Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, June 8, 2014

አገራዊ ስሜት ለምን ይጎድለናል? ክፍል 2

አገራዊ ስሜት ለምን ይጎድለናል? ክፍል 2

http://tekluabate.blogspot.de/2014/06/2_7.html
በክፍል አንድ ጽሁፌ ብዙ ኢትዮጵያዊ በቂ የአገር ስሜት እንደሌለው ሞግቻለሁ:: አገራዊ ስሜት ማለትም አገራችንን በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮችን በነቃ አእምሮ ተከታትሎና መርምሮ የራስን ግንዛቤ መውሰድ ከዚያም የሚገባውን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሆነም ጠቁሜአለሁ:: በስብሰባዎችና የውይይት መድረኮች መሳተፍ: የፖለቲካ ወይም የሲቪል ተቋማትን መምራት ወይም አባል መሆን: የራሱና የሌላ ሰው መብት ሲጣስ መቃወም: እድገትና ለውጥ በሚያመጡ ፕሮጄክቶች መሳተፍ ወዘተ የአገራዊ ፖለቲካዊ ስሜት የሚገለጥባቸው መንገዶች እንደሆኑም ለምሳሌነት አንስቻለሁ:: ከዚያም አገራዊ ጉዳዮችን በአንክሮ እንዳንከታተልና በሚገባ እንዳንሳተፍ የሚያደርጉ መንስኤዎችንና ምክንያቶችን በዝርዝር ማንሳትና መወያየት ፖለቲካዊ ንቃተ ኅሊናን ለማሳደግ በሚደረግ ጥረት አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ አሳስቤአለሁ:: በዚህ ጽሁፍ ሁለት ለአገራዊ ስሜት በበቂ ሁኔታ አለመኖር ተጠቃሽ መንስኤዎችን ወይም ምክንያቶችን ለውይይት አቅርቤአለሁ::   

ባህላዊ አስተምህሮአችን 

ባህላችን የማንነታችንና ምንነታችን መገለጫ ነው:: ይሁን እንጅ ባህል ሁሌ ጠቃሚ እሴችን ብቻ ሊይዝ ሊያስተላልፍ አይችልም:: በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ጎጅ ትምህርቶች ልምዶችና ወጎች ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋሉ:: በመሪና በተመሪ መካከል ስላለው ግንኙነት ብንመለከት ብዙ ጎጅ የሆኑ አመለካከቶችን እናገኛለን:: 

ማንኛውም ዜጋ ለመሪው ወይም ለመንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መታዘዝና መገዛት እንዳለበት ለበርካታ መቶ ዓመታት ተሰብኳል:: መሪዎች ወይም መንግስታት ህግ ቢተላለፉ ማንም መጠየቅ እንደማይችል በአንድም በሌላም ዘዴ ተነግሯል:: ለዚህም "ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ" የሚለው አባባል ጥሩ ምሳሌ ነው:: እንዲያውም ህዝቡ ወይም ተመሪው ለመሪው ያለመታተክ የመገዛት ሃይማኖታዊና ተፈጥሮአዊ ግዴታ እንዳለበት ይነገረዋል:: መንግስት ጌታ ሲሆን ህዝብ ደግሞ ባሪያ ነው:: ባሪያ የሚፈቀድለት ነገር ቢኖር የጌታውን ደህንነት መጠበቅና የሚፈልገውን ማድረግ ነው:: ህግጋትና ሥርዓታት ሁሉ የተዘጋጁት ለባሪያው እንጅ ለጌታው አይደለም:: ጌታው ከህግ በላይ ነው:: ጌታው የህዝቡን ንብረት የመውሰድ መብት አለው:: ፖሊሱ ሚሊሻው የደህንነት ሠራተኛው ወታደሩ አልፎ አልፎ የውጭ ጠላት ካልመጣ በስተቀር በዋናነት የሚያገለግለው ጌታውን ነው:: ይህንን ያልተጻፈ ህግ ከወላጆቻችን እየሰማን በአይናችንም እያየን አድገናል:: አውቀንም ሳናውቅም ህጉን እንፈጽማለን:: አንድ መንግስት የፈለገውን ያህል ጨቋኝ ቢሆን የእኛ መልስ ጸጥታ ነው:: መንግስቱ ለ17 ዓመታት እንደ ሰም አቅልጦ ሲገዛን ምላሻችን ዝምታ ነበር.: የአሁኑ መንግስትም ራሱ ያወጣውን ህግና መመሪያ ለእኛ ባሪያዎቹ ጥሎ እርሱ ከህግ በላይ ከሆነ ሁለት ዓስርት ዓመታት አለፉ:: ጥረን ተጣጥረን ያደረግነው ቢኖር በጣት የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፎችን ማድረግ ብቻ ነው:: አብዛኛው ሰው በጸጥታ ባሪያነቱን ተቀብሎ  እንደሚኖር ለማሳየት ነው እንጅ የተወሰኑት ቆራጦች ዕለት ከዕለት ያደረጉትን ትግል እረስቼ ግን አይደለም:: 
   
