Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, November 13, 2014

ጥንታዊ፣ ጥናታዊና ታሪካዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑ መጽሃፍትና ጋዜጦች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መጽሃፍት በኪሎ 20 ብር ተቸበቸቡ

የአጼ ቴዎድሮስ፤ የአጼ ሚኒሊክ፤ የአጼ ዮሐንስ ደብዳቤዎችን ጨምሮ ሁለት ሺህ ኪሎ የሚመዝኑ ታሪካዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑ መጽሃፍትና ጋዜጦች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መጽሃፍት በኪሎ 20 ብር ተቸበቸቡ።
በሃገር ውስጥ እንዲኖሩ የማድረግ ፍላጎት ያላቸው–በተቻለ ለኢትጵያዊያን ብቻ መጽሃፍ የሚሸጡ ነጋዴዎች በሽያጩ እንዳይሳተፉ ሲታገዱ፤ ከውጭ ሃገር ገዢዎች ጋር ግንኙነት ያላቸውና ጥቅሙን የሚያውቁ አትራፊዎች ግን በሚስጥር ተጋብዘው በርካሹ ገዙት።
የዮብ ሉዶልፍ፤ ጀምስ ብሩስ፤ ሮሲኒ፤ ሂስትሪ ኦፍ አቢሲኒያ፤ የፋሽስት ወረራ ጊዜ በወራሪው ሃይል ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦች እንዳሉ፤ የቄሳር መንግሥትና የሮማ ብርሃን የተባሉት ጋዜጦች እና ሌሎችም የማይገኙና አሁን ቢገኙ ደግሞ ዋጋቸው በእጅጉ የናረ የሆኑ ውድ የሃገር ሃብት ጊዜ ያለፈባቸው፤ ጥቅም የሌላቸው፤ ያረጁ፤ ቦታ ያጣበቡ፤ በሚሉና በሌሎችም ሰበብ እንደ ስኳር መጥቅለያ ተራ ወረቀት በኪሎ ተቸበቸቡ።
ሚስጥራዊ ግን ንግዳዊ መሳይ የኢትዮጵያ ታሪክ ለተተኪው ትውልድ ሊተላለፍ የሚቻልበትን መንገድና ማስረጃ ሁሉ ድምጥማጡን ማጥፋት ቀደም ብሎ የታቀደ መሆኑ ሲሰማ ነበር። አሁንማ ሚስጥርነቱም ሳያስፈልግ፤ ምን ይሉናልም ገደል ገብቶ፤ “ላይጠቅሙ ቦታ ይዘው አዳዲስ መጻሕፍት ቦታ አጡ” (አዳዲስ የሚባሉትም ከ1983 ወዲህ በገዢዎቻችን አባላትና ስለጀግንነታቸው፤ ኢትዮጵያ ትላንት የተፈጠረች ሃገር የሚሉ አይነቶቹ ናቸው) በሚል አጉል ሰበብ እየተመረጡና የኢትዮጵያን ምንነት፤ ማንነት፤ ቀደምት ኢትዮጵያዊያን የፈጸሙት መልካም ምግባርና የኢትዮጵያዊነታቸው መገለጫ የሰፈረበት በውጭ ሰዎች የተጻፉት ዘመን ያስቆጠሩት የታሪክ መዛግብት በኪሎ ከስኳርና ጨው ባነሰ ዋጋ መሸጡ ያሳዝናል።
እነዚህ ጥንታዊ፣ ጥናታዊ፣ አብዛኛው በአይን ምስክር ላይ ተመስርተውና ምርምር ተካሂዶባቸው ጉልበት ጊዜ መዋዕለ ንዋይ ፈሶባቸው በምሁራን የተጻፉ፤ ሃገራችንን ጎብኝተው፤ ከማሕበረሰቡ ጋር ተግባብተውና ባሕልና ልምዱን ቀስመው፤ ልምዱን ተላምደው ለታሪክና ለትውልድም እንዲተላለፍ በማለት በዚያ መጓጓዣ እንደአሁኑ አልጋ ባልጋ ባልሆነበት ዘመን፤ ሽያጭ ያዋጣል አያዋጣም የሚለው ጥያቄ ባልታወቀበትና፤ ተጉዘው ያዩትንና የተረዱትን ላላዩትና እድሉ ላልገጠማቸው ሁሉ እንዲሆን ብለው ጽፈው ለሕትመት ያበቋቸው የሃገራችን ታሪካዊ ሰነዶች በኛው በዜጎቻችንን እንዲጠፉና እንዳይነበቡ ከቤተመዘክራችን ወጥተው አንዱን በ16ኛው ክፍል ዘመን የተጻፈውን መጽሐፍ ከአንድ ኪሎ ሽንኩርት ባነሰ ዋጋ በኛ ዘመን መሸጡ ያሳፍራል፤ ያናድዳል፤ ያሰቆጫል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials