ባለፈው አርብህዳር 12፣ 2007 ዓም የሃረሪ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ሙራድ አብዱላሂ በሀረሪ ሊግ ዋና ጸሃፊና በንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃለፊ አቶ ነቢል መሃዲ ጽ/ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ተደብድበዋል። የክልሉ ባለስልጣናት ለሁለት መከፈላቸው የጸጥታ ስጋት መደቀኑንም ምንጮች ተናግረዋል።
በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው አቶ ነቢል ሙሃመድ ከወራት በፊት በተደረገ ግምገማ ከሀረሪ ሊግ ዋና ጸሃፊ እንዲነሱ ከተደረጉ በሁዋላ፣ ዘግይቶ ደግሞ ከንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ሃላፊነታቸው ተነስተው በክልሉ እቃ ግዢ ውስጥ በሃላፊነት እንዲሰሩ በፕሬዚዳንቱ ታዘዋል። ፕሬዚዳንቱ ተቀናቃኞቻቸውን በሰበብ አስባቡ እያስወገዱና ስልጣኑን በዘመዶቻቸው እያስያዙ ነው ብለው የሚያምኑ ሌሎች የፓርቲው አመራሮች ፕሬዚዳንቱን ሲቃወሙና ፕሬዚዳንቱ ሰሩዋቸው የሚሉዋቸውን ስራዎች ለአደባባይ እያበቁ ነው። የፕሬዚዳንቱ ባለቤት በቅርቡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይዘው አሜሪካ መግባታቸው ፕሬዚዳንቱ በባልደረቦቻቸው እንዲናቁ እንዳደረጋቸው የሚናገሩት ምንጮች፣ ባለፈው አርብ የተከሰተው ድርጊቱም የንቀቱን ደረጃ የሚያሳይ መሆኑን ይገልጻሉ።
አቶ ነቢል ከፕሬዚዳንቱ ጋር ለመነጋገር እንደሚፈልጉ ጸሃፊያቸውን አስፈቅደው ከገቡ በሁዋላ፣ የፕሬዚዳንቱን አንገት በማነቅ በቦክስ መማታት ሲጀምሩ ጸሃፊዎች ተሯሩጠው ለመገላገል ሞክረዋል። በጥበቃ ላይ የነበሩት ፖሊሶች በፍጥነት ደርሰው አቶ ነቢልን ይዘው የወጡ ሲሆን፣ አቶ ነቢል ይታሰሩ አይታሰሩ በሚለው ላይ ክፍፍል መፈጠሩንም ምንጮች ገልጸዋል። ይሁን እንጅ አቶ ነቢል ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ አለመታሰራቸውን ለማወቅ ተችሎአል። አቶ ነቢል የሀረሪ መዘጋጃ ቤት ሃላፊና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሆነው ሰርተዋል።
በሀረሪ ክልል ባለስልጣናት መካከል የሚታየው የእርስ በርስ ሽኩቻ ክልሉን በበላይነት ለሚያስተዳድሩት ለህወሃቱ ጄ/ል አብራሃ ወ/ምርያም ፈተና እንደሆነባቸውም ምንጮች ይገልጻሉ። በተለይ ከሃረሪ ተወላጆች ውጭ ያለው አብዛኛው ህዝብ በዘር መድሎ ከፍተኛ የሰብአዊና የአስተዳደር እግሮች እየደረሰበት መሆኑ፣ በክልሉ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ የሚችል ውጥረት እንዲፈጠር ማድረጉን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ምንጮች ይናገራሉ።
የሀረሪ ክልል 36 ቀበሌዎች ያሉት ሲሆን፣ በገጠር የሚኖረው አብዛኛው ህዝብ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሲሆን፣ በከተማ የሚኖረው ደግሞ በአብዛኛው አማርኛ ተናጋሪ ነው። ክልሉ አደርኛና ኦሮምኛን ብቻ የስራ ቋንቋ እንዲሆን በማድረጉ በክልሉ የሚኖረው ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነው የአማርኛና ሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ። ምንም ሰው ማመልከቻውን በአደርኛ ወይም በኦሮምኛ ካልጻፈ ተቀባይነት እንደማያገኝ የሚገልጹት ነዋሪዎች ለአስተርጓሚ በሚል ከፍተኛ ወጪ እንዲያወጡ እየተገደዱ ነው።