ለዚህ ጎጅ ባህል መዳበር በግንባር ቀደምትነት የሃይማኖት ተቋማትን ተገን ያደረጉ ልሂቃን ተጠቃሽ ናቸው:: በክርስትናውም በእስልምናውም ሃይማኖቶች ይህ ጉዳይ አለ:: የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላት ለመከላከል በተደረጉ መራራ ትግሎች ወሳኝ ሚና ተጫውታለች:: ኢትዮጵያዊ ወኔ እንዲዳብርም ሁሌ ትሰብካለች:: ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጨቋኝ መንግስታትና መሪዎች ህግን እንዲያከብሩና ህዝቡን በማስተዋል እንዲመሩ ግን ያደረገችው አስተዋጽዖ የጎላ አይደለም:: እንዲያውም አንዳንድ መምህራን ወቅቱ ላመጣው የመንግስት ሥርዓት ሁሉ ህዝቡ በአንክሮ መገዛት እንዳለባቸው  ያስተምራሉ:: በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አማኙ ስለኢትዮጵያ ሳይሆን ስለሳውዲ ዓረቢያ እንዲያስብና እንዲብከነከን ያስተምራሉ:: ከፕሮቴስታንት አስተማሪዎች የሚሰማው ደግሞ  ስለጌታ አዳኝነት ብቻ እንጅ ስለኢትዮጵያ ህዝብና ችግሩ አይደለም:: 

በአጠቃላይ ሲታይ ህዝቡ በየጊዜው በለስ ለሚቀናቸው መንግስታት እና መሪዎች ያለምንም ጥያቄ እንዲታዘዝ ተነግሮታል:: የፖለቲካ መሪዎች በህዝቡ ላይ በደልና ግፍ ሲፈጽሙ የትኛውም የሃይማኖት ተቋም ተቃውሞ አያነሳም:: ህግና  እውነት እንዲጠበቅ ከመስበክ ይልቅ ህዝቡ መሪዎችን አፍሮና ፈርቶ እንዲኖር ይነገረዋል:: እንዲያውም ከበዳይ መሪዎች ጎን በመቆም ህዝባቸውን የሚያሳዝኑም የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች አሉ:: አሁንማ  ይባስ ብሎ ጨቋኝ የሃይማኖት መሪዎችንም እያየን ነው:: ይህ ጎጅ ባህል ለዘመናት እየተንከባለለ 21ኛው ክፍለ ዘመን ደርሷል:: ብዙ ሰው በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዳያደርግ በተለያዩ መንገዶች አሉታዊ ተጽእኖ እያደረገ ይገኛል:: ይህን ስል ግን የተጠቀሱት የሃማኖት ተቋማት ጭቆናን በአቋም ደረጃ ይደግፋሉ ማለቴ አይደለም:: እነሱን ተገን ያደረጉ አስተማሪዎችንና መሪዎች የሚሰሩት ሥራ እንደሆነ ግን  ይሰመርበት::        
             

ፍርሃትና ስጋት

የኢትዮጵያን ህዝብ ጀግንነት መላው ዓለም ጠንቅቆ ያውቀዋል:: የዓረብና የአውሮፓ ወራሪዎችን ቅስም ሰብሮ አባሯል:: ኢትዮጵያ በማንም አገር ቅኝ እንዳትገዛ አድርገዋል:: ይህ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ከሚያስችሉን ታሪኮቻችን ውስጥ ትልቁ ነው:: ወደፊትም ይህን አይበገሬነታችንን ይዘን እንደምንቀጥል ተስፋዬ ነው::  

ነገር ግን የህዝቡ ጀግንነት ጎልቶ የሚታየው ከውጭ ወራሪ ኃይሎች ጋር በሚደረገው ግብግብ ብቻ ይመስላል:: ከባእዳን ያልተናነሱ ግን በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጨቋኝ መሪዎቻቸውን ግን የሚፋለሙበት ወኔ የሚያንሳቸው ይመስላል:: ለዘመናት በነጻነት ኖረናል ይባላል እንጅ ለአፍታም ቢሆን እያንዳንዱ ዜጋ መብቱና ጥቅሙ ተከብሮለት ኖሮ አያውቅም:: ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ህዝቡ ለመንግስታቱ ያለው ፍርሃት ግን ዋናው ነው:: ውስጥ ለውስጥ በጥንቃቄ ከሚነገር ሃሜት አልፎ ጨቋኝ መሪዎችን በይፋ የሚያወግዝበትና የሚጠይቅበት ድፍረት ያጣ ይመስላል:: በአገር ቤትም ይሁን በውጭው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ድፍረትና ግልጽነት ባለው መልኩ አገሪቱ ያለችበትን አሳሳቢና አሳፋሪ ሁኔታ መናገር ሲያሸማቅቃቸው ይታያል:: ለምን ያለውን የመብት መጣስና ቅጥ ያጣ ድህነት መናገር እንደማይፈልጉ  ሲጠየቁ የብዙዎች መልስ "እባክህ ልኑርበት" ሆኗል:: በስብሰባዎችና በውይይቶች መሳተፍ ባድሜና ዛላንበሳ እንደመዝመት አስፈሪ እየሆነ ነው:: ብዙዎች በፍቅርና በተመስጦ የሚወያዩባቸው ጉዳዮች ስፖርትና ሙዚቃ እንዱሁም አገር ቤት ህንጻ ስለመገንባት ሆነዋል:: 

ብዙዎች ፍርሃታቸው መጠን ከማጣቱ የተነሳ የራሳቸው መብትና ጥቅም ሲነካ እንኳን አይቃወሙም:: ስለህዝባቸው መቸገርና መጨቆን የሚታገሉትን ሳይቀር ፈርተው ለማስፈራት ይጥራሉ:: ተቆርቋሪ ወገን በመሆን ለመብት የሚታገሉትን ያስጠነቅቃሉ:: "አገር ቤት የጀመርከውን ቤት ሰርተህ ብትጨርስና በሰላም ብትኖርበት ይሻልሃል" የሚል ምክር ጣል ያደርጋሉ:: መንግስት ያለውን የካድሬ ብዛትና የስለላ መረብ  እንዲሁም እየሰጠ ያለውን ጽኑ ቅጣት ለማስፈራሪያነት ያነሳሉ:: በአንድ ወቅት አርቲስት ታማኝ በየነ እንዳለው ሌሎች ለሚጽፉትና ለሚናገሩት የሚያነቡትና  የሚሰሙት እየፈሩ ነው:: አንድ በስድሳዎቹ የእድሜ ክልል ያሉ አባት ይህን ቅጥ ያጣ ፍርሃት በተመለከተ ያጫወቱኝን ላካፍልና የዛሬውን ጽሁፌን ላጠቃልል:: 

በፈታኙ የደርግ ጊዜ ነው:: እኒህ የሃይማኖት ሊቅ የሆኑ አባት ኢሰፓዎችን ሳይፈሩ በህዝብ ፊት ይገስጹ ነበር:: አገዛዛቸውን አጥብቀው ይቃወሙ ነበር:: በዚህም የተነሳ አብዮታዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ተወስኖም ነበር:: ይህን ሁኔታ የሚያውቁ ሌላ የሃይማኖት አባት በአንድ ወቅት እኒህን አባት አዲስ አበባ መንገድ ላይ ያገኟቸዋል:: ሰላምታ ከተለዋወጡና ጥቂት ከተነጋገሩ በኋላ "ይህን ድፍረትዎን አልወደድኩልዎትም ይጠንቀቁ" ይሏቸዋል:: እኒህ ሊቅ አባትም "እኔ ደግሞ የእርስዎ ፍርሃት ያስጠላኛል" ብለዋቸው ተለያዩ:: እስካሁን ድረስ እኒህ ጀግና አባት ለእውነት ሲታገሉ አሉ:: ስንቶቻችን ፈርተን ስንቶችን አስፈርተን ይሆን? ስንቶቻችንስ በፈሪዎች ምክር መሳይ ንግግር ተደናግጠን ሩጫችንን  አቁመን ይሆን? 

///////////////// ይቀጥላል ////////////////      

No comments:

Post a Comment

wanted officials