የናይጀሪያ ፀረ ቦኮ ሀራም ትግል እና ጀርመን
ናይጀሪያን የጎበኙት የጀርመን የልማት ሚንስትር ጌርድ ሚውለር ባለፈው ሚያዝያ በሰሜናዊ ናይጀሪያ በቺቦክ መንደር በፅንፈኛው የሙ/ስሊም አክራሪ ቡድን የቦኮ ሀራም የታገቱትን ወደ 300 የሚጠጉ ልጃገረድ ተማሪዎችን
የናይጀሪያ መንግሥት ባስቸኳይ እንዲያስፈታ ለማሳሰብ የተቋቋመው « ልጆቻችን አስመልሱልን» በሚል መጠሪያ ከሚታወቀው የተቃውሞ ቡድን አባላት ጋ በመዲናይቱ አቡጃ ተገናኙ። ጀርመናዊው የልማት ትብብር ሚንስትር በሁለት ቀናት ጉብኝታቸው ማብቂያ ላይ ወደ 30 ከሚጠጉት « ልጆቻችን አስመልሱልን» የተባለው ቡድን የሚያካሂደው ተቃውሞ አደራጂዎች ጋ በተገናኙበት ጊዜ ቡድኑ የተነሳበትን ዓላማ እውን ለማድረግ ባሳየው ፅናት እና ይህ ዓላማቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ተከታይ እንዲያገኝ ባደረጉት ጥረት መደናቃቸውን ገልጸዋል።
« እኛ ከናንተ ጋ ቆመናል። በምትሰሩት ስራ በጣም ተደንቀናል። አሁን በጀመራችሁት ዘመቻ ፖለቲካውን ብቻ አይደለም ያንቀሳቀሳችሁት። የብዙዎችንም ልብ ነክታችኋል። ይሁንና፣ በዚህ ሁሉ መህል ዋናው ነገር ልጃገረዶቹ ባፋጣኝ በነፃ የሚለቀቁበት ድርጊት ነው። »
ይኸው የጌርድ ሚውለር የድጋፍ ቃል አበረታቺ መሆኑን ከ«ልጆቻችን አስመጡልን» ቡድን አባላት አንዷ የሆኑት የቀድሞ የትምህርት ሚንስትር ኦቢ ኤስኬዌስሊ አስታውቀዋል።
« ጀርመን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካል ናት። በአንድ ሀገር የሚከሰት ሽብርተኝነት ሌሎችንም ሀገራት የሚነካ ነው።በብዕና ላይ የሚፈፀም የሽብር ተግባር ሁሉንም ሊያሳስብ ይገባል። »
«ልጆቻችን አስመልሱልን» የተባለው ቡድን ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ለጀመረው ዘመቻ ትኩረት በሰጡት የጀርመን የልማት ትብብር ሚንስትር አንፃር የናይጀሪያ መንግሥት ቡድኑ ካለፉት ስማንት ሳምንታት ወዲህ እያካሄደው ያለውን ትግል እንደ ሸክም ነው የተመለከተው። እንዲያውም በአንድ ወቅት ተቃውሞ ብሎ አደባባይ መውጣት እስከመከልከል ደርሶ፣ የሀገሪቱ ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ለመበተን በኃይል ርምጃ ተጠቅሞዋል። የቀድሞ የትምህርት ሚንስትር ኦቢ ኤስኬዌስሊ የሀገራቸው መንግሥት ከቡድናቸው ጋ ያለው ግንኙነት ይህን መምሰሉ እጅግ ቅር እንዳሰኛቸው ገልጸዋል።
« እርግጥ፣ ከመንግሥት ጋ የሀሳብ ልውውጥ አድርገን ነበር። ግን ሽብርተኝነትን ለመታገል ይቻል ዘንድ በመንግሥት እና በሲቭሉ ማህበረሰብ መካከል መኖር የሚገባው ዓይነት ትብብር ላይ አልተደረሰም። »
ሽብርተኝነት እና ቦኮ ሀራም የተሰኘው ጉዳይ ግን ጀርመናዊው የልማት ትብብር ሚንስትር ከ« ልጆቻችንን አስመጡልን» ቡድን አባላት ጋ ብቻ ሳይሆን ከናይጀሪያ ርዕስ ብሔር ጉድላክ ጆናታንም ጋ የመከሩበት ዓቢይ ጉዳይ ነበር። በዚሁ ጊዜ ሚውለር ጀርመንን ልጃገረዶቹን በማስለቅ ጥረት ላይ ከናይጀሪያ መንግሥት ጋ እንደምትቆም ቢያመለክቱም በጦር ኃይሉ ደረጃ ድጋፍ እንደማትሰጥ ነበር ያስታወቁት።
