እውነት ነው! ስርዓቱ ፍርስርስ ይበል!
ዛሬ በጠዋቱ ነው ወደ አራዳ ችሎት ያቀናሁት፡፡ ሁለት ሰአት ተኩል ላይ ስደርስ ያገኘሁት 3 ሰዎችን ብቻ ነው፡፡ ችሎቱ ሌላ ቦታም የተደረገ መሰለኝ፡፡ እየቆዩ ግን ሰዎች ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ፈረንጆቹ ሳይቀር ችሎቱ ከተባለለት ሰዓት አርፍዶ እንደሚጀመር በሚገባ ተገንዝበውታል፡፡ ቢያንስ ለ2 ሰዓት ያህል ቆመን ጠበቅን፡፡ ያው ይህም ህዝብን የማሰላቻ አንድ ስልት መሆኑ ነው!
ጦማሪያኑ ሲመጡ ማንም ስልክ እንዳያወጣ ተከለከለ፡፡ ሁሉም ነገር ትዕዛዝ ነው፡፡ እነዛን ሰላማዊ ወጣቶች በካቴና ታስረው ላያቸው ልብ ይነካል፡፡ የተቻላቸውን ያህል ፈገግ ለማለት እየሞከሩ የታሰረውን እጃቸውን ወደላይ አንስተው ሰላምታ ሰጡን፡፡ በዛ ሰላማዊነታቸው ላይ እየገጠማቸው ያለውን አንዳች መከራ በግልጽ ይታያል፡፡ የበፍቃዱ እህት ‹‹ወንድሜ ውድድ ነው የማደርግህ!›› ስትለው እሱም ስቃይ ውስጥ ባለ ፈገግታው ምላሽ ሲሰጥ አንጀት ይበላሉ፡፡ ማህሌት አቀርቅራ ስታልፍ ደግሞ በእጅጉ ያስብሳል!
በጣም የሚገርመው ግን ችሎቱ ሲያበቃ የተደረገው ነገር ነው፡፡ ከችሎቱ ግቢ እንድንወጣ ታዘዝን፡፡ ፖሊስ መዝለፍና መገፍተሩን ተያያዘው፡፡ በተለይ አንዲት ሴት ፖሊስ የበፍቄን እህት መሳደብ ጀመረች፡፡
ከግቢ ከወጣን በኋላ ሰው ‹‹ከዚህ ወዲያ የት ነው የምንሄደው?›› ብሎ ማንገራገር ሲጀምር መገፍተሩና ስድቡ ተባብሶ ቀጠለ፡፡ ጋዜጠኛ በላይ ማናየ ጥያቄ ስለጠየቀ ብቻ በፖለሲ ተያዘ፡፡ ያች ባለጌ ፖሊስ አሁን በበፍቄ እህት ላይ የብልግና ስድቧን ማውረድ ጀመረች፡፡ ይህ አልበቃት ብሎም እደባደባለሁ ብላ ተገለገለች፡፡
ይህን አረመኔነት ከልጃቸው ጎን ሆነው ያዩት የበፍቄ እናት ጮህ ብለው ‹‹አንተ መድሃኒያለም አለህ?›› እያሉ ስለ ስርዓቱ ብልሹነት አነቡ፡፡ የበፍቄን እናት ያዩትም ሆነ የስርዓቱ ቅጥ ያጣ ብልሹነት ያማረራቸው በርካታ ወጣቶች ሲያለቅሱ አስተውያለሁ፡፡
በስተመጨረሻም እነዛ ሰላማዊ ወጣቶች እንደተለመደው በሽብር መከሰሳቸውን ሰማን፣ 28 ቀናትም በዛ መጥፎ ቤት እንዲቆዩ የግድ ሊሆን ነው፡፡ ይህን ብልሹ የህግም ሆነ የፖለቲካ ስርዓት ማንም መሸከም እንደማይችል የበፍቄ እናት እንባ ምስክር ነው፡፡ እነዛ ሰላማዊ ግን ደግሞ ያለ አግባብ በካቴና የታሰሩት ወጣቶች ደግሞ ዋነኛዎቹ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እናም ይህ ለኢትዮጵያውያን የማይጠቅምና ዘመኑ የማይሸከመው ስርዓት ተመስገን ደሳለኝ እንደሚለው መፍረስ አለበት፡፡ መፍረስብ ብቻ ሳይሆን በማይጠገን መልኩ ፍርስርስ ማለት አለበት፡፡
Getachew Shiferaw
No comments:
Post a Comment