ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ” ለአንድነታችን በጽናት እንቆማለን” የሚሉ መፈክሮችን በማሰማት የረመዳንን ጾም ጀመሩ
ሰኔ ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ የሰላማዊ ተቃውሞ ታሪክ ውስጥ ረጅም ጊዜ በማስቆጠር ክብረወሰን የሰበረው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ፣ በረመዳን ጾም መግቢያም ” በአንድነታችን እንጸናለን” በሚል መፈክር ተካሂዷል።
እንደወትሮው ሁሉ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በአንዋር መስጊድ በተካሄደው የጸሎት ስነስርአት፣ ሙስሊሙ “በአንድነታችን እንጸናለን” የሚሉ በወረቀት ላይ የተጻፉ መፈክሮችን ከፍ አድርጎ በማሳየትና እጅ ለእጅ በመያያዝ መልእከቱን አስተላልፏል። ዝግጅቱ ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የድምጻችን ይሰማ የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት የፍርድ ሂደት እንደቀጠለ ሲሆን ፣ ኢትዮጵያውያኑ ” የሃይማኖት ነጻነታችን ይከበር” የሚል ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ እጅግ አሰቃቂ እንግልትና በቃላት ሊገለጹ የማይችሉ ግፎች በወንዶችና በሴት እሰረኞች ላይ መፈጸማቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች በማህበራዊ ድረገጾች እየተለቀቁ ነው።
የኮሚቴ አባላቱ የሚያሳዩት ጽናት በርካታ ሙስሊሞች በጽናት እንዲቆሙ እንዳደረጋቸው ታዛቢዎች ይናገራሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች መሪዎቻቸውን ለማየትና ለማበረታታት የፍርድ ቤት ቀጠሮች በሚኖሩበት ጊዜ እየተገኙ ድጋፋቸውን ይገልጻሉ።
በሙስሊሙ ትግል መፍትሄ ያጣ የሚመስለው መንግስት፣ ሙስሊሙ መሪዎቹ ሲታሰሩበት ትግሉን ያቆማል ብሎ መሪዎቹን ቢያስርም፣ ተቃውሞው ግን ሊቆም አልቻለም። ታዛቢዎች እንደሚሉት መንግስት መሪዎቹን ከእስር ካልፈታ፣ በሙስሊሙ ህዝብ ላይ ለፈጸመው በደል ይቅርታ ካልጠየቀና ጥያቄዎቻቸውን በአስቸኳይ ካልመለሰ፣ ተቃውሞው መቀጠሉ አይቀሬ ነው።
No comments:
Post a Comment