« በጦሩ ርምጃ መፍትሔ ለማግኘት ለሚደረግ ጥረት የምንሰጠው ድጋፍ አይኖርም። ይሁንና፣ በወቅቱ በሀገሪቱ የተካረረው ውጥረት እና በሰበቡ የተፈጠረው ችግር መፍትሔ ሊገኝለት እንደሚገባ ለፕሬዚደንቱ ግልጽ አድርጌአለሁ። እንደሚታወቀው ባለፉት ጥቂት ቀናትም ሌሎች ሴቶች በቦኮ ሀራም ቡድን ታግተዋል። ይህ ናይጀሪያ መፍትሔ ልታስገኝለት የሚገባ መሠረታዊ ችግር ነው። »
ጀርመን ለናይጀሪያ ወደፊትም በተለይ በትምህርቱ እና በሙያ ሥልጠናው ዘርፍ መርዳቷን እንደምትቀጥል ሚውለር አስታውቀዋል።
« የናይጀሪያ መንግሥት በገጠሩ አካባቢ በያንዳንዱ ትምህርት ቤት ውስጥ አስቸኳይ ርምጃ በመውሰድ የፀጥታውን ጥበቃ ዋስትና ለማረጋገጥ እና ወጣት ሴቶች እና ወንዶች ካላንዳች ፍርሀት ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ የሚያስችለው «ሴቭ ስኩል» የተባለ አዲስ የርዳታ መዋጮ ይዘጋጃል። »
እዚህ ላይ የጀርመን ርዳታ በተጨባጭ ምን እንደሚመስል ግን ሚንስትሩ አላብራሩም። የናይጀሪያ የግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ ለዚሁ ፈንድ መጀመሪያ 10 ሚልዮን ዩኤስ ዶላር ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አመልክቶዋል፣ ሌላ 10 ሚልዮን ዶላር ደግሞ ከሌሎች ዘርፎች እንደሚዋጣ ተገልጾዋል።
የብሪታንያ መንግሥት ደግሞ ከዩኤስ አሜሪካ ጋ ባንድነት በመሆን የናይጀሪያ መንግሥት በቦኮ ሀራም አንፃር ለጀመረው ትግሉ ተጨማሪ ርዳታ እንደሚያቀርብ የብሪታንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዊልያም ሄግ ከጥቂት ቀናት በፊት በለንደን ገልጸዋል።
« በቦኮ ሀራም አንፃር የተጀመረው ትግል ይጠናከር ዘንድ ከናይጀሪያ መንግሥት ጋ ትብብራችንን ለማስፋፋት እናጠናክራለን። ይህ የብሪታንያ ርዳታ ሀገሪቱ ለናይጀሪያ የጦር ኃይል የምትሰጠውን የሥልጠና እና የታክቲክ ድጋፍ የምታስፋፋበትን፣ በቦኮ ሀራም አንፃር በሰሜናዊ ምሥራቅ ናይጀሪያ የተሠማሩትን የጦር ቡድናት የምታሠለጥንበትን፣ ላካባቢ ፀጥታ እና የስለላ መረጃ ተጨማሪ ርዳታ የምታቀርብበትን፣ እንዲሁም፣ ቦኮ ሀራም ልጃገረዶችን የትምህርት ዕድል ለመንፈግ የጀመረው ጥረቱ እንዳይሳካለት የምታከላክልበትንም ድጋፍ ያካትታል። እና ከዩኤስ አሜሪካ ጋ ባንድነት በመሆን ለትምህርቱ ዘርፍ የምናደርገውን ርዳታ እና በሰሜናዊ ናይጀሪያ ብዙ ወንዶች እና ሴቶች በትምህርቱ ገበታ የሚሳተፉበትን ዕድል እናስፋፋለን። »
የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን ከጥቂት ቀናት በፊት የመንግሥቱን በጀት ያጸደቁ ሲሆን፣ ከዚሁ በጀት ውስጥ ከየአምስቱ ናይራ (የሀገሪቱ ሸርፍ) መካከል አንዱ ወደመከላከያ ሚንስቴር ካዝና ይገባል፤ ያም ቢሆን ግን አንድም ሳንቲም የፅንፈኛው ሙሥሊም ቡድን ቦኮ ሀራም ዋነኛ የጥቃት ዒላማ የሆኑትን ትምህርት ቤቶችን ለመከላከሉ ተግባር አለመመደቡ የመንግሥቱን ግድ የለሽነት ያሳየ ነው በሚል ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ትግል የጀመሩት እና ሌሎች የመብት ተሟጋቾች ቡድናት ወቅሰዋል።
ካትሪን ጌንስለር/አርያም ተክሌ
ልደት አበበ
No comments:
Post a Comment