Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, November 15, 2014

አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እየተባባሰ ነው አለ

ሲፒጄ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እየተባባሰ ነው አለ
በወቅታዊ የመብት ጥሰቶች ዙሪያ የሰራውን ጥናት ይፋ አድርጓል
መቀመጫውን በኒውዮርክ ያደረገው አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈጽማቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሄዱን አስታወቀ፡፡ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ቢሆንም የአገሪቱ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈጽማቸው ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ግን እየተባባሱ ቀጥለዋል ያለው ሲፒጄ፣ ይፈጸማሉ ባላቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዙሪያ የሰራውን ጥናት በትላንትናው ዕለት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ያወጣቸውን ህጎች ከቅርብ አመታት ወዲህ ዜጎችን በሚጨቁን መልኩ ያለአግባብ እየተጠቀመበት ነው ያለው ሲፒጄ፤ መንግሥት በሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች፣ በፕሬስ ነጻነትና በዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጥሰት እየፈጸመ ነው በሏል፡፡
በጸረ-ሽብርተኝነት ህግ ሽፋን ለእስር የሚዳረጉ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ቁጥር እያደገ ነው፤ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር እንዳይችሉ ተደርገዋል ሲል ኮንኗል - ሲፒጄ፡፡
“ቶም ላንቶስ ሂውማን ራይትስ ኮሚሽን” የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት በትናንትናው ዕለት በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በሚገኘው ሬይበርን ሃውስ አዳራሽ ባዘጋጀው የመወያያ መድረክ፣ በአገሪቱ ይፈፀማሉ የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን የሚዳስስ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሱኢ ቫለንታይን የተሰራው ጥናት፤ በኢትዮጵያ መንግስት ይፈፀማሉ የተባሉ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖችን እንቅስቃሴ የመገደብ፣ መገናኛ ብዙሃንን የመጨቆንና በልማት ፕሮጀክቶች ሰበብ የነዋሪዎችን ሰብዓዊ መብት የመጣስ ድርጊቶች ያብራራል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ በየዓመቱ የ800ሚ. ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጥ የጠቆመው ሲፒጂኤ፤ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት በመጠቀም ድጋፉ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይውልና መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብር ተፅእኖ ማድረግ በምትችልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ገልጿል፡፡
በውይይት መድረኩ የፓርላማ አባላት፣ የተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ተወካዮች፣ ተመራማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደተሳተፉበት ሲፒጂ ጠቁሟል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials