከትሎ ለምረቃ የተዘጋጀው መጽሄት ” ውሃ በፈረቃ ድሮ ቀረ!” በሚል ርእስ ሃምሌ 2004 ዓም ባሰፈረው ጽሁፍ ” በሀረር ከተማ የመጠት ውሃና ሳንቴሽን ፕሮጀክት ግንባታው በመጠናቁ ከድሬዳዋ አስተዳደር የሃሰሊሶ ቀበሌ ገበሬ ማህበር፣ የድሬዳዋ ፖሊስ አካዳሚ፣ የገነት መናፈሻ አካባቢ፣ የጀሎ በሊናና ሀርላ ገጠር ቀበሌዎች ተጠቃሚ ሲሆኑ ከመስራቅ ሃረርጌ አስተዳደር ደግሞ የደንገጎ፣ የአዴሌ፣ የሃረማያና አወዳይ የወሌንቦ ገጠር ቀበሌ፣ እንዲሁም የሃረማያ ዩኒቨርስቲ እና የሃረር ከተማ ነዋሪዎች ባለድርሻ ተጠቃሚ በመሆናቸው ከሁለት አስር አመታት በላይ የዘለቀው የነዋሪዎቹ መሰረታዊ ችግር የነበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ ተቀርፎላቸው የ24 ሰአት ተጠቃሚ ሆነዋል” ሲል ይገልጻል።
መጽሄቱ በመቀጠልም ” በክልላችን የተጀመሩትን የልማት ግንባታዎች ከማፋጠኑም በላኢ በከተማችን የተሻለ የማህበራዊ አገልግሎት እና የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ከዚህ በሁዋላ የሃረር ከተማ የውሃ አቅርቦት ጉዳይ ለጸረ-ሰላም ሃይሎች የፖለቲካ መቀስቀሻ አጀንዳ መሆኑም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያከትማል።” ሲል ያትታል።
ይሁን እንጅ ከሁለት አመት በሁዋላ ይህ ብዙ የተባለለት ፕሮጀክት አደጋ ውስጥ በመውደቁ ሃረር በውሃ ችግር አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች።
ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የሃሰሊሶ መስመር ሙሉ በሙሉ ሲቋረጥ በሃረር ኤረር ሸለቆ የተቆፈሩት 7 ጥልቅ ጉድጓዶች ደግሞ በሃረሪ ክልል እና በኦሮምያ ምስራቅ ሃረርጌ ዞን በባሌ ወረዳ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት እና ውዝግብ ምክንያት በኦሮምያ ክልላዊ መንግስት ውሳኔ እስከሚሰጥበት በሚል ስራው ተቋርጧል፡
የሶስትዮሽ የጋራ ሀብት የሆነው እና 3 ክልሎችን ማለትም ሃረሪ፣ ኦሮምያንና ድሬዳዋን አቆራርጦ የሚሄደው ከ1998 እስከ 2004 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ የተሰራው የሀሰሊሶ ውሃ ከ747 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የወጣበት ሲሆን ፣ 350 ሺ የሚደርስ ህዝብ ለ30 ዓመታት ያለምንም እንከን እንደሚያጠጣ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ይሁን እንጅ ” ውሃ በፈረቃ ድሮ ቀረ፣ ውሃ በቦቴ ቀረ” ተብሎ የተጻፈበት የብእር ቀልም ሳይደርቅ ፣ ፕሮጀክቱ 2ኛ አመት የምረቃ በአሉን ሊያከብር ሁለት ወራት ሲቀረው የውሃ መስመሩ ተቋርጧል።
ክስተቱ በክልሉ ባለስልጣናት እና ባለሙያዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ የፈጠረ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በሙስና ምክንያት እንደቆመ የውስጥ አዋቂ ምንጮች ይገልጻሉ።
የተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 340/95 ” ለሃረር ከተማ የንጹህ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከአፍሪካ ልማት ፈንድ ብድር ለማግኘት የተፈረመ የብድር ስምምነት” በሚል ያወጣው አዋጅ ከ2005 ዓም ጀምሮ በ40 አመታት የሚከፈል 215 ሚሊዮን ብር መንግስት ከአፍሪካ ልማት ባንክ ገንዘብ መበደሩን ያመለክታል። እንዲሁም ለአቅም ግንባታ በሚል 12ሚሊዮን ተጨማሪ እርዳታ ተሰጥቶበታል።
በፕሮጀክቱ ከተሳተፉት መካከል ሲዮም የተባለው የፈረንሳይ ኩባንያ አጠቃላይ ሂደቱን በመምራቱ 18 ሚሊዮን ብር፣ የቻይና ኮንስትራክሽን እና ኦቨርሲስ ኩባንያ የሲቪል ግንባታዎች ለመስራት 49 ሚሊዮን ብር፣ የህንዱ ቴክኖፋብ ለኤሌክትሮ መካኒካልና ለፓምፕ እና ለመሳሰሉት 100 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም የኔዘርላንዱ ቬቲንስ ኢቪዴስ ኢንተርናሽናል በውሃው ያለውን ከፍተኛ የካልስየም ባይ ካርቦኔት ስራ ለመስራት 37 ሚሊዮን ብሮች ተከፍሎአቸዋል።
ፕሮጀክቱ እንደተጠናቀቀ ሃረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በአዲሱ የውሃ መስመር በአመት ለኤሌክትሪክ ፍጆታ እና ለጥገና የማወጣው ወጪ 13 ሚሊዮን ብር ነው በሚል ምክንያት ቀድሞ ከነበረው ታሪክ ላይ 100 ፐርሰንት በመጨመር ነዋሪዎች ከታህሳስ 1 /2005 ዓም ጀምሮ በአዲሱ ታሪክ መሰረት እንዲከፍሉ አድርጓል።
የሃሮማያ ሃይቅ ሙሉ በሙሉ በደለል ተሞልቶ የከብት ግጦሽ መሬት ቢሆንም ከሃይቁ በስተምስራቅ ዳር ኢፋቴባ በሚባለው ቀበሌ ለመጠባበቂያነት የተቆፈሩት 7 ጉድጓዶች በአሁኑ ወቅት ለነዋሪው ባለውለታ እየሆኑ ነው።
ዳገታማ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች 20 ሊትር ውሃ በ10 ብር እየገዙ ሲሆን ፣ በክልሉ ያሉት ሁለቱ የውሃ ቦቴዎች በደርሶመልስ ጉዞ 40 ኪሜ ያክል ስለሚጓዙ የነዋሪውን ፍላጎት ማርካት ቀርቶ ማቃመስ አልቻሉም።
የሃረሪ ክልል እና የኦሮምያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን በባቢሌ ወረዳ ስር የሚገኘው ኤረር ሸለቆ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ በተገመተው ወጪ 7 ከፍተኛ ጥልቅ ጉድጓዶች በቅርቡ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ወጥቶበት በተገዛ የውሃ መቆፈሪያ ማሽን ቢቆፈርም፣ የባብሌ ወረዳ መስተዳደር ባነሳው ” የእንካፈል” ጥያቄ በተፈጠረ ውዝግብ የኦሮምያ ክልል ምላሽ እስከሚሰጥ በሚል ስራው እንዲቆም ተደርጓል።
የሃሰሊሶ ውሃ የተቆፈረው በሀረሪ ክልል ተበዳሪነትና ወጪ እድራጊነት ሲሆን የድሬዳዋ መስተዳደርና የኦሮምያ ምስራቅ ሃረርጌ ዞን መስተዳደር ” ውሃ ካላካፈላችሁን አናስቆፍርም” በማለታቸው ውሃ እንዲካፈሉ ተደርጓል።
በሃረር የውሃ እና የዘይት አቅርቦት ችግር መከሰቱን በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment