Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, June 20, 2014

የጅማ ዩኒቨርስቲ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎች ለመጾም ተቸግረዋል

የጅማ ዩኒቨርስቲ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎች ለመጾም ተቸግረዋል፤ ‹‹የአምልኮ፣ የአለባበስና አመጋገብ መመሪያ›› አፈጻጸም እንደ ሓላፊዎች እምነት የሚወሰን ኾኗል

  • ‹‹መመሪያው በኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ላይ በማተኮር በአድሏዊነት ይፈጸማል›› /ተማሪዎቹ/
  • ‹‹መንግሥት ለሙስሊም ኾነ ለክርስቲያን ተማሪዎች በልዩ ኹኔታ ምግብ እንዲዘጋጅ ፈቅዷል›› /የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሚያዝያ ፳፻፮ ዓ.ም. የመመሪያው አጸፋዊ ማብራሪያ/
  • ‹‹ዩኒቨርስቲው ያወጣው መመሪያ ላይ እንዲህ የሚል የለም፤ ሴኩላሪዝም ባለበት ዩኒቨርስቲና በዩኒቨርስቲው የሴኔት ሕግ መሠረትየሰኔን ጾም ይኹን ሌላውን ጾም የማጾም ግዴታ የለብንም፤ ዩኒቨርስቲው የራሱ ፕሪንስፕልና መመሪያ አለው፡፡›› /በአድሏዊነት የሚከሰሱት የተማሪዎች ዲን አቶ እውነቱ ኃይሉ/
(ሰንደቅ፤ ፱ኛ ዓመት ቁጥር ፬፻፶፰፤ ረቡዕ ፲፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
በጅማ ዩኒቨርስቲ የተለያዩ ካምፓሶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎች በሥርዓተ እምነታቸው የተደነገጉ የዐዋጅ አጽዋማትን በመጾም ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ለመወጣት መቸገራቸውንና የትምህርት ተቋማት የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያውን በአድሏዊነት በሚያስፈጽሙ ግለሰብ ሓላፊዎች ምክንያት የእምነት ነጻነታቸው እየተረገጠ መኾኑን ለሰንደቅ ገለጹ፡፡
በጅማ ዩኒቨርስቲ የዋናው ግቢ፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ የግብርናና እንስሳት ካምፓሶችና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪዎች ለሰንደቅ እንደተናገሩት፣ ከሰኔ 2 ቀን 2006 ዓ.ም. አንሥቶ የተጀመረውን የሐዋርያት ጾም /በተለምዶ የሰኔ ጾም/ በተማሪዎች ዲኑ በኩል ‹‹የሰኔ ጾም የሚባል የምናውቀው ነገር የለም›› በመባላቸው ምክንያት ሥርዓተ እምነታቸውን ለመፈጸም እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡
ጾመ ሐዋርያት/የሰኔ ጾም/ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሰባት ዓመት ዕድሜ በላይ የሚገኙ ምእመናንዋ እንዲጾሟቸው ካዘዛቸው ሰባት የሕግ/የዐዋጅ/ አጽዋማት አንዱ ነው የሚሉት ተማሪዎቹ፣ የጾም ምግብ ባለመዘጋጀቱ ጾማቸውን ለማፍረስ የተገደዱ ተማሪዎች እንዳሉና የተቀሩትም በጾም ከዋሉ በኋላ ዳቦና ውኃ ከመቅመስ በቀር የሚመገቡት እንደሌላቸው በምሬት ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ኅብረት በጉዳዩ ላይ ከዲኑ ጋራ ያደረገው ውይይትም በዲኑ ‹‹ማንም የፈለገውን ቢል አይዘጋጅም›› በሚል የተለመደ ጥላቻ የተሞላበት ዕብሪትና የሚያራምዱት ፕሮቴስታንታዊ እምነት የተጫነው አቋም ሳቢያ ውጤት እንዳላመጣ ጠቅሰዋል፡፡
በአጽዋማት ወቅት የጿሚ ተማሪዎችን ብዛትና ስም ዝርዝር ለተማሪዎች ዲኑ በማስታወቅ የጾም ምግብ በቁጥራቸው ልክ እንደሚዘጋጅላቸው ያወሱት ተማሪዎቹ፣ ከመመገብ ታቅበው በሚቆዩበት ሰዓት የማይጠቀሙበትን ኮታቸውን ከካፊቴሪያው በማውጣት በሰዓታቸው መመገብ ይችሉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ከ2004 ዓ.ም. ዐቢይ ጾም ጀምሮ ግን ጥዋት በቁርስ ሰዓት ከሚያወጡት አንድ ዳቦ በስተቀር ከሌሎች እምነት ተከታዮች በተለየ የካፊቴሪያውን አገልግሎት ማግኘትና በጀታቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡
የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያው፣ በግቢው ውስጥ ሃይማኖትን የሚገልጽ ነገር ለብሶ መግባት እንደማይቻል የሚያዝዘውን ብናከብርም ከሌሎች እምነት ተከታዮች በተለየ ትኩረት የግቢው የጸጥታ አካላት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎችን በማሸማቀቅ እናደርገዋለን የሚሉት ቁጥጥር አድሏዊነት የሚታይበትና ፍትሐዊነት የጎደለው መኾኑን ገልጸዋል፡፡mk gibi gubae students00
[በቀዳም ስዑር ዕለት ተማሪዎቹ በራሳቸው ላይ ቄጤማ እንዳሰሩ ወደ ሲገቡ ቄጤማውን እንዲያስወግዱ ታዝዘዋል፤ የበዓለ ትንሣኤ ሌሊት ከቅዳሴ በኋላዳ ግቢው ሲመለሱ ለክብረ በዓሉ የለበሱትን ነጭ የሀገር ልብስ እንደለበሱ ወደ ግቢው እንዳይገቡ ተከልክለዋል፡፡ በመመሪያው መሠረት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሔዱ የለበሱትን ነጠላ ከዩኒቨርስቲው ግቢ በር ላይ አጣጥፈው ይዘው የሚገቡ ቢኾንም ያጣጠፉትን ነጠላ በትክሻቸው ጣል አድርገው ከታዩ በጥበቃ አባላት አጸያፊ ኃይለ ቃል ይሰነዝርባቸዋል፡፡
በአንፃሩ በሌሎች እምነት ተከታዮች ላይ (ማንነትን በግልጽ አያሳውቅም በሚል ከሰላምና ደኅንነት አጠባበቅ አኳያ ተከልክሏል የተባለውን ኒቃብ በሚያደርጉ ሙስሊም ተማሪዎች ይኹን እምነት ገላጭ ጥቅሶች ያለባቸው ቲሸርቶችን በሚለብሱ ፕሮቴስታንት ተማሪዎች) ምንም ዓይነት ቁጥጥር ሲደረግ እንደማይታይ ተገልጧል፡፡ በአለባበስና ሥርዓተ አምልኮ ረገድ በአድሏዊነትና ፍትሐዊነት በጎደለው የተማሪዎች አያያዝ ከፕሮቴስታንቱ የተማሪዎች ዲን አቶ እውነቱ ኃይሉ በተጨማሪ ስማቸው የሚነሣው የዩኒቨርስቲው የጸጥታ ሓላፊ ኢንስፔክተር ካሊድ አባ ተማም ናቸው፡፡
በሥርዓተ አምልኮ ረገድም የእምነታቸውን ክብር ለማስጠበቅ ባለፈው ዓመት በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ባቀረቡ ተማሪዎች ተደራራቢ ግፍ መፈጸሙ ተመልክቷል፡፡ ለተማሪዎቹ ሰላማዊ ጥያቄ ፖሊስ የኃይል ምላሽ ከመስጠቱም ባሻገር በዩኒቨርስቲው የሥነ ምግባር ደንብ ስም ጨርሶ ከትምህርት ገበታቸው የተባረሩ፣ ለአንድና ኹለት የታገዱ፣ ማስጠንቀቂያ የተላለፈባቸውና በተደራቢነት በዞን ፍ/ቤት ደረጃ ተከሰው ለእስራት የተዳረጉ ተማሪዎችም እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡]
ሰንደቅ በጉዳዩ ላይ በስልክ ያነጋገራቸው የተማሪዎች ዲን አቶ እውነቱ ኃይሉ፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግ ዐዋቃለኹ፤ ሴኩላሪዝም ባለበት ዩኒቨርስቲና በዩኒቨርስቲው የሴኔት ሕግ መሠረት የሰኔን ጾም ይኹን ሌላውን ጾም የማጾም ግዴታ የለብንም፤ ዩኒቨርስቲው የራሱ ፕሪንስፕልና መመሪያ አለው፤›› ብለዋል፡፡
በትምህርት ተቋማት እንዲተገበር በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በወጣው የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያ መንግሥት፣ ‹‹አቅም በፈቀደ መጠን ለክርስቲያንና ሙስሊም ተማሪዎች በተለየ ኹኔታ ምግብ እንዲዘጋጅ›› መግለጹን በመጥቀስ ዩኒቨርስቲው በመመሪያው መሠረት ለምን የተማሪዎቹን ጥያቁ እንደማያስተናግድ የተጠየቁት አቶ እውነቱ፣ ‹‹ዩኒቨርስቲው ያወጣው መመሪያ ላይ እንዲህ የሚል የለም፤›› በሚል የመመሪያውን ተግባራዊነት የሚቃወም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
መመሪያው በሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተተገበረ የጅማ ዩኒቨርስቲ የሴኔት መመሪያ መንግሥት ሴኩላሪዝምን አሰፍንበታለኹ ከሚለው መርሖ ልዩ ስለኾነበት ምክንያት ሲጠየቁም ‹‹እኔ ስለ ጅማ ዩኒቨርስቲ ብቻ ነው የማውቀው፤ ከተማሪዎች ጋራም ተወያይተናል፤ እዚያም የሚያደርስ አይመስለኝም፤ ወደፊትም እንወያያለን፤›› ብለዋል፡፡
ሐራዊ ማስታወሻ፡-
በበጀት ዓመቱ መንግሥትና ገዥው ግንባር፣ ‹‹በመዋቅራችንና በሕዝባችን ውስጥ ዘርፈ ብዙ ንቅናቄ በመፍጠር አክራሪነት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማነቆ እንዳይኾን›› የሚል ዓላማ በመያዝ፡- የመንግሥት መዋቅር አመራርና ሲቪል ሰርቪሱ ኹሉንም ሃይማኖት በእኩልነት የማገልገል አመለካከትና ተግባር ለመገንባት፤ የአምልኮ፣ የአመጋገብና የአለባበስ መመሪያውን በትምህርት ተቋማት ተግባራዊ በማድረግ ‹‹ከሃይማኖት፣ ከባህልና ከፖሊቲካ ተጽዕኖ የተላቀቁ መኾናቸውን የማረጋገጥ›› ግቦችን አስቀምጠው ነበር፡፡
የሴኩላሪዝም መርሖና የሴኔት ሕግ በሽፋንነት የሚጠቀስበት የጅማ ዩኒቨርስቲው የእነ አቶ እውነቱ ኃይሉና ኢንስፔክተር ካሊድ አባ ተማም አሠራር ግን ለወጉም ቢኾን ከፌዴራል መንግሥቱ መመሪያ ጋራ የተግባባ አይመስልም፡፡
አለመግባባት ብቻ ሳይኾን እንደ ጅማ ዩኒቨርስቲው ኹሉ ስማቸው ባልተጠቀሱ ሌሎችም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሓላፊነታቸውን ተገን በሚያደርጉ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያናችንና በኦርቶዶክሳውያን ላይ ጥቃቱና ጫናው በርብርብ መልክ የሚፈጸም አስመስሎታልና ‹‹ከፀረ አክራሪነት ትግሉ አኳያ›› ለዓመቱ በተያዘው ዕቅድና በተጣሉት ግቦች መሠረት ፈጻሚ አካላት ሓላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ክትትልና ድጋፉ የግድ ሊደረግ ይገባል፡፡mk gibi gubae students
በሌላ ገጹ ጉዳዩ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን በየሰበቡ አነሣስቶ ወደ ቀውስ በማስገባት በማኅበሩ ላይ ጠቅላላ ምት የማሳረፍ ፍላጎት እንዳለ ማሳበቁም አልቀረም፤ ማኅበሩ ግን አኹን በጅማ ማእከል የግቢ ጉባኤያት መዋቅሩ በኩል እንዳደረገው ሃይማኖታዊ መብታቸውን የሚጠይቁ የዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ አካልና የግቢ ጉባኤያቱ አባላት የኾኑ ተማሪዎችን በማረጋጋት ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ እየሠራ መኾኑ ነው የሚታወቀው፡፡
ማኅበሩ፡-
  • የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በግቢ ጉባኤያት አደራጅቶና በቂ ዝግጅት አድርጎ ትውልዱ ከሃይማኖቱ እንዳይናወጽ፣ ከሥርዓተ እምነቱ እንዳይወጣ፣ ታሪኩንና ባህሉን እንዳይዘነጋ የማስተማር፤
  • ባለንበት ዘመን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚካሔደውን የተቀናጀ የሃይማኖት ወረራ ለመከላከል ሃይማኖቱን የሚያውቅና የሚጠብቅ፣ ቤተ ክርስቲያኑን የሚከባከብና በቅንነት የሚያገለግል፣ ሀገሩን የሚወድ ግብረ ገብና ብቁ ዜጋ የማፍራት፤
  • በመንፈሳዊና በዘመኑ ትምህርት የበሰለው የኅብተረሰብ ክፍል በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሥር ኾኖ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲፈጽምና የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲያበረክት በሚያስችል ኹኔታ የማደራጀትና ለተልእኮ የማዘጋጀት ሓላፊነት ያለበት ነውና!!

No comments:

Post a Comment

wanted officials