የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት መጓተት ጥያቄ እያስነሳ ነው
የአገሪቱን የሞባይል ኔትወርክ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ሲባል ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች ዜድቲኢና ሁዋዌ ከዓመት በፊት የተረከቡት የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት መጓተት ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡
ከቻይና ኤግዚም ባንክ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው 1.6 ቢሊዮን ዶላር ባለመለቀቁ፣ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ላለመጀመሩ ምክንያት መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ያስረዳሉ፡፡
የአዲስ አበባው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተጀምሮ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ለውጥ እየታየ መሆኑ ቢነገርም፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ይጀመራል የተባለው የማስፋፊያ ሥራ መዘግየቱ አሳሳቢ ነው ተብሏል፡፡
ዜድቲኢና ሁዋዌ የተባሉት የቻይና የቴሌኮም ኩባንያዎች ፕሮጀክቱን እኩል ተካፍለው አገር አቀፉን ፕሮጀክት ያስጀምራሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ ከአዲስ አበባው ፕሮጀክት በስተቀር በክልሎች ምንም የሚታይ እንቅስቃሴ አለመኖሩ ለጥያቄው መነሳት ምክንያት ሆኗል፡፡
ሁዋዌ በአዲስ አበባ የማስፋፊያ ፕሮጀክትን በመጀመር በተለያዩ አካባቢዎች የመቀበያ አንቴናዎችን እየተከለ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ከፍተኛ የኔትወርክ ችግር የነበረባቸው ቦታዎች መፍትሔ እያገኙ ናቸው ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹4G›› የተሰኘውን የፕሮጀክት አካልም ተረክቧል፡፡ በአገር አቀፉ ፕሮጀክትም የሚሳተፍባቸው ቦታዎች አሉ፡፡
ዜድቲኢ በክልል ደረጃ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ላይ የሚሳተፍ ቢሆንም ሥራ አለመጀመሩ ታውቋል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ሠራተኞችን እየቀነሰና ባለሙያዎችንም ከአገር እያስወጣ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበለት ዜድቲኢ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ፕሮጀክቶች እንዳሉት ገልጾ፣ የሠራተኞች ቁጥር በመካሄድ ላይ እንዳሉ ፕሮጀክቶች ሁኔታ ይለዋወጣል ብሏል፡፡ ስለዚህ ሥራ ሲኖር የሠራተኞች ቁጥር ይጨምራል፡፡ ሳይኖር ደግሞ ይቀንሳል ብሏል፡፡ ከአንድ ፕሮጀክት ወደ ሌላ ፕሮጀክት ማዛወርም የተለመደ መሆኑን ገልጿል፡፡
የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክቱን በተመለከተ ባለፈው ዓመት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ኮንትራት መፈራረሙን አስታውሶ፣ በኮንትራቱ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ድርድር ከተደረገ በኋላ በአብዛኛው ስምምነት መደረሱን አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ በፊት መታየት ያለባቸው የተወሰኑ ጉዳዮች መቅረታቸውንም አክሏል፡፡ የቀሩት ጉዳዮች ምን እንደሆኑ ግን መግለጽ አልፈለገም፡፡
አገር አቀፍ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን በቅርቡ በመጀመር በፍጥነት ለማጠናቀቅ በማሰብ የኮንትራት ሥራ የሚሰጣቸውን ድርጅቶች እንዲዘጋጁ ማስታወቁን አስረድቶ፣ ለፕሮጀክቱ የሚያገለግሉ ግብዓቶችን በማዘጋጀት ላይ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ይሁንና መንግሥት ለአዲስ አበባ የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት ቅድሚያ በመስጠቱ የከተማው ማስፋፊያ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን፣ ነገር ግን የክልል ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት አለመጀመራቸውን አስረድቷል፡፡
ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበለት ዜድቲኢ፣ ለቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የሚሆን የገንዘብ ችግር የለብኝም ብሏል፡፡ ምንም እንኳ ለፕሮጀክቱ የሚውለው የገንዘብ አቅርቦት ሁኔታ ጥሩ ባይሆንም፣ ቢያንስ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የሚደረገው ቀሪ ድርድር ሲጠናቀቅ ገንዘቡ እንደሚገኝ ግን ተስፋ እንዳለ አስታውቋል፡፡
ዜድቲኢ በሌላ በኩል ያቀረበው ቅሬታ ከዚህ ቀደም ላከናወነው የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት ያልተከፈለው ገንዘብ መኖሩን ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ታሪካዊ ነው ለሚባለው የመጀመሪያው ፕሮጀክት ያወጣው ከፍተኛ ወጪ ባለመክፈሉ፣ ዜድቲኢ ለአዲሱ ፕሮጀክት ሊኖረው የሚገባውን ከፍተኛ መነሳሳት እንደጎዳበት ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ያልተከፈለው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡
የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ግን ፕሮጀክቱ አልተጀመረም መባሉን አይቀበልም፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱራሂም አህመድ፣ በአሁኑ ጊዜ የፕሮጀክቱ የቅድመ ትግበራ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ይላሉ፡፡ የቅድመ ትግበራ ሥራዎች የሚባሉት ፕላን፣ ቅየሳ፣ እንዲሁም አስፈላጊ የሚባሉ ተግባራትን እንደሚያካትቱ ገልጸው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ አገሪቱን በ13 ክበቦች (Circles) በመከፋፈል ተግባራዊ መደረግ በተጀመረው እንቅስቃሴ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ መሠረት ይጀመራል ብለዋል፡፡
‹‹ለፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ የሚሆን አማካሪ ጅርጅት ለመምረጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቷል፡፡ አማካሪ ድርጅቱን ለመቅጠር ቴክኒካዊ ግምገማው አልቋል፡፡ ቢበዛ በሁለት ሳምንት ውስጥ ይታወቃል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች ማለትም ሁዋዌና ዜድቲኢ በኮንትራት ስምምነቱ መሠረት አገር አቀፉን ፕሮጀክት በቅርቡ ይጀምራሉ፤›› ያሉት አቶ አብዱራሂም፣ ፕሮጀክቱ ተጓቷል ተብሎ የሚነሳው ጥያቄ መሠረተ ቢስ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
መንግሥት የቴሌኮም ማስፋፊያው ፕሮጀክት በስድስት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ብሎ ቃል መግባቱ እየታወቀ ፕሮጀክቱ አልተጓተተም የሚሉት በምን መነሻ ነው በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ባህሪ በተመለከተ የአረዳድ ችግር አለ ብለዋል፡፡
‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ ፕሮጀክቱ የሚጠናቀቀው በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ማለትም በ2007 ዓ.ም. መጠናቀቂያ ላይ ነው፡፡ በዚያ ወቅት በአሁኑ ጊዜ ያለውን 23 ሚሊዮን የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 59 ሚሊዮን ለማድረስ ነው ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ሁዋዌ በተባለው ኩባንያ የተጀመረው የሞባይል ማስፋፊያ ፕሮጀክት በሦስት ምዕራፎች እየተከናወነ ነው፡፡ ሁለቱ ምዕራፎች ተጠናቀው አንዱ ምዕራፍ ይቀራል፡፡ በሰኔ ወር መጨረሻ መንግሥት በገባው ቃል መሠረት የአዲስ አበባ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ለማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የሚውለውን 1.6 ቢሊዮን ዶላር አለመለቀቅንና ምክንያቱ ምን እንደሆነ በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከሁለቱም ኩባንያዎች ጋር ውል መፈራረሙንና በዚህም መሠረት ሥራው እንደሚቀጥል ያውቃል ብለው፣ ከዚህ ውጪ ገንዘቡ አልተለቀቀም ስለሚባለው ጉዳይ እሳቸውም ሆኑ መሥሪያ ቤታቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡ ይህንን በተመለከተ ከየትኛውም ኩባንያ የቀረበ አቤቱታ የለም ብለዋል፡፡
‹‹ይህንን ፕሮጀክት በተመለከተ ኮንትራት ተፈርሟል፡፡ ኮንትራቱ ገዥ ነው፡፡ ኩባንያዎቹ በውላቸው መሠረት ገንዘብ አምጥተው ነው የሚሠሩት፡፡ ኢትዮ ቴሌኮምም ይህንን ነው የሚያውቀው፡፡ ከዚህ ውጪ ገንዘብ የለም የሚባለው ጉዳይ ፈጽሞ የማያስኬድ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በላይ መናገር እንደማይቻልም አስረድተዋል፡፡
ዜድቲኢ አልተከፈለኝም ያለውን ከፍተኛ ዕዳ በተመለከተም የበፊቱንና የአሁኑን ፕሮጀክት ምንም የሚያገናኛቸው ጉዳይ እንደሌለ፣ ጉዳዩ ቢነሳ እንኳ በቀድሞው ፕሮጀክት በዜድቲኢ በኩል ላልተፈጸሙ ሥራዎች ኢትዮ ቴሌኮም የሚቀረው ነገር ስላለ ለጊዜው ዝርዝር ውስጥ መግባት አስፈላጊ አይደለም በማለት አስረድተዋል፡፡
የአገር አቀፉን ፕሮጀክት መጓተት አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበለት ሁዋዌ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ፕሮጀክት ላይ በመጠመዱ ምክንያት፣ ለቀረበለት ጥያቄ ለጊዜው ምላሽ እንደሌለው አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ለኩባንያው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ሁዋዌ የአዲስ አበባ ፕሮጀክትን በማከናወን ላይ ያለው በራሱ ገንዘብ ነው ይላሉ፡፡ የቻይናው ኤግዚም ባንክ 1.6 ቢሊዮን ዶላሩን ባለመልቀቁ ምክንያት ሁዋዌ ፕሮጀክቱን ከራሱ ገንዘብ ለመደጎም መገደዱንም ያስረዳሉ፡፡
የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ተጀምሮ በመገባደድ ላይ መሆኑ ቢነገርም፣ መላ አገሪቱን የሚያካልለው ትልቁ ፕሮጀክት ባለመጀመሩ ምክንያት ተቃራኒ አቋሞች ይደመጣሉ፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የቅድመ ትግበራ ሥራዎች ሲጠናቀቁ ሥራው ይጀመራል ሲል፣ ለፕሮጀክቱ ቃል የተገባው ገንዘብ አለመለቀቁና በውሉ መሠረት ሥራ ለመጀመር የሚያስችሉ አንዳንድ ድርድሮች አለመጠናቀቃቸው፣ ለጥያቄዎቹ መነሻ ምክንያት መሆናቸው ግን በሁለቱም የቴሌኮም ኩባንያዎች ውስጥ ጎልቶ ይሰማል፡፡ የቻይናው ኤግዚም ባንክ ተፈላጊውን ገንዘብ ስለመልቀቁና አለመልቀቁ ኢትዮ ቴሌኮም ማወቅ አለበት የሚሉም አሉ፡፡ ለሁለቱ ኩባንያዎች የሚሰጡት የፕሮጀክት ሳይቶች ጉዳይም ለፕሮጀክቱ በጊዜ አለመጀመር ምክንያት መሆኑን የሚጠቅሱ ምንጮች፣ ኢትዮ ቴሌኮም ፕሮጀክቱን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ መስጠት አለበት ይላሉ፡፡ በሁለቱ ኩባንያዎች ላይም ጠንከርና ጠበቅ ያለ ቁጥጥር መደረግ አለበት በማለት ያሳስባሉ፡፡ Reporter Amharic
No comments:
Post a Comment